ጋና ፤የአፍሪቃ የመልካም አስተዳደር ተምሳሌት
ሰኞ፣ ኅዳር 18 2010በዚህም መሰረት ምዕራብ አፍሪቃዊቷ ጋና 8 ተኛ ደረጃ ትገኛለች። ይሁን እንጅ ጋና ከመልካም አስተዳደር ባሻገር በኢኮኖሚዉ ረገድ ብዙ መስራት እንዳለባት የድርጅቱ ዋና ስራ አፅፈጻሚ ገልጸዋል።
የአፍሪቃ መንግስታት በየአመቱ ያሉበትን የመልካም አስተዳደር ደረጃ በመለየትና በመሸለም ይታወቃል። የሞኢብራሂም ድርጅት ።ይህ ድርጅት በዘንድሮዉ አመትም ምዕራብ አፍሪቃዊቷ ሀገር ጋና ከ54 ቱ ሀገራት ስምንተኛ ደረጃ መያዟን ገልጿል። ከቀጠናዉ ሀገራት ጋር ሲነጻጸር ጋና የተሻለ አፈጻጸም ብታሳይም በምዕራብ አፍሪቃ ሀገራትም ይሁን በመላዉ አፍሪቃ የመልካም አስተዳደር ሁኔታ እያሽቆለቆለ መምጣቱን በጎርጎሮሳዊዉ ህዳር 20 ቀን 2017 አ/ም የወጣዉ 11ኛዉ የድርጅቱ የመረጃ ጠቋሚ ሰነድ አመልክቷል።
እንደ ድርጅቱ የመልካም አስተዳደር ጥራት ማሳያ ጠቅላላ እሴቶች ከዜሮ እስከ 100 በተቀመጡ እርከኖች በ2007 እና በ2016 መካከል ከአንድ እስከ አምስት እስከ 65 ባሉት ነጥቦች ላይ ያረፈ ነበር።ባለፉት አምስት አመታት ግን እነዚህ እሴቶች በአመት በአማካኝ በ 0 ነጥብ 7 ማሽቆልቆላቸዉ ነዉ የተገለጸዉ ።
ይህ የሀገራት መረጃ ጠቋሚ ሰነድ ከ 100 የተለያዩ አመላካች መረጃወች የተገነባ ሲሆን ከ 2000 አ/ም ጀምሮ ከ36 የተለያዩ ምንጮች በተሰበሰበ መረጃም የተዋቀረ ነዉ።በዚህም መሰረት ሞሪሸስ ፣ሲሸልስና ቦትሳዋና የተሻለ መልካም አስተዳደር ያላቸዉ ሀገራት ተብለዋል።ኤርትራ ፣ደቡብ ሱዳንና ሶማሊያ ደግሞ በተቃራኒዉ ተቀምጠዋል።
መረጃዉ የመንግስታት እርምጃ በሰዎች ላይ ምን አይነት ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ማሳየት አለበት ሲሉ የሞኢብራሂም ድርጅት ዋና ስራ አስፈፃሚ ናታሊ ዴላፓሚ ይገልጻሉ።
«ይህ ስለቁርጠኝነት አይደለም ።ስለ ዲሞክራሲና የሰዉ ልጆች መብት፣ እንዲሁም ስለህጎች አይደለም።ይህ ዜጎች የመንግስታቸዉን የማገልገል ችሎታ ምን እንደሆነ መሬት ላይ የሚያዩበት ነዉ። ይህ እያንዳንዱ የ 21ኛዉ ክፍለ ዘመን መንግስት ለዜጎቹ ሊያቀርበው የሚገባው፣ ሸቀጦችንና አገልግሎቶች በአንድ ላይ የያዘ የጋራ ቅርጫት ነዉ። »
እንደ ናታሊ ዴላፓኒ የመንግስት ስራ አ የተሟላ የጤናና የትምህርት ስርዓትን የመሳሰሉ የግል ደህንነቶችን ሊያስጠብቁ የሚችሉ አገልግሎቶችን ሊያካትት ይገባል ።ይሁን እንጅ 8ተኛ ደረጃ በያዘችዉ ጋና በእነዚህ ዘርፎች ማሽቆልቆል ታይቶባታል።በመሰረተ ልማት ረገድም ቢሆን ከ10 ዓመት በፊት በምርጫ ዋዜማ በዋና ከተማ አክራ ከተሳራዉ የክዋሜ ንክሩማን አደባባይና መስቀለኛ መንገዶች ዉጭ ሌሎቹ መንገዶች ለትራፊክ ችግር የተጋለጡ መሆናቸዉ ይነገራል። የዉሃና የመብራት መቆራረጥ ችግርም ሌላዉ የነዋሪዎቿ ፈተና ነዉ ተብሏል። ያምሆኖ ግን የድርጅቱ ዘገባ በገጠር ልማት ዘርፍ ጋና ከፍተኛ እድገት እንዳላት ያሳያል። የድርጅቱ ስራ አስፈጻሚ ግን ጥሩ መንግስት በሁሉም ዘርፎች ሊሰራ ይገባል ባይ ናቸዉ።
«በጣም ከፍተኛ በሆነ ደረጃም ቢሆን፤ በአንድ የአስተዳደር እርከን ዉስጥ ብቻ መሻሻል ማስመዝገብ ዘላቄታ የለዉም።ይህ ቀጣይነት ያለዉ መሻሻል ፣ይህ ቀጣይነት ያለዉ ቁርጠኝነት ሁሉንም የአስተዳደር ዘርፎች ሊሸፍን ይገባል።» ናታሊ ዴላፓሚ የሞ ኢብራሂም ፋዉንዴሽን ዋና ዳይሬክተር።
የጋና ምክትል የማስታወቂያ ሚንስትር ኮዮ ንክሩማን ግን ሁኔታዉን ለማሻሻል መንግስታቸዉ የተቻለዉን ሁሉ እያደረገ መሆኑን ይናገራሉ።በተለይ ኢኮኖሚውን ማረጋጋት እና የቁጥጥር ስርዓቶችን በማጠናከር ላይ ትኩረት አድርጎ መስራቱን ይገልጻሉ።
«በመጀመሪያዉ አመት ብዙዉን ጊዜ ያጠፋነዉ የሀገር ዉስጥ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴን ወደነበረበት በመመለሱ፣ የዋጋ ግሽበትን በማዉረዱ፣ የውጭ ምንዛሪን በማረጋጋቱ፣ የመጠባበቂያ አቅማችንን በማረጋገጡ ላይ ነዉ። መንግስት ኢኮኖሚዉን ሊያሽመደምዱ የሚችሉ በሂደት ላይ ያሉ አቤቱታወችንና ዉዝፍ እዳወችን ለመክፈል በተጨማሪም እየሰራ ነዉ። እነዚህ ሁሉ የመለስተኛዉን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ለማረጋጋትና ወደነበረበት ለመመለስ በመጀመሪያ አመት የሰራናቸዉ ናቸዉ። ነገር ግን እድገትን ለማምጣትም በተመሳሳይ ሁኔታ ሰርተናል። ኮዮ ንክሩማህ የጋና ምክትል የማስተወቂያ ምንስትር።»
ምክትል ምንስትሩ ይህን ይበሉ እንጅ በ2016 ምርጫ በመንበረ መንግስቱን የያዙት አኮፎ አዶ በቀጣዮቹ ሶስት አመታት በርትተዉ ካልሰሩ የተሰናባቹ ፕሬዝዳንት የጆን ማሃማ እጣ ፋንታ ይገጥማቸዋል እየተባለ ነዉ። በሀገሪቱ የታየው ሰላማዊ የስልጣን ሽግግርና መልካም አስተዳደር ይህንን ይፈቅዳልና።ለዚህም ነዉ ትዉልደ ሱዳናዊና ብርታኒያዊዉ ሞ ኢብራሂም «በጋና ኮራን »ያሉት።
«ጋና በአፍሪቃ ጥሩ ዲሞክራሲ ካላቸዉ ሀገራት ዉስጥ አንዷ ሆና ቀጥላለች። በጋና የታየው የስልጣን ሽግግር አስደናቂና ልንኮራበት የሚገባ ነዉ።» ሞ ኢብራሂም
ፀሐይ ጫኔ
አርያም ተክሌ