1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ፖለቲካሰሜን አሜሪካ

"ትራምፕን ፕሬዚዳንት ከመሆን የሚያግዳቸው የለም" ስለመባሉ

ዓርብ፣ የካቲት 1 2016

የቀድሞው ፕሬዚዳንት፣ በኮሎራዶና ዋና ዋና ግዛቶች በሚካሄዱ ቅድመ ምርጫዎች እንዳይሳተፉ መታገዳቸውን ተከትሎ ከዚህ ቀደም ለሀገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ አስገብተዋል። ፍርድ ቤቱም፣ ዶናልድ ትራምፕ በድጋሚ ለፕሬዚዳንትነት ብቁ ስለመሆናቸው ወይም አለመሆናቸው ውሳኔ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።

https://p.dw.com/p/4cED1
የቀድሞው የአሜሪካ ፕረዚደንት ዶናልድ ትራምፕ
የቀድሞው የአሜሪካ ፕረዚደንት ዶናልድ ትራምፕምስል Eduardo Munoz/REUTERS

ትራምፕ ያለመከሰስ መብት የላቸውም

ዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ ባለፈው ማክሰኞ ያስቻለው የፌዴራል ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ውሳኔ አሳልፏል። ፍርድ ቤት፣ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ከክስ ነፃ ነኝ በማለት የሚያሰሙትን የይገባኛል ጥያቄ  ውድቅ አድርጎታል። በመሆኑም፣ ትራምፕ ፣ በ2020 ከአሁኑ ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ባይደን ጋር በተፎካከሩበት ምርጫ፣ ውጤቱን ለመቀልበስ አሲረዋል የሚል ክስ ሊመሰረተባቸው ይችላል። በቨርጂኒያ ግዛት የሕግ ባለሙያ የሆኑት ዶክተር ፍጹም አቻምየለህ እንደሚሉት፣ በፌዴራል ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ መሠረትበቀድሞ ፕሬዚዳንት ላይ የቀረበው ክስይቀጥላል።
«ስለዚህ ከሱ ይቀጥላል ማለት ነው። እና የእማኝ ዳኞች ፊት የሚደረገው ክስ ለጊዜው በይርጋ ቆሞ ነበር አሁን ይቀጥላል ማለት ነው። በርግጥ፣ትራምፕ፣ ይህንን ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ይግባኝ ማለቱ አይቀርም።ግን ይሄኛው የዋሽንግተን ዲሲው ክስ ይቀጥላል።»
ዳኞች  ባሳለፉት ውሳኔ መሠረት፣ ለዚህ ክስ አላማ የቀድሞው ፕሬዚዳንት የሌላ ማንኛውም የወንጀል ተከሳሽ መከላከያዎችን በመያዝ ዜጋ ሆነዋል።


ትራምፕ ያለመከሰስ መብት የላቸውም

በፕሬዚዳንትነት ሲያገለግሉ ሊጠብቃቸው የሚችል ማንኛውም ያለመከሰስ መብት፣ ከዚህ ክስ ሊጠብቃቸው አይችልም ነው የተባለው። ትራምፕ በበኩላቸው፣ ከክስ ነጻ ነኝ ሲሉ ይሞግታሉ። ውሳኔው ከተላለፈ በኋላ ትራምፕ «ትሩዝ ሶሻል» በተባለው የራሳቸው ማኀበራዊ መገናኛ ላይ ባጋሩት ጽሑፍ፣ «አንድ ፕሬዚዳንት በተገቢው መንገድ ለመሥራትና ለሀገራችን ጥቅም መደረግ ያለበትን ለማድረግ ሙሉ ያለመከሰስ መብት ሊኖረው ይገባል» ብለዋል። ቃል አቀባያቸውም ትራምፕ፣ ፕሬዚዳንቱንና ሕገ መንግሥቱን ለመጠበቅ ብይኑን ይግባኝ እንደሚሉ አረጋግጠዋል።

ትራምፕ፣ በአሜሪካ ዘንድሮ በሚካሄደው ፕሬዝደንታዊ ምርጫ፣ የሪፐብሊክ ፓርቲው ግንባር ቀደም ተወዳዳሪ በመሆን ብቸኛ ተፎካራቸው የሆኑትን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቀድሞ አምባሳደር ኒኪ ሄሊን እየመሩ ይገኛሉ። የሪፐብሊካን ፓርቲውን ፉክክር አሸንፈው፣ ለዋናው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ከጆሴፍ ባይደን ጋር ለምርጫ እንደሚቀርቡ ሰፊ ግምት አለ። ይሁንና ትራምፕ በርከት ያሉ የወንጀል እና የፍትሐብሔር ክሶች እየቀረቡባቸው ይገኛል።

ዶናልድ ትራፕ ፍርድ ቤት ሲደርሱ
ዶናልድ ትራፕ ፍርድ ቤት ሲደርሱምስል ANGELA WEISS/AFP

"ትራምፕን ፕሬዚዳንት ከመሆን የሚያግዳቸው የለም" ስለመባሉ

 ዶናልድ ትራምፕ የሚቀርቡባቸው ክሶች ቀጣይ የምርጫ እንቅስቃሴዎች ላይ የሚያስከትሉት ተጽዕኖ ይኖር ይሆን ስንል የሕግ ባለሙያው ዶክተር ፍጹምን ጠየቅን። ዶክተር ፍፁም፣ «በአሜሪካ ሕግ መሰረት አንድ ሰው በወንጀል ጥፋተኛም ቢሆን ፕሬዝደንት ከመሆን ምንም ሊያግደው አይችልም። ችግሩ ቴክኒካሊ እስር ቤት ከገባ እስር ቤት ሆኖ እንዴት አድርጎ ነው ፕሬዝደንት የሚሆነው እንጂ በአሜሪካ ሕግ መሰረት በወንጀል ጥፋተኛ መባል በራሱ አንድን ሰው ለፕሬዚዳንትነት ምርጫ እንዳይወዳደር አያደርገውም።» ነው የሚሉት። 
የትራምፕ የሕግ ቡድን አባላት ይግባኝ እንደሚሉ በመግለጻቸው ጉዳዩን ገና በሳምንታት ወይም በወራት ሊያራዝመው ይችላል ተብሏል። ይህ የሚሆነው ግን ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩ ተቀብሎ ለማየት ከተስማማ ነው።


ለጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የቀረበው ይግባኝ

የቀድሞው ፕሬዚዳንት፣ በኮሎራዶና ዋና ዋና ግዛቶች በሚካሄዱ ቅድመ ምርጫዎች እንዳይሳተፉ መታገዳቸውን ተከትሎ ከዚህ ቀደም ለሀገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ አስገብተዋል። ፍርድ ቤቱም፣ ዶናልድ ትራምፕ በድጋሚ ለፕሬዚዳንትነት ብቁ ስለመሆናቸው ወይም አለመሆናቸው ውሳኔ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል። የዶናልድ ትራምፕ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ቀጠሮ ገና በቀጠሮ ላይ ነው።


ታሪኩ ኃይሉ 
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሔር
ሽዋዬ ለገሰ