የጋና አጠቃላይ ምርጫ
ቅዳሜ፣ ኅዳር 28 2017ለሚቀጥሉት አራት ዓመታት ጋናን የሚመራ አዲስ ፕሬዝዳንት ለመምረጥ ዜጎች ዛሬ ድምጻቸውን ሲሰጡ ውለዋል። 12 እጩ ተወዳዳሪዎች በሚወዳደሩበት በዚህ ምርጫ ትልቁን የሀገሪቱን ሥልጣን ለመያዝ ከባዱ ፉክክር የሚካሄደው በገዥው «አዲስ የአርበኞች ፓርቲ» በእንግሊዘኛው ምህጻር NPP እጩ ምክትል ፕሬዝዳንት ማህማዱ ባዉምያና ፣በብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ምክር ቤት በምህጻሩ NDC ፓርቲ ፕሬዝዳንታዊ እጩ ጆን ድራማኒ ማሀማ መካከል ነው። ድራማኒ ከጎርጎሮሳዊው 2013 እስከ 2017 ዓ.ም. የጋና ፕሬዝዳንት ነበሩ። ለፕሬዝዳንትነት ሲወዳደሩ የአሁኑ ሦስተኛቸው ነው። በ2016 እና በ2020 ዓም ከተሰናባቹ ፕሬዝዳንት ናና አኩፎ አዶ ጋር ተወዳድረው አልተሳካላቸውም። የፕሬዝዳንት አኩፎ አዶ ምክትል ባዉሚያ በዚህ ምርጫ የገዥውን ፓርቲ ሥልጣን የማራዘም ተስፋ ሰንቀዋል።
የጋና ምርጫ እና የዕጩ ፕሬዚደንቶች የምርጫ ዘመቻ አንድምታ
ምርጫው በመላ ሀገሪቱ በሚገኙ ከ40ሺህ በላይ የምርጫ ጣቢያዎች በሀገሩ ሰዓት አቆጣጠር ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት አንስቶ ሲካሄድ ውሏል። ከ18 ሚሊዮን በላይ ዜጎች በዚህ ምርጫ ድምጽ የመስጠት መብት አላቸው። ግልጽነት ይጎድለዋል በሚለው በአንዳንድ ፓርቲዎች የሚደርሱበት ወቀሳዎች የሚቀርቡበት የጋና የምርጫ ኮሚሽን ሊቀመንበር ጂን ሜንሳ ምርጫው ሰላማዊ እና ተዓማኒ እንደሚሆን ቃል ገብተዋል።
«በጋና የምርጫ ኮሚሽን ስም በኔ የሚመራው ቡድን እና እኔ ፣ሰላማዊ ምርጫ እንዲካሄድ ለማረጋገጥ የሚያስችሉ እንቅስቃሴዎችን በምርጫው እለትም ሆነ ከዚያ በኋላ ባሉት ቀናት እናደርጋለን። በምርጫው እለትና ከዚያ በኋላ ባሉት ቀናት ሂደቱ ጠንካራ ግልጽና አሳታፊ ይሆናል። ይፋ የምናደርጋቸው ውጤቶች ዜጎች በምርጫው የሰጡትን ድምጽች የሚያንጸባርቁ ይሆናሉ። »
ኮሚሽኑ በቅርቡ ስለምርጫ ውጤት የሚድያ መረጃ አሰባሰብ ለመገደብ ያወጣው ፖሊሲ ቁጣ አስነስቶ ነበር። አሁን ግን ጉዳዩን እንደገና ለማየት ወስኗል። ዛሬ 275 መቀመጫዎች ያሉት የጋና ምክር ቤት አባላት ምርጫም ተካሂዷል። የፕሬዝዳንታዊው ምርጫ አሸናፊ ከ50 በመቶ ድምጽ በላይ ማግኘት አለበት። አንዳቸውም ከግማሽ በላይ ድምጽ ካላገኙ ግን ሁለተኛ ዙር ምርጫ ይካሄዳል።
ጋናውያን ከፕሬዝዳንታዊው ምርጫ አሸናፊ ብዙ ይጠብቃሉ። ብዙዎቹ ፖለቲከኞች በምርጫ ዘመቻ ወቅት የሚገቡ ቃሎች ተፈጻሚ ባለመሆናቸው ተስፋ ቆርጠዋል።ከመካከላቸው አንዱ አብዱላሂ ጀማል ነው። ሳቬልጉ ከተማ የሚኖረው ጀማልና ጎረቤቶቹ ፖለቲከኞች በአካባቢያቸው የልማት ስራ ባለማከናወናቸው ተማረዋል« እኛ እንመርጣለን ነገር ግን እኛን ትተው ለሌላው ኅብረተሰብ ነው ኤሌክትሪክ የሚዘረጉት፤ ኤሌክትሪክ እንደሚዘረጋልን ቃል የሚገቡልን ፖለቲከኞች ሁሉ ሲመረጡ ዞር ብለው አያዩንም» ብሏል። በዚህ የተነሳም ጀማልና ጎረቤቹ በአካባቢያቸው የልማት ስራ ካላዩ በስተቀር ድምጽ ላለመስጠት ወስነዋል። በአካባቢው ተመሳሳይ ችግር እንዳለ የተናገሩት ኢብራሂምም መብራት እስኪገባልኝ ድረስ አልመርጥም ብለዋል። ታዛቢዎች፣ ፖለቲከኞች ፣መራጮች ሁሌም ከኛ ጋር ናቸው ብለው ማሰብ ማቆም አለባቸው ይላሉ ።ዘንድሮ የሚካሄደው የጋና ምርጫ
ተፎካካሪዎቹ ባዉምያ እና ማሃማ በምርጫ ዘመቻቸው ያተኮሩት በጋና የኤኮኖሚ ተሀድሶ ላይ ነበር። ይህ ተሰናባቹን የአኩፎ አዶ አስተዳደርን ሰንጎ የያዘው ትልቁ ችግር ነበር።
ጋና ኤኮኖሚዋን ለማሻሻል ለዓመታት በዓለም የገንዘብ ድርጅት በሚመራ መርሃ ግብር ነው ስራዋን የምታካሂደው። በአሁኑ ጊዜ ለዓመታት በተከማቸ እዳ ምክንያት አብዛኛዎቹን የውጭ ብድሮቿን መክፈል አቅቷታል ። ያልተከፈለው ብድርም 30 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል። በዚህ ምርጫ ለፕሬዝዳንትነት የተወዳደሩት የኤኮኖሚ ባለሞያው የቀድሞ የማዕከላዊ ባንክ ሠራተኛ ባዉምያ ለጋና የምጣኔ ሀብት ችግሮች መፍትኄው የዲጂታል የፈጠራ ፖሊሲ ነው ሲሉ ቃል ገብተዋል።ይህን ማድረጊያው መንገድ ደግሞ ስልጣን መያዝ ነው። ባዉምያ፣ ሥልጣኑን መያዝ የሚፈልጉበትን ምክንያትም ዘርዘር አድርገው ተናግረዋል።
«ስልጣን የምንፈልግበት ብቸኛው ምክንያት ስልጣናችንን በመጠቀም የዚህችን ሀገር ህዝብ ለማበልጸግ ነው። ስለዚህ በሕጎቹ መሠረት ስራዬን ለማከናወንና ሰላማዊ ምርጫ እንዲካሄድ ለማረጋገጥም በሙሉ ልቤ በቁርጠኝነት ለመስራት ቃል እገባለሁ።»
በጋና ለወጣቱ ስራ ያስፈልጋል የሚሉት ባዉምያ የጋናን የኤኮኖሚ ችግሮች መፍቻ ያሉትንም እቅድ በምርጫ ዘመቻቸው ወቅት ሲያነሱ ነበር። ከመካከላቸው አንዱ ለአንድ ሚሊዮን ጋናውያን ወጣቶች የዲጅታል ክህሎት ስልጠና እንዲሰጥ አደርጋለሁ ያሉት ነው። ይህን ያሉትም ደቡብ ምሥራቅ የሀገሪቱ ክፍል በምትገኘው በቮልታ ግዛት የምርጫ ዘመቻ ሲያካሂዱ ነበር። በዚሁ ወቅትም ትምሕርታቸውን ያቋረጡም ቢሆኑ የዚህ እድል ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ቃል ገብተዋል። የቀድሞው ፕሬዝዳንት ማሀማም በበኩላቸው የጋናን እምቅ የኤኮኖሚ ኃይል ጥቅም ላይ አውላለሁ እያሉ ነው። ምንም እንኳን ፕሬዝዳንቱና ምክትል ፕሬዝዳንቱ ከ2 ሚሊዮን በላይ የስራ እድሎችን ፈጥረናል ቢሉም ሥራዎቹ የት አሉ ሲሉ ማሀማ ይጠይቃሉ።
የዛሚቢያ አና የጋና የዕዳ ቀውስ
እስከዛሬ በጋና የተካሄዱ ምርጫዎች ሰላማዊ ናቸው። ታዛቢዎች ፣በዛሬው ምርጫ የሚለወጥ ነገር ይኖራል ብለው አይጠብቁም። ሁለቱ እጩዎችም የምርጫው ውጤት ምንም ይሁን ምን እንቀበላለን የሚል ውል አስቀድመው ፈርመዋል።የቀድሞው ፕሬዝዳንት ጆና ማሀማ እንደተናገሩት እርሳቸውና ፓርቲያቸው ምርጫው ሰላማዊ እንዲሆን ቁርጠኛ ነን ብለዋል።
«ዛሬ እዚህ የመጣሁት የእኔንና የፓርቲየን የብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ምክር ቤት ለሰላሙ ማበብ ቁርጠኝነታችንን ለማስመዝገብ ነው። በማናቸውም ሁኔታ እኛ NDC ውስጥ ያለን ሰዎች ሰላማዊና የበለጸገች ሀገር ለመገንባት እና የፓርቲያችንንም ምኞቶችም ማሳካት እንዲቻል ሁሌም ቁርጠኞች ነን።»
አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢኖሩም ለመረጥነው መንገድ ለዴሞክራሲ ጀርባችንን ሰጥተን አናውቅም ያሉት ማሀማ በምርጫው እንደ ሀገር ጠንካራ ሆነን እንወጣለን ብለዋል።
ኂሩት መለሰ
አዜብ ታደሰ