ያለተጠያቂነት ዘላቂ ሰላም እንዴት?
እሑድ፣ ሚያዝያ 29 2015በፌደራል መንግስትና በትግራይ ሃይሎች መካከል በተካሄደ ጦርነት በግርድፉ ከአንድ ሚልዮን በላይ ዜጎችን ሕይወት እንደቀጠፈ ይነገራል። በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች መፈናቀላቸውን፤ ሴቶች ሕጻናት ጭምር መደፈራቸውን እንደ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ያሉ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተከራካሪዎች ባወጡት ሪፖርት አረጋግጠዋል።
በሁለቱም ሃይሎች መካከል በፕሪቶሪያ በተደረሰ ስምምነት መሰረት በትግራይ፣ በዓፋርና በአማራ ክልሎች አንጻራዊ ሰላም ተገኝቷል፤ በትግራይ የምግብና የመድሃኒት እርዳታ አቅርቦት ተጀምሮ ነበር። አሁን በስርቆት ምክንያት ለጊዜው ቢቆምም።የሁሉም ክልሎች ፕረዚዳንቶች ሰሞኑ በትግራይ ባካሄዱት ጉብኝንት በክልሉ ለደረሰው ከፍተኛ ውድመት መልሶ ግንባታና እርዳታ የሚውል የገንዘብ ድጋፍ አድርገዋል። ይሁንና ስለተፈጸመው የሰው ሕይወትና የንብረት ውድመት አንዳቸው ለሌላኛው የጸጸትና የይቅርታ ቃላት ሲለዋወጡ አልተደመጠም።
በጦርነቱ የደረሰውን የሰው ሕይወትና ንብረት ውድመት በሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ይታያል ቢባልም እስካሁን ብዙ ርቀት አልተጓዘም። የሽግግር ፍትህ ሂደቱ ራሱ በውድመቱ ቀጥተኛ ተሳታፊ ነበር ተብሎ በሚነገርለት በመንግስት የሚዋቀር መሆኑ ገለልተኝነቱ ላይ እና ዘላቂ ሰላምን የሚያመጣ ፍትሕ ስለማሰጠቱ ብዙዎች አብዝተው ይጠራጠራሉ።
በጦርነቱ የደረሰ የሰው ሕይወት መጥፋትናየንብረት መውደም በገለልተኛ አካል ተጣርቶ ለቀጣይ ትውልድም በሚያስተምር መልኩ በፍትሕ አደባባይ ካልተቐጨ የጦርነት ውድመት ታሪካችን አዙሪት ውስጥ መቀጠሉ አይቀርም በማለት የሰብአዊ መብት ተከራካሪዎች ይተቻሉ።
በዛሬው ውይይታችን ያለተጠያቂነት ዘላቂ ሰላም እንዴት? በሚል ርእስ ተወያዮችን ጋብዘናል።
ዮሐንስ ገብረእግዚአብሄር