ጎንደር ከትናንቱ ውጊያ ማግስት
ረቡዕ፣ መስከረም 8 2017ትናንትና ውጊያ ሲካሄድባት ነበር የተባለችው የጎንደር ከተማ ዛሬ የተኩስ ድምፅ እንደማይሰማባት ተገለጠ ። ሆኖም መደበኛ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ወደ ቀድሞው ሁኔታቸው እንዳልተመለሱ ነዋሪዎች ተናግረዋል ። የከተማዋ አስተዳደር በበኩሉ ሁሉም እንቅስቃሴዎች ወደነበሩበት ተመልሰዋል ብሏል ። በነበረው ተኩስ ሕጻናትን ጨምሮ ሰላማዊ ሰዎች ሕይወታቸውን ማጣታቸው ተዘግቧል ።
ባለፉት ጥቂት ሳምንታት በጎንደር ቀጣናዎች በመከላከያ ሰራዊትና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ጦርነቶች ሲካሄዱ ሰንብተዋል፡፡ ከሁለት ሳምንት በፊት በምዕራብ ጎንደር ዞን አንዳንድ አካባቢዎች ጦርነቶች ነበሩ፤ በዚህ ሳምንት ደግሞ በሰሜን ጎንደርና ማዕከላዊ ጎንደር ዞኖች አንዳንድ አካባቢዎች በሁለቱ ኃይሎች መካከል ውጊያዎች መከሄዳቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡
ከትናንት በስቲያ ከሰዓት በኋላና ትናንት በጎንደር ከተማ በከባድ መሳሪዎች የታገዘ ጦርነት በፋኖና በመከላከያ ሰራዊት መካከል ቀጥሎ መዋሉን ነዋሪዎች ለዶይቼ ቬሌ ገልፀዋል፡፡
ዛሬ ጎንደር እንዴት ናት?
ዛሬ ያነጋገርናቸው አንዳንድ የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች እንደገለፁልን ዛሬ በከተማዋና በአካባቢው የተኩስ ድምፅ አይሰማም፡፡ ትናንት በነበረው ውጊያ አዘዞ ተክለሃይማኖት በተባለው አካባቢ 3 ሰዎች መገደላቸውንና 2ቱ የት እንደደረሱ እንደማይታወቅ አንድ አስተያየት ሰጪ ዛሬ ቀትር ላይ ነግረውናል፡፡
"ጓደኞቻችን ነበሩ ሦስቱ ሞተዋል፣ አንዱ ቀብሩ ተፈፅሟል፣ ሁለቱም ሊቀበሩ ነው፣” ሁለት ሌሎች ሰዎች የት እንደደረሱ ማወቅ እንዳልተቻለ የተናገሩት አኚህ አስተያየት ሰጪ በከተማዋ ሁሉም ነገር ፀጥ ያለ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡
ቀበሌ 18 በሚባለው የከተማው ክፍል የሚገኙ ሌላ ነዋሪ በከተማዋ ምንም እንቅስቃሴ እንደሌለና ብዙዎቹ ሱቆች ዝግ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡ አሁን የጥይት ድምፅ በከተማዋና በአካባቢው አይሰማምምመ ብለዋል፤ ሆኖም ሌሊት ላይ አልፎ አልፎ የከባድ መሣሪ ድምፅ ይሰማ እንደነበር አስረድተዋል፡፡
"ቡልኮ” በተባለ ስፍራ በአንድ ከባድ መሳሪ በተተኮሰ ጥይት የሁለት ህፃናት ሕይወት ማለፉን አንድ የዓይን እማኝ ገልጠዋል፣ በነበረው ጦርነት አጠቃላይ ምን ያክል ጉዳት መድረሱን ለማወቅ እንቅስቃሴዎች ስለሌሉ ማወቅ እንዳልተቻለም እኚሁ ስተያየት ሰጪ አመልክተዋል፡፡
እንቅስቃሴ የለም
አንድ ሌላ የከተማዋ ነዋሪ የባለሦስት እር ተሸከርካሪዎች ቀስ በቀስ አገልግጎሎት መስጠት ቢጀምሩም ወደ አዘዞ መስመር ግን መንቀሳቀስ እንደማይቻል ተናግረዋል። የጎንደር ከተማ አስተዳደር የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ አቶ አበበ ላቀው ዛሬ ቀን 6 ሰዓት ላይ በሰጡን አስተያየት ደግሞ ትናንት በከተማዋ እስከ ቀኑ 10 ሰዓት ድረስ ጦርነት ስለነበር እንቅስቃሴዎች ሁሉ ተገትተው እንደነበር አስታውሰው፣ ሆኖም ዛሬ በከተማዋ ምንም ዓይነት የጦርነት ሁኔታ ባለመኖሩ ሁሉም መደበኛ እንቅስቃሴዎች በሁሉም የከተማው ክፍል ወደነበሩበት መመለሳቸውን አመልክተዋል፡፡
በነበረው ጦርነት የደረሰው ጉዳት ምንያክል እንደሆነ የተጠየቁት አቶ አበበ አሁን ባለው ሁኔታ ጉዳቱ እንደማይታወቅ ጠቁመው ጉዳዩ ተጣርቶ ካለቀ በኋላ በሚመለከተው የፀጥታ ክፍል በኩል መረጃው ይሰጣል ብለዋል፡፡
በሚያዝያ 2015 ዓ.ም መንግስት የልዩ ኃይሉን እንደገና ለማደራጀት በሚል ያወጣውን እቅድ ተከትሎ በተነሳ ተቃውሞ በአማራ ክልል የተፈጠረው ጦርነት ብዙ ሕይወት አጥፍቶ አሁንም መፍትሔ ሳያገኝ እንደቀጠለ ይገኛል፡፡
ዓለምነው መኮንን
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ፀሐይ ጫኔ