1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጥቅምት 28 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የዓለም ዜና

Shewaye Legesseሐሙስ፣ ጥቅምት 28 2017

ኦሮሚያ ክልል ውስጥ የወረዳ ባለሥልጣናትን ጨምሮ 48 ሰዎች የተገደሉበትን ጥቃት እየመረመረ መሆኑን የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ዛሬ አስታወቀ። የባሕርዳር ከተማ አስተዳደር በእገታና በዘረፋ ተሰማርተው ነበር ያላቸውን ክ129 በላይ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ማዋሉን ገለጠ። የጀርመን የፋይናንስ ሚኒስትር ከሥልጣናቸው መነሳታቸውን ተከትሎ የሀገሪቱ ጥምር መንግሥት ቀውስ ውስጥ ገብቷል። ተቃዋሚዎች አስቸኳይ ምርጫ እንዲካሄድ ግፊት እያደረጉ ነው። ፕሬዝደንት ፍራንክ ቫልተር ሽታይን ማየር የጥምር መንግሥቱ ለገባበት ቀውስ መፍትሄ ለማምጣት ኃላፊነት የተሞላበት አካሄድ እንዲኖር ፖለቲከኞቹን አሳስበዋል።

https://p.dw.com/p/4mlwq

አዲስ አበባ፤ ኢሰመኮ ኦሮሚያ ክልል 48 ሰዎች የተገደሉበትን እየመረመረ መሆኑ

ኦሮሚያ ክልል ውስጥ የወረዳ ባለሥልጣናትን ጨምሮ 48 ሰዎች የተገደሉበትን ጥቃት እየመረመረ መሆኑን የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ዛሬ አስታወቀ። ድርጊቱ ባለፈው ሳምንት ሰሜን ሸዋ ውስጥ የተፈጸመው መንግሥት አሸባሪ ብሎ በፈረጀረው ታጣቂ ቡድን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ኦነሠ መሆኑን ኮሚሽኑ ይፋ ማድረጉን አዣንስ ፍራንስ ፕረስ ዘግቧል። የአካባቢው የኢሰመኮ ጽሕፈት ቤት ኃላፊም ጥቃቱ በተፈጸመበት አካባቢ ሁኔታዎች አሁንም በቋፍ መሆናቸውን መግለጻቸውንም ጠቅሷል። ኃላፊውም አክለውም ከተገደሉት ሌላ ቁጥራቸውን በውል ያልተገለጸ በርከት ያሉ ሰዎች መታገታቸውንም ገልጸዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለም በክልሉ ሰሜን ሸዋ ዞን ሰሞኑን ዳግም ባገረሸው የሰላም መደፍረስ ምክንያት የአካባቢው ነዋሪዎች ስጋት እንደገባቸው ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል።  የኦሮሚያ ክልል ከጎርጎሪዮሳዊው 2018 ዓ,ም አንስቶ በኦነሠ እንቅስቃሴ ሕዝባዊ አመጽ ውስጥ እንደምትገኝ የዜና ወኪሉ አመልክቷል። መንግሥት በኦሮሚያ ክልል ለሚፈጸሙ ግድያዎችም ሆኑ እገታዎች ኦነሠን ተጠያቂ ያደርጋል፤ ቡድኑ በበኩሉ በተደጋጋሚ የሚቀርቡበትን መሰል ክሶች ውድቅ አድርጓል።

 

ባሕር ዳር፤ የባሕርዳር ከተማ አስተዳደር ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉ

የባሕርዳር ከተማ አስተዳደር በእገታና በዘረፋ ተሰማርተው ነበር ያላቸውን ክ129 በላይ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታወቀ። አስተዳደሩ 17 የሚሆኑ በመሬት ወረራ ላይ ተስማርተው ነበር ያላቸውን ግለስቦችም መያዙን አመልክቷል።

የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር የሰላምና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊ አቶ ጌትነት አናጋው ከከተማ አስተዳደሩ ፖሊስ መምሪያ ጋር በጋራ በሰጡት መግለጫ በከተማዋ ተደራጅተው ሰው በማገት፣ በማስፈራራትና በመዝረፍ የተጠረጠሩ 121 ሰዎች በፖሊስ ተይዘው ምርመራ እየተካሄደ ነው ብለዋል።

የከተማው ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ዋለልኝ ቢምረው በበኩላቸው በተለያዩ የከተማው ከፍሎች በዚህ በጀት ዓመት ብቻ ከ40 በላይ የቦምብ ፍንዳታዎች መመዝገባቸውን፣ በ2016 እና 2017 ዓ ም ደግሞ 20 የእገታ ወንጀሎች መፈፀማቸውን ተናግረዋል።

ከኅብረተስቡ ጋር በተደረጉ ውይይቶችና መግባባቶች በርካታ አጋቾች በቁጥጥር መዋላቸውን በማመልከትም፤ ችግሩ አሁን ቀደም ሲል ከነበረው እየቀነስ እንደሆንም ጠቁመዋል። አንድ የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ በበኩላቸው አሁንም ችግሩ ሙሉ በሙሉ ተቃልሏል እንደማይባል ነው የተናገሩት። እሳቸው እንደሚሉትም ከነበረው ሰጋት ጋር ሲነፃጸር የእገታ ወልጀል በተወሰን ደረጃ ቀንሷል።

 

በርሊን፤ የጀርመን ጥምር መንግሥት ቀውስ

የጀርመን የፋይናንስ ሚኒስትር ከሥልጣናቸው መነሳታቸውን ተከትሎ የሀገሪቱ ጥምር መንግሥት ቀውስ ውስጥ ገብቷል። ተቃዋሚ ፓርቲዎችም የመራኄ መንግሥት ኦላፍ ሾልስ አስተዳደር ባስቸኳይ ምርጫ እንዲያካሂድ ግፊት እያደረጉ ነው። ምክር ቤቱም የመተማመኛ ድምፅ እንደሰጥ ጠይቀዋል። ጥምር መንግሥቱ ትናንት ማምሻውን ባካሄደው አጣዳፊ ስብሰባ ላይ የነጻ ዴሞክራት ፓርቲው የፋይናስ ሚኒስትር ክርስቲያን ሊንድነር አዲስ ምርጫ እንዲካሄድ ጠየቁ፤ ሃሳቡን የተቃወሙት ሾልስ፤ ወዲያው ከሥልጣን አሰናበቷቸው። ውሳኔያቸውን ተከትሎም ሀገሪቱን የሚያስተዳድረው የሦስቱ ማለትም የሶሻል ዴሞክራት፤ የነጻ ዴሞክራት እና የአረንጓዴ ፓርቲ ጥምር መንግሥት ችግር ውስጥ መግባቱ ነው የተነገረው። የጀርመን ፕሬዝደንት ፍራንክ ቫልተር ሽታይን ማየር የጥምር መንግሥቱ ለገባበት ቀውስ መፍትሄ ለማምጣት ኃላፊነት የተሞላበት አካሄድ እንዲኖር ፖለቲከኞቹን አሳስበዋል።

«አሁኑ ጊዜ የታክቲክ እና ግጭት አይደለም። ጊዜ የምክንያታዊነት እና የኃላፊነት ነው። እያንዳንዱ ሀላፊነት ይወስዳል ብዬ እጠብቃለሁ። በኃላፊነት ላይ ያሉ ሁሉ የገጠመንን ተግዳሮት እንደሚቋቋሙ እጠብቃለሁ። ሀገራችን የተረጋጋ ብዙሃን እና አቅም ያለው መንግሥት ትፈልጋለች።»

ፕሬዝደንት ሽታይን ማየር በሾልስ ጥምር መንግሥት ካቢኔ ውስጥ ለነበሩ ሦስት የነጻ ዴሞክራት ፓርቲ ሚኒስትሮችም የስንብት ደብዳቤ ሰጥተዋል። የፋይንስ ሚኒስትሩን ጨምሮ፤ የፍትህ ሚኒስትሩ ማርኮ ቡሽማን እንዲሁም የትምህርት ሚኒስትሯ ቤቲና ሽታርክ ቫትሲንገር ተሰናብተዋል። የሾልስ የኤኮኖሚ አማካሪ የነበሩት ዮርግ ኩኪስ የፋይናንስ ሚኒስትር ሆነው ተሰይመዋል። ሦስት ፓርቲዎች የመሠረቱት የጀርመን ጥምር መንግሥት ያለፉትን ሦስት ዓመታት በበርካታ ፈተናዎች ታጅቦ ዘልቋል።

 

ቤይሩት፤ በእስራኤል ጥቃት ሊባኖስ ውስጥ ሦስት ተገደሉ

በደቡባዊ ሊባኖስ ሲዶን ከተማ ላይ እስራኤል በአየር ባካሄደችው ጥቃት ቢያንስ ሦስት ሲገደሉ በርካቶች መጎዳታቸውን የሊባኖስ ጦር ዛሬ አስታወቀ። በጥቃቱ የተመድ የሰላም አስከባሪዎችም መጎዳታቸው ተገልጿል። የሊባኖስ ጦር በአንድ መስመር በሰጠው መግለጫ ጥቃቱ የመኪና መፈተሻ ጣቢያ ላይ ያነጣጠረ እንደነበር ማመልከቱን የጀርመን የዜና ወኪል ዲፒኤ ዘግቧል። በስፍeራው ተሽከርካሪ ውስጥ የነበሩ ሦስት የሊባኖስ ዜጎች መገደላቸውን፤ ሌሎች ሦስት የሊባኖስ ወታደሮችም፤ ለሰላም ማስከበር ከተሰማሩ ከማሌዢያ ወታደሮች ጋር መጎዳታቸውን ጦሩ አመልክቷል። የእስራኤል ጦር ሲዶን ላይ የተፈጸመውን ጥቃት አረጋግጦ፤ ሰላም አስከባሪዎች ስለመጎዳታቸው እንደሚያጣራ መግለጹን ዘገባው አመልክቷል። የጥቃቱ አላማ ሲቪሎችና ሰላም አስከባሪዎችን መጉዳት አይደልምም ማለቱ ተገልጿል።

 

ዋሽንግተን፤ ባይደን ለአሜሪካ ሕዝብ ንግግር ያደርጋሉ

ተሰናባቹ የአሜሪካን ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ዛሬ ለሀገሪቱ ሕዝብ ንግግር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል። በፕሬዝደንታዊ ምርጫው ድል የቀናቸው ዶናልድ ትራምፕ በቀጣይ አብረዋቸው አሜሪካንን የሚመሩ ባለሥልጣናትን ለመምረጥ እየሠሩ ነው በሚባልበት በዚህ ሰዓት ባይደን እተጩም ቢሆን ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ለማድረግ ቃል የሚገቡበትን ንግግር ለማድረግ መዘጋጀታቸውን አሶሲየትድ ፕረስ ከዋሽንግተን ዘግቧል። በዕድሜያቸው መግፋት ምክንያት ለምርጫው ብቁ አይደሉም በሚል ወደጎን የተገፉት የ81 ዓመቱ ተሰናባቹ ፕሬዝደንት የእሳቸውን የእጩነት ስፍራ ለምክትላቸው ካማላ ሃሪስ አሳልፈው ለመስጠት ተገደዋል። የምር|ጫው ውጤት ይፋ ከሆነ በኋላም ባይደን ትናንትናውን ከትራምፕ ጋር በስልክ የተነጋሩ ሲሆን ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር እንዲኖር እንደሚሠሩ ቃል መግባታቸውን ዋይት ሃውስ አመልክቷል። ባይደን በዋሽንግተን ሰዓት አቆጣጠር ከቀኑ አምስት ሰዓት ላይ በሮዝ ጋርደን ለመላው አሜሪካውያን ንግግር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።  

 

ማድሪድ፤ ከ13 ቶን አደንዛዥ ዕጽ መያዙ

የስፔን ባለሥልጣናት 13 ቶን ማለትም 13 ሺህ ኪሎ ግራም ኮኬይን መያዛቸውን አስታወቁ። ባለሥልጣናቱ የሙዝ ጭነት ውስጥ ያገኙት ኮኬይን በሀገሪቱ የጸረ አደንዛዥ ዕጽ ዘመቻ ታሪክ የተያዘ መጠኑ የበዛው ይህ መሆኑን አመልክተዋል። አደንዛዥ ዕጹ የተገኘው በደቡባዊ ስፔን የባሕር ወደብ መልሕቋን ከጣለች ፍራፍሬ የጫነች መርከብ ውስጥ ነው። ጭነቱ ከኤኳዶር የተነሳ መሆኑ ነው የተገለጸው። ካለፈው አንስቶ ከኤኳዶር ፖሊስ ጋር በመተባበው የተካሄደው ይህ ዘመቻም አምስት አሰሳና ፍተሻዎችን ያካተተ ሲሆን አንድ ሰው ታስሯል።

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋኅ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ስለዚሕ ዝግጅት

ስለዚሕ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።