1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ደመወዝ ያልተከፈላቸው የአማራ ክልል ሠራተኞች አቤቱታ

ረቡዕ፣ ኅዳር 25 2017

ሰሜን ጎጃም ዞን ሰሜን አቸፈር ወረዳ ይስማላ ከተማ መምህር እንደሆኑ የነገሩን ነዋሪ በአካባቢው የፋኖ ታጣቂዎች እንደሚንቀሳቀሱ ጠቁመው ደመወዝ ወቅቱን ጠብቆ ባይመጣም እንዳልተቋረጠባቸው ግን ተናግረዋል።ፋኖ በሚቆጣጠራቸው ቋሪትና ሰከላ በተባሉ ወረዳዎችም በተመሳሳይ የመንግሥት ሰራተኞች ደመወዝ እንደማይከፈላቸው ከስፍራው ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

https://p.dw.com/p/4njiq
የአማራ ክልል የትምህርት ቢሮ
የአማራ ክልል የትምህርት ቢሮ ምስል Alemenew Mekonnen/DW

ደመወዝ ያልተከፈላቸው የአማራ ክልል ሠራተኞች አቤቱታ

 

በአንዳንድ የአማራ ክልል አካባቢዎች ደመወዝ ከተከፈላቸው ወራት ማለፉን የመንግሥት ሠራተኞች ተናግረዋል። የክልሉ መምህራን ማህበር ደግሞ መምህራን ደመወዛቸው እንዲከፈል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተነጋገርኩ ነው ብሏል።በአማራ ክልል ከአንድ ዓመት በላይ ያስቆጠረው ጦርነት በክልሉ በርካታ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖዎችን እያስከተለ ነው። በአንዳንድ ወረዳዎች ደመወዝ ከወሰዱ ወራትን ማስቆጠራቸውን የመንግሥት ሠራተኞች እየገለፁ ነው።

ደሞዛቸዉን በፈረቃ የሚቀበሎት ዜጎች አቤቱታ

በክልሉ ምዕራብ ጎጃም ዞን የደጋዳሞት ወረዳ አንድ መምህር እንዳሉት ደመወዝ ከወሰዱ 3ኛ ወራቸውን አስቆጥረዋል፣ በዚህ የተነሳም ከነቤተሰቦቻቸው በችግር ላይ እንደሆኑ ነው ያስረዱት።

 

በኢኮኖሚ ቀውስ ወጣት ባለትዳሮች እስከ ፍቺ ደርሰዋል

ሌላ በወረዳው የሚገኙ አስተያየት ሰጪ ተመሳሳይ አስተያየት የሰጡ ሲሆን፣ በተፈጠረው የኢኮኖሚ ቀውስ ምክንያት ጋብቻቸውን እያፈረሱ ወደወላጆቻችው የተመለሱ ወጣቶች አሉ ብለዋል ።

አማራ ክልል የትምህርት ቢሮ
አማራ ክልል የትምህርት ቢሮምስል Alemenew Mekonnen/DW


በሰሜን ጎጃም ዞን ሰሜን አቸፈር ወረዳ በይስማላ ከተማ መምህር እንደሆኑ የነገሩን አስተያየት ሰጪ በበኩላቸው በአካባቢው የፋኖ ታጣቂዎች እንደሚንቀሳቀሱ ጠቁመው ደመወዝ ወቅቱን ጠብቆ እየመጣ ባይሆንም እንዳልተቋረጠባቸው ግን አመልክተዋል።

 ደሞዝ ለጠየቁ መሥፈራሪያ እና እሥር ለምን?

ፋኖ በሚቆጣጠራቸው ቋሪትና ሰከላ በተባሉ ወረዳዎችም በተመሳሳይ የመንግሥት ሰራተኞች ደመወዝ እንደማይከፈላቸው ከስፍራው ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

 

የወረዳው ሠራተኞች ደመወዝ ከወሰዱ ወራት ተቆጥረዋል

የደጋዳሞት ወረዳ አስተያየት ሰጪ እንደሚሉት ደግሞ በወረዳው መምህራን ብቻ ሳይሆኑ ሁሉም የመንግሥት ሠራተኞች ደመወዝ ከወሰዱ ወራት ተቆጥረዋል ብለዋል።በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ያልተፈታው የመምህራን የደሞዝ ጥያቄ
ጉዳዩን በተመለከተ አንድ የትምህርት ቢሮ የመምህራንን ጉዳይ የሚመለክት ኃላፊ ድምፃቸው እንዲቀረፅ ባይፈልጉም ክፍያንና በጀትን  በተመለከተ ወረዳዎችን ስለሚመለከት በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንደማይሰጡ ገልጠዋል።  የወርዳ ኃላፊዎችን ለማነጋግር ብንሞክርም ደመወዝ የማይከፈልባቸው አብዝኛዎቹ አካባቢዎች በፋኖ ታጣቂዎች የተያዙ በመሆኑ የመንግሥት መዋቅር ማግኘት አልተቻለም።

የአማራ ክልል መምህራን ማኅበር
የአማራ ክልል መምህራን ማኅበርምስል Alemenew Mekonnen/DW

በክልሉ በአሁኑ ጊዜ የ7 ወረዳ መምህራን ደመወዝ አልተከፈለም

የአማራ ክልል መምህራን ማህበር ሰብሳቢ አቶ ታጀበ አቻምየለህ፣ ደመወዝ የማይከፈላቸውን መምህራን ቁጠር መግለፅ ባይፈልጉም በክልሉ 7 ወረዳዎች አሁንም ደመወዝ የማይከፈላቸው መምህራን መኖራቸውን ተናግረዋል። ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር አሁን ደመወዝ ያልተከፈላቸው መምህራን እንዲከፈላቸው ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ እንደሆንም ገልጠዋል።
በምስራቅ አማራ ዞኖች 8 ወረዳዎች ተቋርጦ የነበረው የመምህራን ደመወዝ አሁን በመከፈል ላይ መሆኑን አቶ ታጀበ  ጠቅሰው፣ በምዕራብ አማራ ዞኖችም ደመወዝ ያልተከፈላቸው የ7 ወረዳዎች መምህራን ደመወዝ እንዲከፈል ሥራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል። በአማራ ክልል ከቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት እስከ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከ200ሺህ በላይ መምህራን እንደሚገኙም ከማህበሩ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

ዓለምነው መኮንን
ኂሩት መለሰ
አዜብ ታደሰ