የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት አፈጻጸም ግምገማ
ሐሙስ፣ የካቲት 28 2016የአፍሪካ ህብረት የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ መንግስት እና ህዝባዊ ወያኔ ኃርነት ትግራይ (ህወሓት) ከአንድ ዓመት ተኩል ገደማ በፊት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የተፈራረሙትን ስምምነት አተገባበር መገምገም ጀመረ፡፡ ይህ የተሰማው በሁለቱ ወገኖች በኩል በስምምነቱ ሁለንተናዊ አተገባበር ላይ የተለያዩ የሚያወዛግቡ አስተያየቶችን መስጠታቸው ከቀጠሉ በኋላ መሆኑ ነው፡፡
በሰሜን ኢትዮጵያ የኢትዮጵያ መንግስት ኃይሎች እና የትግራይ ክልል ኃይሎች መካከል ለሁለት ዓመታት የቆየው ደም አፋሳሽ ጦርነት እዲያበቃ የረዳውን የፕሪቶሪያ ስምምነት ገቢራዊነት ላይ አሸማጋዩ የአፍሪካ ህብረት የእስካሁኑን አፈጻጸም አዲስ አበባ ውስጥ ለመገምገም ስብሰባ ሲቀመጡ፤ የተባበሩት መንግስታት፣ የአውሮጳ ኅብረት፣ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (IGAD) እና ዩናይትድ ስቴትስ በታዛቢነት ሂደቱን ይከታተሉታል ተብሏል፡፡ስብሰባው ከዛሬ ጀምሮ አዲስ አበባ ውስጥ እንደሚካሄድ ጥቆማዎች ብሰሙም የሂደቱ ዝርዝር ጉዳይን በተመለከተ ግን የተሰጡ ግልጽ ማብራሪያዎች የሉም፡፡
ዶቼ ቬለ ስምምነቱን በተመለከተ የእስካሁን ሂደቱን ይገመግማል ስለተባለው ስለዚህ ስብሰባ ዝርዝር ጉዳዮች ከኢትዮጵያ መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ኃላፊዎች፣ ከኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ፣ ከትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ እንዲሁም ከአፍሪካ ህብረት ቃል አቀባይ ጽ/ቤት ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት ያደረገው ጥረት ለዛሬ አልሰመረም፡፡
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር አቶ ጌታቸው ረዳ በይፋዊ ማህበራዊ ገጻቸው ላይ ባስነበቡት መረጃ ግን፤ የአፍሪካ ህብረት የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት እንዲያበቃ የረዳው የፕሪቶሪያው ስምምነት የእስካሁኑ አተገባበር የሚገመግም ስትራቴጂካዊ ስብሰባ መጀመሩን አረጋግጠዋል፡፡
የፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት አፈፃፀምና ትችቱ
አቶ ጌታቸው በዚሁ ጽሁፋቸው “ይህ ፎረም ሁለቱ አካላት ማለትም የፌዴራል መንግስት እና የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ከአፍሪካ ህብረት የስምምነቱ ተወካዮች ጋር ተቀምጠው የስምምነቱ የእስካሁን አተገባበርን የሚገመግሙበት ነው” ሲሉ ጠቁመዋል፡፡ አቶ ጌታቸው አክለውም የተባበሩት መንግስታት፣ የአውሮፓ ህብረት፣ የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት (IGAD) እና ዩናይትድ ስቴትስ በታዛቢነት እንደሚቀመጡም አክለው ጠቅሰዋል፡፡
አቶ ጌታቸው አክለውም “ዘላቂ ሰላም በኢትዮጵያ እና በቃጣናው ማስፈን ከተቻለ የፕሪቶሪያውን ስምምነት በሙሉ አቅም ገቢራዊ በማድረግ የትግራይ ህዝብ ህገመንግስታዊ ፍላጎት ማሟላት ይቻላል” ሲሉም በጽሁፋቸው ጠቁመዋል፡፡ በመሆኑም ይህ እንዲሆን የሚቻለንን ሁሉ ማድረግ አለብን ሲሉም አስተያየታቸውን ቋጭተዋል፡፡የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤትም ትናንት ማምሻውን ባወጣው ይፋዊ መግለጫ በምስራቅ አፍሪካ የአሜሪካ ልዩ መልእክተኛ አምባሳደር ማይክል ሐመር ከዛሬ ጀምሮ ለሰባት ተከታታይ ቀናት ወደ አዲስ አበባ ማቅናታቸውን አመልክቷል፡፡
ዓመት ስለደፈነው የፕሪቶሪያው ስምምነት የፖለቲከኞች አስተያየት
ልዩ መልእክተኛው በቆይታቸው የአፍሪካ ህብረት የፕሪቶሪያው ስምምነት አተገባበር ግምገማ ላይ እንደሚታደሙም ይህ የዩናይትድ ስቴትስ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የላከልን የኢ-ሜይል መረጃ አትቷል፡፡የውጭ መስሪያ ቤቱ መረጃ የፕሪቶሪያው ስምምነት በሰሜን ኢትዮጵያ ለበርካቶች ሞት እና ለንብረት ውድመት ምክኒያት የሆነውን ጦርነት በመግታት የመሳሪያ ደምጽ እንዳይሰማ አይነተኛ ሚና መጫወቱን በአዎንታዊነት በማንሳት፤ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ግን ተጨማሪ ሂደቶች ያስፈልጉታል ሲል አስረድቷል፡፡ የስምምነቱ ቀሪ ስራዎች ትጥቅ በማውረድ የጸጥታ ኃይሎች መዋቅራዊ መቀላቀል( reintegration)፣ የሽግግር ፍትህ ሂደቶችን ማቀላጠፍ እና ተፈናቃዮችን በዘላቂነት ወደ ቀዬያቸው መመለስ ናቸው ሲል ጠቁሟልም፡፡
ልዩ መልእክተኛው ሐመር በኢትዮጵያ ቆይታቸው ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋር በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ግጭቶችን መቋጨት በሚቻልበት መንገድ ላይ እንደሚወያዩም ተጠቁሟል፡፡ በተጨማሪም በፕሪቶሪያ ስምምነት አፈጻጸም ላይ ከምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት (IGAD) እና ሌሎች ዓለማቀፍ አጋር ተቋማት ጋር እንደሚወያዩም ነው የተገለጸው፡፡
በጎርጎሳውያኑ 2022 መጨረሻ በፕሪቶሪያ በስምምነት የተቋጨው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ለበርካቶች እፎይታን የሰጠ መሆኑ በጉልህ ብነሳም፤ በአፈጻጸሙ ላይ ስምምነቱን የፈረሙ ሁለቱ ኃይሎች አልፎ አልፎም ብሆን ስወዛገቡ ይስተዋላል፡፡ የኤርትራ ሰራዊት ፈጽሞ ከሁሉም ትግራይ ክልል አከባቢዎች አለመውጣት፣ ከአወዛጋቢዎቹ የአማራ እና ትግራይ ክልል አዋሳን ግዛቶች የተፈናቀሉ የትግራይ ተወላጆች ወደ ቀዬያቸው አለመመለስ እና የእርዳታ አቅርቦት ሁለቱን አካላት ካወዛገቡ ነጥቦች ናቸው፡፡
ስዩም ጌቱ
ኂሩት መለሰ
ነጋሽ መሐመድ