1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጥቅምት 29 ቀን 2017 ዓ/ም የዓለም ዜና

Tamirat Geletaዓርብ፣ ጥቅምት 29 2017

አርስተ ዜና፤ --በአማራ ክልል ሰሜን ጎጃም ዞን አቸፈር ወረዳ ባለፈው ማክሰኞ ጥቅምት 26/2017 በድሮን በተፈፀመ ጥቃት ከ40 በላይ ሰዎች መገደላቸውንና 9 መቁሰላቸውን ነዋሪዎች ተናገሩ። --የኢትዮጵያ የገንዘብ ሚኒስቴር በፍራንኮ ቫሉታ ሸቀጦችን ወደ ሃገር ውስጥ ማስገባት ከዛሬ ጀምሮ አገደ። --አቶ ዮሃንስ ቧያሌው 1ኛ ተከሳሽ በሆኑበት መዝገብ የተከሰሱና ጉዳያቸው በፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት እየታየ ያለው ግለሰቦች ለሕዳር 20 ቀን 2017 ዓ.ም ተቀጠሩ። --በጋዛ ጦርነት ከተገደሉት ውስጥ 70 በመቶ ያህሉ ሴቶች እና ህጻናት መሆናቸው መለየቱን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታወቀ። ሙሉዉን ዜና ያድምጡ!

https://p.dw.com/p/4mobC

 

በአማራ ክልል ሰሜን ጎጃም ዞን አቸፈር ወረዳ ባለፈው ማክሰኞ ጥቅምት 26/2017 በድሮን በተፈፀመ ጥቃት ከ40 በላይ ሰዎች ተገደሉ።

በጥቃቱ ሌሎች 9 መቁሰላቸውን  የአካባቢው ነዋሪ ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋል፡፡

በእለቱ ጠዋት 1 ሰዓት አካባቢ “ዝልስት” በተባለ ቦታ ላይ በተከታታይ በድሮን በተፈጸመው ጥቃት  ህፃናትና ሌሎች ሰላማዊ ሰዎችን ጨምሮ  ከ40 በላይ ሰዎች መገደላቸውን ነው በቀብር ላይ መገኘታቸውን የገለጹ አንድ የአቸፈር ወረዳ ነዋሪ ተናግረዋል።

ሌላ ስማቸው እንዳይጠቀሱ የጠየቁ የአካባቢው ነዋሪም ተመሳሳይ ጥቃት መድረሱንና ሰዎች መገደላቸውን ተናግረዋል።

በአማራ ክልል ባለፈው ዓመት በፋኖና የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች መካከል እየተደረገ ባለው ውጊያ  በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች በሰው አልባ አውሮፕላኖች በደረሱ ጥቃቶች ሰላማዊ ሰዎች ጭምር መገደላቸውን የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪ ድርጅቶች በተከታታይ ሲያሳስቡ ቆይተዋል።

ዶቼ ቬለ በጉዳዩ ዙሪያ የዞኑን ዋና አስተዳዳሪ ጨምሮ የሚመለከታቸውን አካላት አስተያየት ለማካተት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።  

 

 

ኢትዮጵያ የገንዘብ ሚኒስቴር በፍራንኮ ቫሉታ ሸቀጦችን ወደ ሃገር ውስጥ ማስገባት ከዛሬ ጀምሮ አገደ።

ሚኒስቴሩ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እና ለጉሙሩክ በላከው ደብዳቤ  ስራ ላይ የነበረው አሰራር ዘላቂነት ባለው እና በተሻለ አሰራር እንዲተካ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን በምክንያትነት ጠቅሷል።

መግስት የኤኮኖሚ ማሻሻያ መርኃ ግብሩን ተግባራዊ ባደረገበት ወቅት የምግብ ዘይትን ጨምሮ የምግብ ሸቀጦች እና  የኢንደስትሪዎች የምርት ግብዓቶች በፍራንኮ ቫሉታ ወደ ሃገር ውስጥ እንዲገቡ መፈቀዱ ይታወሳል።

የገንዘብ ሚኒስቴር በደብዳቤው በፍራንኮ ቫሉታ ግዢ የተፈጸመባቸው ቁሳቁሶች በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ወደ ሃገር ውስጥ መግባት እንዳለባቸው ሲያመለክት ከዚያ ውጭ ያሉ ደብዳቤው ከተጻፈበት ከትናንት ጥቅምት 28 ቀን ጀምሮ መታገዱን የሀገር ውስጥ የመገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

የገንዘብ ሚኒስቴር በደብዳቤው የውጭ ምንዛሬ በንግድ ባንኮች በኩል በበቂ መጠን እየቀረበ መሆኑንንም  ዶቼ ቬለ ተመልክቷል።

 

አቶ ዮሃንስ ቧያሌው 1ኛ ተከሳሽ የሆኑበት የክስ መዝገብ ሥር የተከሰሱ እና  ጉዳያቸው በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት እየታየ ያለው ግለሰቦች ለ ሕዳር 20 ቀን 2017 ዓ.ም ተቀጠሩ።

ተከሳሾቹ ለዛሬ ጥቅምት 29 ቀን 2017 ዓ. ም በፌዴሬል ከፍተኛው ፍርድ ቤት የሕገ-መንግሥት እና የሽብር ወንጀል ጉዳዮች ችሎት የቀረቡት ዐቃቤ ሕግ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ያቀረበበትን የክስ ማሻሻያ ብይን ለመስማት ነበር።

ሆኖም ጠቅላይ ፍርድ ቤት በዐቃቤ ሕግ የክስ ይሻሻል ይግባኝ ላይ ብይን ለመስጠት ለሕዳር 19 የቀጠረ በመሆኑ ዛሬ የተሰየመው የከፍተኛው ፍርድ ቤት ጉዳዩን መመልከት እንዳልቻለ እና ጉዳዩን ለመመልከት ለሕዳር 20 ቀን  ቀጠሮ መሰጠቱን ከተከሳሽ ጠበቆች አንደኛው ሰለሞን ገዛኸኝ ተናግረዋል።

ተከሳሾች እና ጠበቆቻቸው ለችሎቱ በፍርድ ሂደቱ ላይ ቅሬታ አሰምተዋል ያሉት ጠበቃው ከተከሳሾች መካከል አቶ ዮሃንስ ቧያሌው እና አቶ ክርስትያን ታደለ ልዩ ሕክምና እንዲያገኙ ያቀረቡትን ጥያቄ መነሻ አድርጎ ፍርድ ቤቱ ከዚህ በፊት የሰጠው ትዕዛዝ ባለመፈፀሙ፣ ማረሚያ ቤት የችሎቱን ትዕዛዝ እንዲያስፈጽም ዛሬ በድጋሜ መታዘዙን ገልፀዋል። 

 

 

የኮሞሮስ ፖሊስ በርካቶችን ለህልፈት በዳረገ የጀልባ አደጋ ህገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪ ቡድን መሪ ነው ያለውን ሰው መያዙን አስታወቀ።

ባለፈው ሳምንት አርብ በኮሞሮስ የአንጁዋን ደሴት አቅራቢያ ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር በሚዘወትርበት የህንድ ውቅያኖስ ክፍል በሰጠመች ጀልባ የ25  ሰዎች ህይወት አልፏል።

የሰጠመችው ጀልባ ባለቤት እና የህገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪ ቡድን መሪ የሆነውን የ37 ዓመት ጎልማሳ በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን የኮሞሮስ ፖሊስ አዛዥ ኮሎኔል ታችፍኔ አህመድ ለፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ተናግረዋል።

ዓለም አቀፉ የስደተኞች ጉዳይ ድርጅት (አይኦኤም) ባለፈው ሰኞ ዕለት ባወጣው መግለጫ ጀልባዋ  ሆን ተብሎ እንድትገለበጥ መደረጓ ለሰዎቹ ህልፈት ምክንያት መሆኑን ማረጋገጡን ጠቅሷል።

ጀልባዋ በሰጠመችበት ወቅት አቅራቢያ የነበሩ የአሳ አጥማጆች የአምስት ሰዎችን ህይወት አትርፈዋል።

በቁጥጥር ስር የዋለው ተጠርጣሪው ግለሰብ ከተመሰረተበት የሰው መግደል ወንጀል በተጨማሪ በተደራጀ የወንጀል ቡድን አባል በመሆን እስከ 10 አመት የሚደርስ እስራት ሊቀጣ እንደሚችል በዘገባው ተመላክቷል። በተጨማሪም  በህገ-ወጥ መንገድ ሰዎችን በማጓጓዝ የ3 አመት እስራት ይጠብቀዋል ነው ፤ የተባለው።

በኮሞሮስ በርካታ  አዘዋዋሪዎች “ኩሳ-ክዋሳ” በተባሉ አነስተኛ  የአሳ ማጥመጃ ጀልባዎች በተጨናነቀ ሁኔታ  በአደገኛውን የባህር መተላለፊያ ሰዎች በማሸጋገር ስራ ላይ ተሰማርተዋል።

 

                                                

በሱዳን በፈጥኖ ደራሽ አር ኤስ ኤፍ ወታደሮች ተከባ በምትገኘው የአል ሂላይላ ከተማ 73 ሰዎች ምክንያቱ ባልታወቀ ህመም መሞታቸውን የየሱዳን የሐኪሞች ህብረት ዛሬ አስታወቀ።

ከተማዋ በቅርቡ በፈጥኖ ደራሽ ወታደሮች የብቀላ ጥቃት ከደረሰባቸው በርካታ ከተሞች አንዷ ስትሆን ጥቃቱን ተከትሎ ከ135 ሺ በላይ ነዋሪዎች መኖሪያቸውን ጥለው ተሰደዋል።

የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ወታደራዊ አዛዥ የነበረው አቡ አግላ ኬይ ቃል ከነ ወታደሮቹ ቡድኑን ከድቶ ብሔራዊ ጦሩን መቀላቀሉን ተከትሎ ቡድኑ በምስራቃዊ የኤል ጄዚራ ግዛት በመቶዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ህልፈት እና ቁስለት ምክንያት የሆነ የብቀላ እርምጃ አስከትሏል።

በከተማዋ የግንኙነት መቋረጥ ተከትሎ ሰሞንኑ ለበርካታ ሰዎች ሞት ትክክለኛ ምክንያቱን ማወቅ እንዳልቻለ የሀኪሞች ህብረት ገልጿል። ሮይተርስ በተናጥል ያነጋገረው አንድ የከተማዋ ነዋሪ ሶስት የቤተሰቡ አባላት ምንነቱ ባልታወቀ በሽታ ሞተው መገኘታቸውን ተናግሯል።  

በፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ከበባ ስር በምትገኘው ከተማዋ በርካታ የመንግስት እና የግል የንግድ ተቋማት መዘረፋቸውን ያመለከተው ዘገባው በከተማዋ በትክክል ስለደረሰ ሰብአዊ እና ቁሳዊ ውድመት መገመት አዳጋች መሆኑን አመልክቷል።

 

የእስራኤል፣ የኔዘርላንድ እና ሌሎች የአውሮጳ መሪዎች ትናንት አርብ ምሽት በአምስተርዳም ከአውሮጳ ሊግ የእግር ኳስ ጨዋታ በኋላ በእስራኤል ደጋፊዎች ላይ የተፈጸመውን  የ “ፀረ-ሴማዊ” ጥቃት አወገዙ ።   

እስራኤል በተናጥል ለዜጎቿ የነፍስ አድን አውሮፕላኖችን ልካለች። ጥቃቱን ተከትሎ አምስት ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ሆስፒታል ሲወሰዱ በጥቃቱ ተሳትፈዋል የተባሉ 62 ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የኔዘርላንድ ፖሊስ አስታውቋል።

ጥቃቱ የኔዘርላንዱ አያክስ አምስተርዳም የእስራኤሉን ማካቢ ቴል አቪቭን አስተናግዶ 5 ለ 0 በሆነ ሰፊ ዉጤት ካሸነፈ በኋላ በእስራኤል ደጋፊዎች ላይ ከስቴዲየም ዉጪ ግጭት መቀስቀሱን ፖሊስ ገልጿል።

 የእስራኤሉ ፕሬዚዳንት ኢሳቅ ሄርዞግ ግጭቱን አውግዘው በኤክስ ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት ግጭቱን ያስመለከቱ ምስሎች ባለፈው ዓመት ሃማስ በእስራኤል ላይ የፈጸመውን ጥቃት ያስታውሰናል ብለዋል። የጀርመኑ መራሄ መንግስት ኦላፍ ሾልዝ በበኩላቸው በአምስተርዳም በእስራኤል ደጋፊዎች ላይ የተፈጸመውን ጥቃት «አሳፋሪ » እና ተቀባይነት የሌለው ሲሉ አውግዘዉታል።

የአውሮጳ ህብረት ኮሚሽን ፕሬዚደንት ኦርሱላ ፎን ደር ላየንን ጨምሮ የኔዘርላንድ እና ፈረንሳይ እንዲሁም የሌሎች የአውሮጳ ሃገራት  እንዲሁ ክስተቱን በጽኑ ማውገዛቸውን የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።

 

 

በጋዛ ጦርነት ከተገደሉት ውስጥ 70 በመቶ ያህሉ ሴቶች እና ህጻናት መሆናቸው መለየቱን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታወቀ። 

በጋዛ ጦርነት ዓለማቀፍ መሰረታዊ የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎች መጣሳቸውን ያመለከተው የድርጅቱ መግለጫ በስልታዊ መንገድ ተፈጽሟል ያለውን ግድያ እንደሚቃወም ገልጿል።

እስራኤል ከሃማስ ታጣቂ ቡድን ጋር እያደረገች ባለው ጦርነት የሟቾችን መረጃ ከሶስት የመረጃ ምንጮች ብቻ ማሰባሰቡን የገለጸው ዓለማቀፉ ድርጅት በጦርነቱ የተገደሉ ሰዎችን ለይቶ የመቁጠር ስራው መቀጠሉን አመልክቷል።

በጦርነቱ የተገደሉ የ8,119 ተጎጂዎችን መረጃ ማሰባሰቡን ያመለከተው መረጃው ነገር ግን በፍልስጥኤል የጤና ሚኒስቴር ከቀረበው የ43 ሺ ሰዎች መረጃ ጋር በእጅጉ እንደሚራራቅ የሮይተርስ ዘገባ አመልክቷል።

ነገር ግን የመንግስታቱ ከዚሁ ሰበሰብኩ ባለው መረጃ በጦርነቱ በከፍተኛ ደረጃ ተጎጂዎች ናቸው ያላቸውን ሴቶች እና ህጻናት በዕድሜ ጭምር ለይቶ መያዙን ገልጿል።

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔትያናሁ በጉዳዩ ላይ መልስ እንዲሰጡ መጠየቁን የጠቀሰው የዜና ምንጩ ነገር ግን ምላሽ አለማግኘቱን አስነብቧል።

እንዲያም ሆኖ ግን በጋዛ በቀጠለው ጦርነት ሃማስ ሲቪሊያዉያንን መሸሸጊያ አድርጓል ስትል እስራኤል ትከሳለች።

ታምራት ዲንሳ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ስለዚሕ ዝግጅት

ስለዚሕ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።