ጀርመን እስራኤልና ኢራን
ዓርብ፣ መጋቢት 14 2004
የኢራንን የኑክሌር መርሐ-ግብር በጦር ሐይል ድብደባ ለማስቆም መሞከር ለአካባቢዉም፥ለመላዉ ዓለምም ሠላም አደገኛ ሊሆን እንደሚችል የጀርመኑ መከላከያ ሚንስትር አስጠነቀቁ።የጀርመን መከላከያ ሚንስትር ቶማስ ደ ሚዚየር ትናንት በርሊን ዉስጥ ከእስራኤሉ አቻቸዉ ከኤሁድ ባራክ ጋር ከተናጋገሩ በሕዋላ እንዳሉት ጀርመን ምንጊዜም ከእስራኤል ጎን ትቆማለች።መንግሥታቸዉ ዘመናይ ባሕር ሰርጓጅ ጀልባዎች ለእስራኤል ለመሸጥ መወሰኑንም መከላከያ ሚንስትሩ አረጋግጠዋል። ይሁንና የእስራኤል ባለሥልጣናት በተደጋጋሚ እደዛቱት የሐገራቸዉ ጦር የኢራንን የኑክሌር ተቋማት ከደበደበ መዘዙ እስራኤልን ጭምሮ ሁሉንም የሚጎዳ ነዉ-የሚሆን።ነጋሽ መሐመድ ዝር ዝር ዘገባ አለዉ።
የሁለቱ ሚንስትሮች ፈገግታ፥ አንዱ ሌላዉን ለማመስገን፥ ለማድነቅ ማወደስ የተጠቀሙባቸዉ ቃላት፥ ሚንስትሮቹ ሁለት ሰዓት ከተወያዩበት አዳራሽ ሲወጡ-ያዩ የሰሟቸዉ እንደዘገቡት፥የወዳጅነታቸዉን ፅናት ገላጮች ነበሩ።«ታላቅ ወታደር ነበር» አሉ የጀርመኑ መከላከያ ሚንስትር ቶማስ ደ ሚዜየር ከጎናቸዉ ወደቆሙት ወደ እስራኤሉ አቻ-እንግዳቸዉ ኤሁድ ባራክ እያመለከቱ፥ አሁን ደግሞ «ብልሕ ፖለቲከኛ ናቸዉ»
የባራክ አፀፋም ተመጣጣኝ ግን በርሊን ድረስ ወደተጓዙበት ዋና ጉዳይ በቀጥታ የገባ ነበር።የአዉሮጳ ሕብረት በኢራን ላይ የነዳጅ ግዢ ማዕቀብ እንዲጥል ጀርመን ለተጫወተችዉ ቁልፍ ሚን እናመሰግናለን የሚል።
የኢራን ጉዳይ በቀጥታ ተነሳ።እና ፈገግታ፥ ሙገሳ፥ ምስገናዉ ፔተር ሽቱትስል እንደዘገበዉ አብቅቶ ሚንስትሮቹ ከቁም ነገሩ-ጥልቅ፥ ልዩነቶቻቸዉ ደግሞ ብቅ አሉ።ደ ሚዚየር።
«ወቅቱ የሚጠይቀዉ ቆጥቋጭ ማዕቀብና ጠንካራ ድርድር ነዉ።የእስራኤልን የመንግሥትነት ሕልዉናን (ማስከበርን) በተመለከተ በኛ ፅኑ ትብብር እስራኤል እርግጠኛ መሆን ትችለች።ለዚሕ የጀርመንዋ መራሒተ-መንግሥት ቃል (ጥሩ) ማረጋገጪያ ነዉ።ከእስራኤልም ሆነ ከሌሎቹ ወዳጆቻችን የሚጠበቀዉ ጠቃሚ ጉዳይ የመካከለኛዉ ምሥራቅ ግጭትን ለማስወገድ አበክሮ መጣር ነዉ።»
እርግጥ ነዉ የአዉሮጳ ሕብረት በቅርቡ በኢራን ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ መጣሉን የእስራኤሉ መከላከያ ሚንስትር እንደ ጥሩ እርምጃ ነዉ-ያዩት።ማዕቀቡ እንዲጣል ጀርመን ላደረገችዉ አስተዋፅኦም አስተናጋጃቸዉን በይፋ ትናንትናዉኑ አመስግነዋል።ግን በተቃራኒዉ ድርድሩም ሆነ ማዕቀቡ ዉጤት አያመጣም ባይ ናቸዉ።
«የኢራን መሪዎች በሐገራቸዉ ላይ በተጣለዉ ማዕቀብ ተገድደዉ የኑክሌር መርሐ-ግብራቸዉን ማቆማቸዉን፥ እንዲያዉ አንድ ጠዋት ከእንቅልፋችን ስንነቃ ብንሰማ እንወድ ነበር።እንዳለመታደል ሆኖ ይሕ እንደማይሆን ለመገመትና ለሌላ አማራጭ ለመዘጋጀት፥ በተጨባጩ እዉነት የምናምን ነን።በእድሜም የበለሰልን።»
ሌላዉ አማራጭ ስዉር አይደለም። የኢራንን ተጠርጣሪ የኑክሌር ተቋማት መደብደብ።ያም ሆኖ ኤሁድ ባራክ እንደ ቀድሞ ጄኔራልነታቸዉ ወታደራዊዉን እርምጃ በርሊን ላይ በግልፅ አልተናገሩትም።እንደ ፖለቲከኛ በግድምድሞሽ ቋንቋ «ሁሉም» አሉት።
«ኢራን የኑክሌር ጦር መሳሪያ ከመታጠቅ ልትገታ እንደሚገባት እናምናለን።ሁሉም አማራጮች ጠረጳዛ ላይ እንዲቀመጥም እንሻለን።ሁሉንም አማራጭ ስል፥ ሁሉንም አማራጭ እንጂ ባለበት መግታትን ማለቴ አይደለም።ኑክሌር የታጠቀች ኢራንን ማመን የማይቻል፥እና መላዉ አለም የማይቀበለዉ ነዉ ብዬም አምናለሁ።»
የጀርመኑ መከላከያ ሚንስትር እንዳሉት ግን ከድርድር-ማዕቀቡ ባለፍ ያለዉ አማራጭ በተለይ ወታደራዊ እርምጃዉ ቢያንስ ላሁኑ ተቀባይነት የለዉም።የጦር ምርጃዉ መዘዝም ደ-ሚዜር እንደሚያምኑት ማስላት አይቻልም።
«ሁሉም ወገኖች ከቃላት እንኪያ ሠላንቲያ፥ ከወታደራዊ ፍጥጫ እንዲታቀቡ እጠይቃለሁ። እኔ እንደማምነዉ የወታደራዊ ግጭት ከተከሰተ በእስራኤል፥ በአካባቢዉም በሌሎች ላይ የሚያደርሰዉ አደጋ እና በእስራኤል ላይ የሚያስከትለዉ ጥፋትም ሊገመት አይቻልም።»
ያም ሆኖ ጀርመን ለእስኤል ስድስት ዘመናይ ባሕር ሰርጓጅ የጦር ጀልባዎች ለመሸጥ መስማማቷን መከላከያ ሚንስትር ደሚዚየር አስታዉቀዋል።እስራኤል ኢራንን መሰል ጠላቶቿን ለማጥቃት ይጠቅማሉ የሚባሉትን ጀልባዎች ገሚስ ወጪ የምትችለዉ ጀርመን ናት።
ኢንተርናሲዮናለ ፖለቲክ የተሰኘዉ የጀርመን መፅሔት አዘጋጅ ዚልከ ቴምፕለ እንደሚሉት ጀርመን ባንድ በኩል እስራኤልን እያስታጠቀች፥ በሌላ በኩል እስራኤል ወታደራዊ እርምጃ እንዳትወሰድ እያሳሰበች የሰላም ሚዛንን ለማስጠበቅ እየጣረች ነዉ።
«(ለእስራኤል) የሚሰጠዉ ድጋፍ ኢራን የኑክሌር ቦምብ እንዳታመርት ወይም የጀመረችዉን እንዳትጨርስ ለማገድ ማዕቀብን ጨምሮ የሚቻለዉን ሁሉ ለማድረግ መጣርን የሚያመለክት ነዉ።የዚያኑ ያክል እስራኤል ወታደራዊ እርምጃ ብትወስድ ብዙ አደጋ እንዳለዉ ለእስራኤል ማስገንዘብ ነዉ።»
ነጋሽ መሐመድ
ሒሩት መለሰ