“ገበታ ለወገኔ” በስዊዘርላን የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያን ተሳትፎ
ሐሙስ፣ ሚያዝያ 26 2015«ኢትዮጵያ ዉስጥ በተከሰተዉ ጦርነቱ በጣም ብዙ ትምህርት ቤቶች ናቸዉ የፈረሱት። አሁን ደግሞ ትግራይ ዉስጥ የፈረሱትን ትምህርት ቤት አጠቃለን ስናያቸዉ በጣም ብዙ ትምህርት ቤቶች ናቸዉ ከጥቅም ዉጭ የሆኑት። በሰሜን ሸዋ እና አፋር አካባቢ የፈረሱትን ትምህርት ቤቶች አይተናል። በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ዉስጥ በዚህ ጦርነት የደረሰዉ ኪሳራ፤ የደረሰዉ መፈናቀል፤ የደረሰዉ ዉድመት በጣም ከፍተኛ ስለሆነ በቀላሉ የሚጠገን አይደለም። መንግሥት እራሱ ይህን መልሶ ለማቋቋም የሚያደርገዉ ነገር አለ። እንደ ኢትዮጵያዉያን ይህን ኪሳራ ቁጭ ብለን ማየት አንችልም። ይህ እኛ የምናደርገዉ ነገር ግን በማህበር ተሰባስበን የምንሰራዉ ነዉ። እኛን ይመለከተናል የኛ ጉዳይ ነዉ ብለን ነዉ የተነሳነዉ።»
በስዊዘርላንድ ኢትዮጵያዉያን እና ትዉልደ ኢትዮጵያዉያን የተሰባሰቡበት “ገበታ ለወገኔ” የተሰኘዉ የበጎ አድራጎት ድርጅት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ኃይሉ ኡርጌሳ ከተናገሩት የተወሰደ ነዉ። በስዊዘርላንድ ኢትዮጵያዉያን እና ትዉልደ ኢትዮጵያዉያንን ያሰባሰበዉ “ገበታ ለወገኔ” የተባለዉ በጎ አድራጎት ድርጅት፤ ስለ ኢትዮጵያ ያገባናል፤ ኃላፊነትም አለብን በሚል መርህ በኢትዮጵያ የተለያዩ ድጋፎችን ማድረግ ከጀመረ ዓመታትን አስቆጥሯል።
“ገበታ ለወገኔ” ሰሞኑን፤ ታዋቂዉን የዜማ እና ግጥም ደራሲ ብሎም አቀንቃኝ ንዋይ ደበበን እንዲሁም አርቲስት ሃመልማል አባተን ጄኔቫ ላይ ጋብዞ የተዋጣለት የገቢ ማሰባሰቢያ የሙዚቃ መድረክ አዘጋጅቶ ለበጎ አድራጎት የሚዉል ገንዘብን አሰባስቧል። “ገበታ ለወገኔ” በስዊዘርላንድ የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያንን እና ትዉልደ ኢትዮጵያዉያንን ሁሉ ያቀፈ ማህበር ነዉ ያሉን የድርጅቱ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ኃይሉ ኡርጌሳ፤ ድርጅታችን “ገበታ ለወገኔ” በሰሜን ኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች በጦርነት ጉዳት የደረሰባቸውን ትምህርት ቤቶች መልሶ ለመገንባት እቅድ ነድፎ መንቀሳቀስ መጀመሩን ነግረዉናል። አቶ ኃይሉ ኡርጌሳ ስለ በጎ አድራጎት ድርጅቱ እንዲነግሩን ከዶቼ ቬለ ለቃለ መጠይቅ በግብዣችን መሰረት ሲቀርቡ “ገበታ ለወገኔ” ማለት ግን ማለት ነዉ ስንል ነበር ቃለ ምልልስቻንን የጀመርነዉ።
«ይህን የበጎ አድራጎት ስራ ስንጀምር መጀመርያ ያዘጋጀነዉ የማህበርተኛዉን ማሰባሰብያ አይነት የእራት ግብዣ አድርገን ነበር። ሰዎች ይህን የእራት ግብዣ ከፍለዉ በመግባት እና በመመገብ ገንዘብ በማሰባሰብ ገበታ ዘርግተን እንዲሳተፉ አደረግን። ለዝያ ነዉ ከዚህ ዝግጅት ተነስተን ነዉ “ገበታ ለወገኔ” ብለን የሰየምነዉ። ከዚህ የምግብ ሽያጭ የተገኘዉን ገቢ ለወገኖቻችን በተለይም ኢትዮጵያ ዉስጥ በጦርነት ሳብያ ከትምህርት ዉጭ ለሆኑ ህጻናት “ገበታ ለወገኔ” ብለን እርዳታ ለማቅረብ ያሰብነዉ ነዉ። ከዚህ በፊት የተሰባሰብነት የማህበር ስም ዘመቻ ለወገን ህልዉና የሚል ነበር።»
በተለያዩ የዉጭ ሃገራት ኢትዮጵያዉያን በተለያየ ሁኔታ እና አጋጣሚ ይሰባሰባሉ፤ ሃሳብ ይለዋወጣሉ፤ ቤተሰቦቻቸዉን የትዉልድ አካባቢያቸዉን ብሎም ሃገራቸዉን ይረዳሉ። በስዊዘርላንድ የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያንም በሌሎች ሃገራት እንደሚገኙ ኢትዮጵያዉያን ሁሉ በሃገራቸዉ ጉዳይ ላይ ንቁ ተሳትፎ ያደርጋሉ። የገበታ ለወገኔ ማኅበር የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኃይሉ ኡርጌሳ እንደነገሩን፤ በስዊዘርላንድ የሚገኙ ኢትዮጵያዉያን መሰባሰብ ከጀመሩ 30 እና 40 ዓመታት በላይ ሆናቸዋል። ይሁንና ኢትዮጵያዉያን ስለ ሃገሪ ያገባኛል ብለዉ በንቁ መሰባሰብ የጀመሩት የታላቁ ህዳሴ የዓባይ ጉዳይ ሲነሳ ነዉ ሲሉ አቶ ኃይሉ ተናግረዋል።
«በተለይ ኢትዮጵያ ዉስጥ ለዉጡ ከመጣ በኋላ በስዊዘርላንድ ዉስጥ ኢትዮጵያዉያንን ያሰባሰበዉ፤ ኢትዮጵያ ላይ በተቀናበበረ መልኩ በምዕራባዉያን ዘመቻ በተከፈተበት ወቅት ነዉ። በተለይም ግብጽ የኢትዮጵያን የዓባይ ተጠቃሚነት በፀጥታዉ ምክር ቤት ጭምር ለማዘጋት በተንቀሳቀሰችበት ወቅት ነበር። በግብፅ አነሳሽነት በአየርላንድ በኩል በሚነሱ ጥያቄዎች ወዘተ ኢትዮጵያ ተወጥራ የተያዘችበት ወቅት ነበር። የአሜሪካዉ ፕሬዚዳንት የነበሩት በዶናል ትራምፕ ጭምር ግብፅ ግድቡን ማፈንዳት ትችላለች ብለዉ ኃላፊነት የጎደለዉ መግለጫ በሚሰጡበት ወቅት ኢትዮጵያዉያን ተቆጥተዉ የሚንቀሳቀሱበት ወቅት ነዉ እንቅስቃሴያችንን በቁጣ የጀመርነዉ። የ“ኖ ሞር“ እንቅስቃሴም በዚህ ጊዜ ነበር የተወለደዉ። እና በዝያን ወቅት በስዊርላንድ የምንገኝ ኢትዮጵያዉያን እና ትዉልደ ኢትዮጵያዉያን የሃገራችንን ህልዉና የሚፈታተን እንቅስቃሴዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ሲካሄዱ “ዘመቻ ለሃገር ህልዉና“ በሚል ተሰባስበን ምዕራባዉያን በኢትዮጵያዉያን ላይ የሚሚያሳድሩትን ጫና በመቃወም ለመንግሥታቱ ድርጅት አቤቱታችንን በማስገባት፤ በጄኔቫ በተመድ ጽ/ቤት ፊት ለፊት ተቃዉሞዋቸንን በማሰማት ሰላማዊ ሰልፍ በማካሄድ በዚህ አይነት መልኩ በተለያዩ መስኮች ከተለያዩ ቡድኖች ጋር በመቀናጀት “ዘመቻ ለሃገር ህልዉና“ በሚል መልኩ ነበር የመጀመርያዉን እቅስቃሴያችንን የጀመርነዉ። ከዚህ እንቅስቃሴ በኋላ ሃገር ወደ ጦርነት በገባችበት ወቅት የዉጭ ኃይላት በጦርነት ዉስጥ እጃቸዉን አስገብተዉ በተዳፈሩበት ወቅት እንቅስቃሴያችንን ቀጥለናል። ይህን እንቅስቃሴ ያደረግን የዲያስፖራዉ አባላት ከጦርነቱ በኋላ ወደ ሃገር ቤት በመግባት በጦርነቱ የወደሙ አካባቢዎችን ጎብኝተናል። በተለይም በሰሜን ሸዋ እና በአፋር አካባቢዎች የደረሱትን ዉድመቶች አይተናል። የወደሙ ትምህርት ቤቶችን ሆስፒታሎችን ወዘተ አይተናል። ህጻናት ትምህርት ቤት ወድሞባቸዉ ሜዳ ላይ ዛፍ ስር ሆነዉ፤ ታንክ ስር ተቀምጠዉ ፤ በጥይት ቀልሃ ሲጫወቱ አይተናል። በጣም ዘግናኝ ትዕይንት ነበር። ህጻናቱ ወደ ትምህርት ቤት መመለስ አለባቸዉ። በታንክ ስር መጫወት የለባቸዉም፤ የተቻለንን እናድርግ ብለን ወሰንን። ከዝያ በኋላ ነዉ በስዊዘርላንድ የሚገኙ ኢትዮጵያዉያን “ገበታ ለወገኔ” በሚል ጥላ ስር ሆነን የተለያዩ ዝግጅቶችን በማካሄድ እና ገንዘብ በማሰባሰብ ለህጻናቱ ትምህርት ቤት ለመስራት የፈረሱትን ለመጠገን እቅድ ይዘን ወደዚህ ዘመቻ የገባነዉ። ይህንን ደግሞ ደጋግ ኢትዮጵያዉያን ተሰባስበዉ እየሰሩ ገንዘብ እያሰባሰቡ ነዉ።»
አቶ ኃይሉ በወቅቱ ኢትዮጵያ ዉስጥ የሚታየዉ የፖለቲካ ትኩሳት አለመረጋጋትም አለ ይባላል እና ምናልባት ያሰባሰባችሁት ገንዘብ የታለመለት ቦታ አይደርስም ብላችሁ አትሰጉም?
«ገንዘቡን እና እራሳችን ከአካባቢዉ ሰዎች ጋር በመተባበር የምንሰራዉ ነዉ። ይሁንና መንግሥት የሚያስተዳድረዉ ቦታ ስለሆነ መንግሥት ለስራችን መሳካት የሚያስፈልገንን ጉዳዮች ያሟላልናል። ከመንግሥት ጋር እንደ ዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፤ ትምህርት ሚኒስቴር፤ የዲያስፖራዉ ክፍል፤ ብሎም የአካባቢ የመንግሥት ተጠሪዎች የሚያስፈልጉንን ጉዳዮች ያሟሉልናል። በቀጥታ ወደ መንግስት ካዝና የሚገባ ገንዘብ ግን የለም። ገንዘቡን ወጭዉን የምንቆጣጠረዉ እኛዉ ነን። በአንድ ጊዜ ገንብተን የምንጨርሰዉ የምንሰራዉ ስራ ግን የለም። ሁሉም የሚሆነዉ በሂደት ነዉ።»
ነጻነት ጌታቸዉ የ“ገበታ ለወገኔ” ኢትዮጵያዉያን እና ትዉልደ ኢትዮጵያዉያን የተሰባሰቡበት በጎ አድራጎት ድርጅት ሊቀመንበር ናቸዉ። ባለፈዉ ሳምንት መጨረሻ ገበታ ለወገኔ በኢትዮጵያ በጦርነት ለተጎዱ ትምህርት ቤቶችን ለማደስ ያዘጋጀዉ የሙዚቃ መድረክ እና የእራት ሥነ-ስርአት የተዋጣለት እንደነበር በማህበሩ የሚገኙት ሴቶች ከፍተኛ ስራ እየሰሩ መሆኑንም ተናግረዋል። የበጎ አድራጎት ድርጅቱ ሊቀመንበር ነጻነት ጌታቸዉ በዚህ አጋጣሚ ማህበሩን የማያዉቁ ካሉ ወደ ገበታ ለወገኔ ብለዉ እንዲመጡ ጥሪ አቅርበዋል።
የገበታ ለወገኔ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊዉ አቶ ኃይሉ ኡርጌሳም ኢትዮጵያ ካለኛ ካለልጆችዋ ማንም የላትም ሲሉ መልክት አስተላልፈዋል።
« ኢትዮጵያ ካለእኛ ካልጆችዋ ማንም የላትም። ቀዳማዊ ኃላፊነት ተሰምቶን ለሃገራችንን ለኢትዮጵያ ለህዝባችን በተለይ ጦርነት ላደቀቀዉ ህዝብ መድረስ ከማንም በላይ የኛ ኢትዮጵያዉያን ቀዳሚ ኃላፊነት እና ግዴታ ነዉ። እናም በመላዉ ዓለም የምትገኙ ኢትዮጵያዉያን ዘር ሃይማኖት፤ የፖለቲካ አመለካከት ሳይለያችሁ፤ እነዚህ ነገ ሃገር የሚረከቡ ህጻናትን ከፖለቲካ አመለካከት ዉጭ ሆነን በሰብዓዊነት ወደ ትምህርት ቤት እንዲመለሱ በሚደረገዉ ጥረት ሁሉም ኢትዮጵያዉያን ተሳታፊ እንዲሆኑ ጥሪዬን ማስተላለፍ እፈልጋለሁ። »
በስዊዘርላንድ የገበታ ለወገኔ የበጎ አድራጎት በአገርቤት በጦርነት የፈረሱ ትምህርት ቤቶችን ለማሰራት ይዞት የተነሳዉ ዓላማ ስኬሼት እንዲያገኝ እየተመኘን ለቃለምልልሱ የማህበሩን ሊቀመንበር እና የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊን በዶቼ ቬለ ስም በማመስገን ሙሉ ጥንቅሩን የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን።
አዜብ ታደሰ
ዮኃንስ ገብረግዚአብሔር