1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዳግም የአንበጣ መንጋ ስጋት በምሥራቅ አፍሪቃ

ቅዳሜ፣ ግንቦት 8 2012

በምሥራቅ አፍሪቃ የአንበጣ መንጋን ለመቆጣጠር የሚደረገው ጥረት ቀጥሏል። ከመጋቢት እስከ ግንቦት የሚኖረው ቀላል የዝናብ ወቅት ከተራዘመ ደግሞ ምናልባት የተፈለፈለው አንበጣ አድጎ፣ በሰብልና በኗሪዎች ላይ ስጋት እንደሚያስከትል እየተነገረ ነው። ከኮቪድ 19 ወረርሽ ጋር ተዳምሮም በአካባቢው ላለው የምግብ እጥረት ሌላ ጫና እንደሚሆን ተገምቷል። 

https://p.dw.com/p/3cE7n
Heuschreckenplage in Indien
ምስል AFP/S. Panthaky

ዳግም የአንበጣ መንጋ ስጋት በምሥራቅ አፍሪቃ

ካለፈው ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት 2019 ጀምሮ በምሥራቅ አፍሪቃ የአንበጣ መንጋ በተደጋጋሚ እየታየ ነው። ባለፈው ሚያዝያ ወር የአንበጣው መንጋ ከ2 ሺህ ሄክታር በላይ አካባቢን ወርሮ ነበር። አሁንም በመጪው ሰኔ ወር አዲስ የተፈለፈለ የአንበጣ መንጋ ይህንኑ አካባቢ ዳግም ተጠናክሮ እንደሚወር ባለሙያዎች እየጠቆሙ ነው። የተራዘመው የዝናብ ወቅት በፈጠረላቸው አመቺ ሁኔታ በ18 ወራት ውስጥ መበራከታቸው የተነገረው አዲስ የተፈለፈሉ አንበጣዎች ከጥር ወር መጀመሪያ አንስቶ አዝመራውና እፀዋቱ ወደሚለመልምበት ወደ ምሥራቅ አፍሪቃ በብዛት እየመጡ እንደሆነም የባለሙያዎቹ ትንበያ ያሳያል። በአሁኑ ወቅት በአንበጣው መንጋ ክፉኛ የተጎዱት የአካባቢው ሃገራት ኢትዮጵያና ኬንያ ናቸው። በቀጣይ ወራትም በወቅቱ የአየር ጠባይ አመቺነት ሳቢያ አዲስ የአንበጣ መንጋ ኬንያ፣ ደቡብ ኢትዮጵያና ሶማሊያን እንደሚወር ይጠበቃል። በዓለም የምግብና የእርሻ ድርጅት FAO የአንበጣ ወረራ ትንበያ ከፍተኛ ባለሙያ ኬት ክሪስማን፣ ይህንኑ ይናገራሉ። « ቀጣዩ የአንበጣ መንጋ የሚከሰተው በሰኔ መጨረሻና በሐምሌ መጀመሪያ አካባቢ ይሆናል። ይህ ደግሞ በእርግጥ ሰብል ከመሰብሰቢያው ጊዜ ጋር ይገናኛል።» የበረሃ አንበጣው እጅግ ሰፊ አካባቢ ላይ ሲሰፍር ሰብልንም ሆነ ዛፎችን ሳይመርጥ ሁሉንም በመፍጀት ወና መሬት የሚያድቀር ነው። ይህም አርሶ አደሮችም ሆነ አርብቶ አደሮችን ለከፋ የምግብ እጥረት ያጋልጣል። የአንበጣው መንጋ ወረራ ባስከተለው ጉዳትም ከ25 ሚሊየን የሚበልጡ የምሥራቅ አፍሪቃ አካባቢ ነዋሪዎች፣ በያዝነው ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት የምግብ ዋስትና እንደማይኖራቸው FAO አመልክቷል። ኢትዮጵያ ውስጥ የመጀመሪያው የአንበጣ መንጋ ወረራ በተከሰተበት ወቅት አንዳንድ አርሶ አደሮች ከሰብላቸው 90 በመቶውን ማጣታቸውን ከደቡብ ወሎ የግብርና ሚኒስቴር አቶ ይመር ሰይድ ይናገራሉ። «በአንበጣ መንጋው አካባቢያቸው የተጎዳ አርሶአደሮችን ጎብኝቻለሁ፣ በቤታቸው ምግብ የለም፣ እንስሶቻቸውንም ሸጠዋል፣ ልጆቻቸው ሳይቀሩ ተሰደዋል።» በአንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ በበጎ ፈቃደኞች ትብብር ጭምር የአርሶ አደሩን ሰብል ከአንበጣው ለማተረፍ ርብርብ መደረጉንም ገልፀዋል። ቀደም ሲል በምሥራቅ አፍሪቃ የአንበጣ መንጋው ያደረሰው ጉዳት ሳያገግም በአካባቢው ከጥቅምት እስከ ታኅሣስ የተለመደው አጭር የዝናብ ወቅት ሳያቋርጥ እልፎ በመቀጠሉ አንበጣው እንዲበራከት እንቁላልም እንዲጥል ሁሜታዎችን ማመቻቸቱ ችግሩን እንደሚያባብስ FAO አሳስቧል። ይህ አዲስ የተፈለፈለ አንበጣ አድጎ መንጋ ሆኖ አካባቢውን ሳይወርና እንቁላል ሳይጥል በእንጭጩ ለማጥፋት መረባረብ እንደሚያስፈልግም ገልጿል። እንደኬንያ ያሉ ሃገራት የአንበጣ መንጋን በተመለከተ ያላቸው ልምድ በጣም አነስተኛ ነው። ሀገሪቱ በቅርቡ የገጠማትን የአንበጣ መንጋ ወረራ ለመከላከል የሚያስችል ሥርአት ለማደራጀት ጥቂት ወራት ወስዶባታል። ኃላፊዎቹ በአንበጣ በተወረረው በሺህዎች ሄክታር በሚገመተው አካባቢ ላይ ፀረ ተባይ መድኃኒት እንዲረጭ ዘመቻ አካሂደዋል። ሆኖም በመጪው ወራት የአየር ጠባዩ በዚሁ ይዞታ ከቀጠለ የአንበጣ መንጋው በብዙ እጅ እጥፍ ሊጨምር ስለሚችል የተደረገው በቂ አይመስልም። በዚህም ላይ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በምሥራቅ አፍሪቃ በአንበጣ መንጋ በተደጋጋሚ የተወረሩትን ሃገራት ማኅበረሰብ ሕይወት ይበልጥ አክብዶታል። ምንም እንኳ ኢትዮጵያ ዜጎቿን ሙሉ ለሙሉ ከቤት እንዳይወጡ ባታግድም፣ የሰዎች እንቅስቃሴ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መመሪያ ምክንያት ተገድቧል። እንዲያም ሆኖ አቶ ይመር ሰይድ እንደሚሉት የግብርና ባለሙያዎች የአንበጣ መንጋው የሚከማችበት ስፍራ ላይ የመቃኘት ሥራ ያከናውናሉ። ይህም ቢሆን አዲስ የአንበጣ መንጋ እየመጣ በመሆኑ ኢትዮጵያ በዚህ ረገድ እቅስቃሴዋን ማጠናከር እንደሚኖርባት በኢትዮጵያ  የFAO ተጠሪ ፋጡማ ሰይድ አፅንኦት ይሰጣሉ። ለዚህም በየቦታው በርከት ያሉ ቡድኖች፣ ለመንግሥት በርከት ያሉ ተሽከርካሪዎችና ተጨማሪ ፀረ ተባይ መድኃኒት በየቦታው እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። አሁን ያለው ፀረ ተባይ መድኃኒት እስከ ሰኔ ቢያደርስ እንደሆነም ጠቁመዋል። ጎረቤት ሶማሊያ ግን እስከ 2 ሺህ ሄክታር አካባቢን ሊያዳርስ የሚችል በቂ የመድኃኒት ክምችት እንዳላት፣ ይኽም ሐምሌ ድረስ የሚወጣውን ለጋ የአንበጣ መንጋ መቆጣጠር እንደሚያስችል የ FAO ሶማሊያ አስተባባሪ ተናገረዋል። 

FAO, Food and Agriculture Organisation of the United Nations, Logo
ምስል AP Graphics
Data visualization risk level locusts

ሸዋዬ ለገሠ/ኪራ ሻክት

አዜብ ታደሰ