1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አቋም

ዓርብ፣ ጥር 3 2016

ከሰሞኑ የኢትዮጵያ መንግስት ከራስ ገዟ ሶማሌላንድ ጋር የፈረመውን የፍላጎት ማሳያት የመግባቢያ ሰነድ እንደሚደግፍ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አስታወቀ፡፡ ይሁንና መንግስት አስቀድሞ በመሰል አወዛጋቢ አገራዊ ጉዳዮች ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ጨምሮ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር አለመወያይቱን በብርቱ ተችተዋል፡፡

https://p.dw.com/p/4bAvF
የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት
የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ምስል Solomon Muche/DW

መንግስት አስቀድሞ በመሰል አወዛጋቢ አገራዊ ጉዳዮች ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ጨምሮ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር አለመወያይቱን በብርቱ ተችተዋል፡፡

ከሰሞኑ የኢትዮጵያ መንግስት ከራስ ገዟ ሶማሌላንድ ጋር የፈረመውን የፍላጎት ማሳያት የመግባቢያ ሰነድ እንደሚደግፍ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አስታወቀ፡፡ ይሁንና መንግስት አስቀድሞ በመሰል አወዛጋቢ አገራዊ ጉዳዮች ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ጨምሮ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር አለመወያይቱን በብርቱ ተችተዋል፡፡ በሌላ በኩል አብላጫው የፖለቲካ ፓርቲዎች ምክር ቤት አባላቱ የፖለቲካ ድርጅቶች በኢትዮጵያ አለመግባባቶች እንዲቀረፉ የተቋቋመውን የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን የስራ ሂደትን አድምጠው ሂደቱን እንደሚደገፉም ነው የተመላከተው፡፡

የኢትዮጵያ  ፖለቲካ  ፓርቲዎች  የጋራ  ም/ቤት  ከትናንት በስቲያ ጥር 01 ቀን 2016 ዓ.ም. አደረኩ ባለው ጠቅላላ ጉባኤ በቀዳሚነት ከሰሞኑ በኢትዮጵያ መንግስት እና ራስ ገዟ ሶማሌ ላንድ መካከል የተፈረመውን የወደብ "የመግባቢያ ሰነድ" በተመለከተ የስምምነቱን ማዕቀፍ፣ ዝርዝር ይዘቱን እና ከስምምነቱ ጋር ተያይዞ ባሉት እድሎችና ስጋቶች ላይ መወያየቱን አስታውቋል፡፡ ምክር ቤቱ አደረኩ ባለው ጥልቅ ውይይትም ስምምነቱ የሚኖረውን ውስጣዊ እና ውጫዊ ስጋቶችን እና እድሎችን በዝርዝር ተመልክቶ ለስመምምነቱ ያለውን ድጋፍ ገልጿል፡፡ የፓርቲዎቹ ምክር ቤት “ለስምምነቱ ውጤታማነት በጋራ በመቆም ሚናችንን ለመወጣት ያለንን ቁርጠኝነት እናረጋግጣለን” በማለት ህብረተሰቡ አውንታዊ ሚና እንዲወጣም ጥሪ አቅርቧል፡፡

የምክር ቤቱ ሰብሳቢ ፖለቲከኛ ደስታ ዲንቃ የምክር ቤቱ ስራ አስፈጻሚ ጠርቷል ያሉት በዚህ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ “በሳልና ጥልቅ” ያሉት አስተያየቶች መንጸባረቃቸውን ለዶቼ ቬለ በሰጡት ተጨማሪ አስተያየት አብራርተዋል፡፡ “በጠቅላላ ጉባኤው ላይ የተለያዩ ሃሳቦች በጥልቅ ተነስተዋል፡፡ በሳል ውይይት ነበር የተካሄደው፡፡ ከመንግስት የመጣ የመንግስት ተወካይም ስምምነቱ ያለፈበትን ሂደት አስረድተዋል፡፡ በዚያው መሰረት ከቤቱ ያሉትን ስጋቶች እና እድሎች በተመለከተ የተለያዩ አስተያየቶች ተሰጥቶ ተመክሮበታል” ነው ያሉት፡፡

ከስምምነቱ የአገር ውስጥ ባለድርሻ አካላት ውይይት የማስቀደም ጥያቄ

ከሰሞኑ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ባወጣው መግለጫ ስምምነቱን ተከትሎ ከጎረቤት አገር ሶማሊያ የተነሳውን ከፍተኛ የዲፕሎማሲ መሻከር ተከትሎ በዚያ ባሉ ኢትዮጵያውያን ዜጎች ላይ ጉዳት እንዳይፈጸም ሲል ጠይቋል፡፡ መንግስት መሰል ቃጣናዊና ዓለማቀፋዊ ጉዳይ ውስጥ ሲገባ የአገር ውስጥ ችግሮችን አስቀድሞ በማስወገድና ባለድርሻ አካላትን በማወያየት መሆን እንደሚገባም ማንሳቱ ይታወቃል፡፡ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ደስታ ዲንቃ በከትናንት በስቲያው የምክር ቤቱ ስብስባ ላይም ይህ ሃሳብ በጉልህ መንጸባረቁን አልሸሸጉም፡፡ “ይህ ሃሳብ በጥልቀት ነው የተነሳው፡፡ በመንግስት በኩል የቀረቡ የመንግስት ተወካይም ጉዳዩ በምስጥር የተያዘበትና ለውይይት ያልቀረበበትን ምክኒያት አስረድተዋል፡፡ መንግስት አስቀድሞ ሊያወያየን ይገባ የነበረ ቢሆንም የሚመጣው ጉዳትም ሁን ጥቅም ተጋሪ በመሆናችን ሂደቱን እንደግፋለን የሚል ሃሳብ ተንጸባርቋል” ነው ያሉት፡፡ አቶ ደስታ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤቱ አባላት አሁን የተፈረመው ስምምነት የቀጣይ ስራ ፍላጎት ማሳያ ብቻ መሆኑንና በቀጣይ መንግስት የኢትዮጵያን ጥቅም ማዕከል ባደረገ መልኩ በምንግስታዊ ስልጣኑ የሚያስተገብር ከሆነ አንቃወምም የሚል አቋም ነው የተያዘው ብለዋል፡፡ “በዚሁ አግባብ ነው ቤቱ የፍላጎት ማሳያውን እንደግፋለን የሚል መግለጫ እንዲሰጥ የወሰነው” ሲሉም በጉዳዩ ዙሪያ ምክር ቤቱ ደርሶበታል ያሉትን አቋም ያስረዱት፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች /ቤት ስለ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤቱ በዚሁ ተጠርቷል በተባለው ጠቅላላ ጉባኤው የተመለከተው ሌላው ጉዳይ ደግሞ የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን የስራ ሂደትና አሁን የደረሰበትን ደረጃ ነው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚናን አስመልክቶ ከሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ  በቀረበው ሪፓርትና ማብራሪያ ላይ ውይይት መደረጉን ያወሳው ምክር ቤቱ፤ በሂደቱ ሁሉም ፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲሳተፉ ጥሪ ቀርቦ፤ ለምክክር ኮሚሽኑ ተልዕኮ መሳካት ሁሉም አዎንታዊ ሚና እንዲጫወቱ፤ መንግስትም በበኩሉ ለምክክሩ እንቅፋት ሆኗል የተባለውን የሰላምና የጸጥታ ችግር እንዲቀረፍ መጠየቁ ነው የተገለጸው፡፡

ምክር ቤቱ ሰብሳቢ አቶ ደስታ “አገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ የተቻለውን ስራ እኛም እንደግፏለን በሚል በድምጽ ብልጫ ተወስኗል፡፡ ከዚያ በተጨማሪ ደግሞ ለውጥ ሊመጣ የሚችል ተቋም አይደለም በሚል የተቃወሙ ወደ 13 የፖለቲካ ድርጅቶችም አሉ፡፡ ይህ ምክር ቤት ከዚህ ጋር ተያይዞ ከኮሚሽኑ ጋር ለመስራት ከወሰኑ ጋር ነው የሚሰራው፡፡ በዚያው አግባብ ከኮሚሽነሩ ማብራሪያ ተሰጥቶ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምክር ቤቱም ድጋፉን ገልጾ ነው የተለያየነው” ብለዋል፡፡

የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ (ኦፌኮ)፣ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)፣ አረና ትግራይ፣ አፋር ህዝብ ፓርቲ እና ሌሎች ከ10 በላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ላይ እምነት የለንም በማለት የተቃዋሚ ፓርቲዎች ኮከስ ማቋቋማቸው ይታወሳል፡፡

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ገዢው ብልጽግና ፓርቲን ጨምሮ ከ57 በላይ የፖለቲካ ድርጅቶች አባላት ያሉት ሲሆን ትናንት ተከናውኗል በተባው የምክር ቤቱ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ 49 የፖለቲካ ድርጅቶች መሳተፋቸው ተነግሯል፡፡   

ሥዩም ጌቱ

አዜብ ታደሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ