ጉንፋን መሰል በሽታ በባሕር ዳር
ረቡዕ፣ ጥር 17 2015በአማራ ክልል ርዕሰ ከተማ ባሕርዳርና አካባቢዉ የተዛመተዉ ጉንፋን መሰል ወረርሺኝ በርካታ ሰዎችን መያዙን ሕሙማንና ሐኪሞች አስታወቁ።ነዋሪዎች እንደሚሉት በሽታዉ በተለይ ሰዎች በብዛት በሚሰበሰቡበት ትምሕርት ቤቶችና መሰል ተቋማት ዉስጥ በፍጥነት እየተሰራጨ ነዉ።የሕክምና ባለሙያዎች የኮሮና ተሕዋሲ ምርመራ በመንዘንጋቱ በሽታዉ ኮቪድ 19ኝ ይሁን ሌላ በቅጡ ለመለየት አዳጋች ነዉ ይላሉ።የባሕርዳር ጤና መምሪያ ግን በከተማይቱና አካባቢዋ ከባድ ጉንፋን እንጂ ወረርሺኝ የለም ብሏል።
ካለፉት ሁለት ሳምንታት ጀምሮ በጉንፋን መሰል ህመም በዙዎች እየታመሙ እንደሆነ ከባህር ዳር ነዋሪዎች መካከል አንዳንዶቹ ለዶቼ ቬሌ ተናግረዋል፣ ህመሙ በአንድ ጊዜ ሁሉንም የቤተሰብ አባላት እንደሚያጠቃና ብርድ ብርድ የማለትና ሳል እንዳለበት አመልክተዋል፡፡
ወ/ሮ ሰበለ በሪሁን የተባሉ የከተማዋ ነዋሪ ቤተሰባቸውና ራሳቸው ታምመው በህክምና እርዳታ እንደተሸላቸው ገልፀውልናል፡፤
“ልጆች ከሳምንት በላይ ቆይተዋል፣ ኃይለኛ ጉንፋን ታምመው ሁለቱም ትምህርት ቤት አልሄዱም፣ የነሱ ጉንፋን ደግሞ ቤተሰቦቼን፣ እኔንም ባለቤቴንም ጭምር ነው ያመመን፣ በጣም ነው የታመምነው ለሳምንት ያህል፣ አሁን ይኸው ክሊኒክ ሄደን ታክመን መድኃኒት አገኘን አሁን ጥሩ ደረጃ ላይ ነን እግዚአብሔር ይመስገን፡፡” ብለዋል፡፡
የ3ኛ ክፍል ተማሪ ሆነችው ህሊና ያሬድም በህመሙ ምክንያት ትምህርት ቤት ለሳምንት ያክል አቋርጣ እንደነበር ነው ለዶቼ ቬሌ የተናገረችው፡፡
“የምማረው እሸት አካደሚ ነው፣ ክፍሌ 3ኛ ነው፣ ጉንፋን አሞኝ ትምህርት ቤት ቀርቼ ነበረ፣ የተለያዩ ትኩስ ነገሮችን እየጠጣሁ፣ ዘይት ያልበዛባቸውን ምግቦች እየበላሁ ለአንድ ሳምንት ትምህርት ቤት ቀርቼ ነበረ፣ የቀረሁትን ጊዜ ከጓደኞቼ ወስጄ እየፃፍኩኝ ሞልቻለሁ፡፡… ከቤታችን ስድስት ሰዎች አለን፣ ሁላችንም አሞን ነበር ”
በከተማው ከሚገኙ ትምህርት ቤቶች በአንዱ መምህር የሆኑት መምህርት አዳነች ኃይሉ ተማሪዎች በተለያዩ ምክንያቶች እንደሚቀሩ ጠቁመው ባለፈው ሳምንት በጉንፋን ጭምር ከትምህርት የቀሩ ተማሪዎች እንደነበሩ ተናግረዋል፡፡
በባሕር ዳር ከተማ የድሪም ኬር ጠቅላላ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅና የህብረተሰብ ጤና ሳይንስ ስፔሻሊስት ዶ/ር መኮንን አይችሉህም ስለጉዳዩ ተጠይቀው፣ በበሽታው ሁሉም ሰው እየተጠቃ መሆኑን ተናግረዋል፣ ክስተቱን ኮቪድ አይደለም፣ ጉንፋንም አይደለም ለማለት አስቸጋሪ መሆኑን ጠቅሰው ሆስፒታላቸው ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዚህ ህመም የተያዙ ሰዎችን ሲያክም እንደሚውል አስረድተዋል፣ ሆኖም ህብረተሰቡ የኮቪድ የመከላከያ መንገዶችን ሳያዛንፍ ይጠቀም ሲሉ መክረዋል፡፡
ዶ/ር መኮንን፣ “በየትምህርት ቤቱ ያሉ ህፃናት ልጆች፣ በቤተሰብ ደረጃ በጉንፋን መልክ የሚከሰቱ ነገሮች በከፍተኛ ደረጃ እየታዩ እንደሆነ እናያለን፣ በየጊዜው በጤና ተቋሞቻችን የሚጎበኙ ህፃናት ልጆች፣ ጎልማሶች፣ የቤተሰብ ኃላፊዎች በእንደዚህ ዓይነት ስሜት ይመጣሉ፣ ይህ ጉዳይ ኮቪድ አይደለም ሊያሰኘው አይችልም፣ ጉንፋን አይደለምም ሊያሰኘው አይችልም ግን አንድ ነገር ያስተምረናል፣ በአብዛኛው በመተንፈስ፣ በመሳል፣ በማስነጠስ በመሳሰሉት ነገሮች የሚተላለፉ በመሆናቸው ሁሉም ሰው ጥንቃቄዎችን ማድረግ እንዳለበት የሚያሳይ ነገር አለ፣ በዚህም ምክንያት ይኸ ነው ብለን መለየት በማንችለው ሁኔታ ጉንፋን መሰል ምልክት ያላቸው፣ የኮቪድ መሰል ምልክት ያላቸው ሰዎች በስፋት እየታዩ ነው፣ ተቋሞቻችንም እነሱን ነው ሲያክሙ የሚውሉት ” ነው ያሉት፡፡
አሁን በቅርቡ እንደወረርሽኝ እየታየ ያለውን በሽታ ምንነት ለማወቅ ምርመራ ተገቢ መሆኑን ባለሙያው መክረዋል፡፡
“ኮቪድ ነው ወይስ ጉንፋን ነው የሚለውን ነገር መለየት የሚያስችለው አንዱ ትልቁ ሥራ ምርመራዎችን ማድረግ ነው፣ በተለይ የኮቪድ ምርመራ ማካሄድ፡፡ የኮቪድ ምርመራ ደግሞ አሁን ባለንበት ሁኔታ በጣም በዝቅተኛ ደረጃ ያለ ምርመራ ሆኗል፣ በፊት የነበሩ ተቋማት አብዛኛዎቹ አሁን የኮቪድ ምርመራ እያካሄዱ አይደለም፣ በዚህ ሰዓት ምርመራ በየጤና ተቋማት መገኘት የነበረበት ነው፣ ነገር ግን ልክ በሽታው እንደጠፋ ሁሉ መዘናጋቶች በስፋት ያሉ በመሆናቸው ምርመራዎቹ በደንብ እየተካሄዱ አይደለም፤ እኔ በዚህ አጋጣሚ የሚመለከተው የጤና አካል ቢሰማና ቢያዳምጠን ምርመራዎቹ ቢካሄዱ የሚል ጥያቄ ጭምር ማቅረብ ነው የምፈልገው፡፡”
የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ አስማማው ሞገስ ግን የኮቪድ ምርመራዎች በመንግስት ጤና ተቋማት እየተሰጡ እንደሆነ አመልክተው ህብረተሰቡ የመዘናጋትና የመላመድ ነገር እንደሚታይበት ጠቅሰዋል፣ በከተማው ውስጥ በወረርሽኝ መልክ ባይጠቀስም ከባድ በሽታ መኖሩን ተናግረዋል፡፡
እንደ ዶ/ር መኮንን ደግሞ ህብረተሰቡም ሆነ የጤና ባለሙያው ለኮቪድ የሚያደርጉት ጥንቃቄ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መጥቷል፣ ህብረተሰቡ መዘናጋቱን ትቶ የኮሮና መከላከያ ዘዴዎችን ባግባቡ እንዲጠቀም አሳስበዋል፤ የፊት ጭምብል መጠቀም፣ በበሳሙና ባግባቡ መታጠብ፣ እርቀትን መጠበቅና ከንክኪ መራቅ ለኮቪድ ብቻ ሳይሆን ለሎች ተላላፊ በሽታዎችም ለመከላከል በእጅጉ ስለሚጠቅሙ ህብረተሰቡ ይህን አውቆ መከላከያዎቹን መጠቀም ይኖርበታል ብለዋል፡፡
ዓለምነው መኮንን
ነጋሽ መሐመድ
ታምራት ዲንሳ