"ድምጽ የሌለው ሞት እየሞትን ነው" ከባድመ የተፈናቀሉ የልጆች እናት
ሐሙስ፣ ግንቦት 24 2015የሁለት ዓመቱ ደም አፋሳሽ ጦርነት ያስቆመ የፕሪቶርያ የሰላም ስምምነት ከተፈረመ ሰባት ወራት ቢሆንም፥ በጦርነቱ ምክንያት ከቀዬአቸው የተፈናቀሉ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች አሁንም ወደ መኖርያቸው አለመመለሳቸው የተወሳሰቡ ማሕበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች አሁንም እንዲቀጥሉ አድርጎ ይገኛል። በትግራይ አንድ ሚልዮን የሚገመቱ ተፈናቃዮች አሁንም በመጠልያዎች እና የተለያዩ ስፍራዎች ተበትነው እንደሚገኙ የክልሉ አስተዳደር ቁጥራዊ መረጃዎች ያመለክታሉ። እነዚህ የጦርነቱ ተፈናቃዮች፣ ከጦርነቱ መቋረጥ በኋላ እንኳን ወደ ቀዬአቸው አለመመለሳቸው እንዲሁም ይቀርብላቸው የነበረ ሰብአዊ እርዳታ መቋረጡ ተከትሎ ለከፋ ችግር ተጋልጠው እንዳለ ያስረዳሉ።
ዶቼቬሌ ያነጋገራቸው በሽረ ከተማ ጉና የተፈናቃዮች መጠልያ ጣብያ ያሉ አቶ ገብረማርያም ገብረሚካኤል የተባሉ ከምዕራብ ትግራይ ፀገዴ አካባቢ በ2013 ዓመተምህረት የተፈናቀሉ አዛውንት፥ አራት ልጆቻቸው ጨምሮ ከፊል ቤተሰቦቸው ጦርነቱ ሲጀምር ወደ ሱዳን መሰደዳቸው፣ እርሳቸው ከነባለቤታቸው ግን ወደ ሽረ ከተማ መግባታቸው የሚያነሱ ሲሆን፥ ያለፉት ሶስት ዓመታት አስቸጋሪ ሕይወት እየመሩ ስለመሆኑ ይገልፃሉ።
ከሰላም ስምምነቱ በኃላ ጦርነቱ መቆሙ ተከትሎ ወደ ቀድሞ ቀዬአቸው ሊመለሱ፣ ከልጆቻቸው ጋር ሊገናኙ ተስፋ ሰንቀው እንደነበር የሚያወሱት ተፈናቃዮ አቶ ገብረማርያም፣ ይሁንና የሰላም ስምምነቱ ከተፈረመ ሰባት ወራት ቢሆኑም በርሳቸው ዘንድ የተለወጠ ነገር አለመታየቱ አሳዝኗቸዋል።
ሌላዋ በመቐለ አፄ ዮሃንስ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ቅጥር ግቢ ከሌሎች እንደርሷ ተፈናቃዮች ጋር መኖር ከጀመረች ረዥም ግዜ እንዳለፋት የምትገልፀው ያነጋገርናት የሁለት ልጆች እናት ትርሓስ አባዲ፣ ከቀድሞ መኖርያዋ ባድመ ጦርነቱ ሸሽታ የወጣችው በግጭቱ ጅማሮ ሰሞን እንደነበረ ታስታውሳለች። አሁን ትርሓስና አብረዋት ያሉ ሌሎች በርካታ የሰሜን ምዕራብ ዞን ተፈናቃዮች ላለፉት ስምንት ወራት እርዳታ ሳያገኙ በከፋ ሕይወት ላይ እንደሚገኙ ትገልፃለች።
በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ በትግራይ የተለያዩ ከተሞች የሚገኙ ተፈናቃዮች፣ መንግስት ወደ ቀዬአቸው እንዲመልሳቸው የሚጠይቅ ሰልፍ ባለፈው ሳምንት አካሂደው ነበር። ተፈናቃዮቹ በሰላም ስምምነቱ መሰረት አካባቢቸው ድህንነቱ ተረጋግጦ ወደ ቀዬአቸው ሊመለሱ፣ የተቋረጠ ሰብአዊ እርዳታ እንዲቀርብላቸው ይጠብቃሉ።
"በመጀመርያ ደረጃ እርዳታ ልናገኝ ይገባል፣ ቀጥሎም ወደ ቀዬአችን የምንመለስበት ሁኔታ መመቻቸት ይገባል" የሚሉት ከተፈናቃዮች መካከል የሆኑት ያነጋገርናቸው ቄስ ዘርአብሩክ ተክለማርያም፥ የእርዳታ አቅርቦት በአጭበርባሪዎች ምክንያት መቋረጡ የአብዝሃው ተፈናቃይ ሕይወት ለአደጋ አጋልጦ እንዳለ ገልፀውልናል። እንደ ቄስ ዘርአብሩክ ገለፃ ክረምቱ ከመድረሱ በፊት በአጭር ግዜ ወደ አካባቢያቸው የማይመለሱ ከሆነ ማሕበራዊ ችግሩ ካለው ወደ ከፋ ሁኔታ ሊሸጋገር ይችላል።
የተፈናቃዮች ጉዳይ አንድ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር እየፈተነ ያለ አጀንዳ ሆኖ እንዳለ ብዙሃን ይገልፃሉ። የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ከፍተኛ ባለስልጣን የሆኑት አቶ አማኑኤል አሰፋ ከተፈናቃይ ተወካዮች ጋር ባደረጉት ውይይት ግዚያዊ አስተዳደሩ በጦርነቱ ምክንያት ከቀዬአቸው የተፈናቀሉትን ወደ ቦታቸው የመመለስ ጉዳይ ቀዳሚ አጀንዳው አድርጎ እየሰራ ስለመሆኑ ገልፀዋል። "የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ዋነኛ ስራው ይህ ነው። ሌላው የሌላ ግዜ ስራ ነው" የሚሉት አቶ አማኑኤል አሰፋ ችግሩ ለመፍታት የክልሉ አስተዳደር ከፌዴራሉ መንግስት ጋር እየሰራ ስለመሆኑ ጠቁመዋል።
ሚሊዮን ኃይለስላሴ
እሸቴ በቀለ
ማንተጋፍቶት ስለሺ