1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጥቃት ግድያ በሆሮጉዱሩ ወለጋ አሙሩና ጃርደጋ ጃርቴ አከባቢዎች

ረቡዕ፣ መስከረም 18 2015

ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን በጃርደጋ ጃርቴ እና አሙሩ ወረዳዎች ታጣቂዎች ንጹሃን ዜጎችንም ጭምር ኢላማ ያደረጉባቸው ተከታታይ ጥቃቶች የበርካቶችን ሕይወት ቀጥፏል። ኹኔታው አሁንም አሳሳቢ ሆኖ እንደቀጠለ ነው።

https://p.dw.com/p/4HTit
Äthiopien | Wahlen | Oromia

በተከታታይ ጥቃቶች የበርካቶች ሕይወት ተቀጥፏል

ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን በጃርደጋ ጃርቴ እና አሙሩ ወረዳዎች ታጣቂዎች ንጹሃን ዜጎችንም ጭምር ኢላማ ያደረጉባቸው ተከታታይ ጥቃቶች የበርካቶችን ሕይወት ቀጥፏል። ኹኔታው አሁንም አሳሳቢ ሆኖ እንደቀጠለ ነው። ሰሞኑን ከጃርደጋ ጃርቴ የተቋረጠው የስልክ አገልግሎት ዛሬ በአሙሩ ወረዳም ተቋርጦ በውስን የተመረጡ ቦታዎች ብቻ የስልክ የግንኙነት መስመሩ እንደሚሠራ ነው ለማወቅ የተቻለው። በግንኙነት መቋረጥ የተነሣ ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል ከተባሉ ቦታዎች በቀጥታ የዐይን እማኞችን አነጋግሮ ግልጽ መረጃ ለማግኘት አልተቻለም። አንድ አገምሳ ከተማ አቅራቢያ ተራራማ ቦታ ሆነው ለዶይቸ ቬለ የተናገሩ ነዋሪ ግን፦ የታጣቂዎች ሰለባ የሆኑ እንደ ጎቡ፣ ኦቦራ፣ ሃሮጉዲና፣ ወልቂጤ፣ ሪገቴ በሚባሉ አከባቢዎች በደረሰው ጥቃት በርካታ ዜጎች መሞታቸውን እየሰማን ነው ብለዋል።። 

ዶይቼ ቬለ ባለፈው ሳምንት ሐሙስ መስከረም 12 ቀን፣ 2015 ዓ.ም. በጃርደጋ ጃርቴ ወረዳ ከተማ በሆነችው አሊቦ ቀበሌ 01 ታጣቂዎች በንጹሃን ዜጎች ላይ አነጣጥሮ በወሰዱት የጥቃት ርምጃ የበርካታ ሰዎች ሕይወት መቀጠፉንና የነዋሪዎች ቤት ንብረት መውደማቸውን ከዐይን እማኞች በመረዳት መዘገቡ ይታወሳል። በዚህ ወረዳ ከባለፈው ዓርብ ጀምሮ የስልክ መገናኛ ኔትዎርክ በመቋረጡ ዶይቼ ቬለ በቀጥታ የአከባቢውን ነዋሪዎች፣ የዐይን እማኞች አሁን ያሉበትን ሁኔታ ለመጠየቅ ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

ከጃርደጋ ጃርቴ በተጨማሪ በተለይም ባለፈው እሁድ መስከረም 15 ቀን፣ 2015 ዓ.ም ወደ አጎራባች አሙሩ ወረዳ ተስፋፍቶ የበርካታ ንጹሃን ዜጎችን ሕይወት በመቅጠፍ፤ ንብረታቸውንም ያወደመው የታጣቂዎች ጥቃት እስካሁንም እልባት በማጣቱ፤ ስጋትን በአከባቢው አንግሶ መቀጠሉን የሚገልጹ አሉ። 

እንደ ጃርደጋ ጃርቴ ሁሉ በአሙሩ ወረዳም ዛሬ የስልክ ኔትዎርክ ተቋርጦ አዲስ ጥቃቱ በተፈጸመባቸው አከባቢዎች አሁናዊ ሁኔታን በተመለከተ ነዋሪዎችን ቀጥታ ማግኘት አዳጋች ቢሆንም አልፎ አልፎ ከሌላ አከባቢዎች በሚመጣ ኔትዎርክ በወረዳው አገምሳ ከተማ ዛሬ አንድ ነዋሪን በስልክ አነጋግረን ነበር።

Äthiopien | Wahlen | Oromia

እኚህ ነዋሪ ከአንድ ወር በፊት ነሐሴ 24 ቀን፣ 2014 ዓ.ም. የአማራ ታጣቂዎች በአሙሩ ወረዳ አገምሳ ከተማ ላይ ወስደዋል በተባለው ጥቃት ከቀየያቸው የተፈናቀሉ፤ ንብረታቸውም የወደመባቸው ናቸው። እኚህ ነዋሪ እንደሚሉት ይህቺ የአገምሳ ከተማ አሁን ላይ ከአከባቢው የተሻለ አንጻራዊ ሰላም ሲኖራት፤ በአከባቢው ያሉ ቀበሌያትና ወረዳዎች ግን ውጥረት እንደነገሰባቸው ነው፡፡ 

እኚሁ የአገምሳ ከተማ ነዋሪ ዛሬ በሰጡን አስተያየታቸው በአከባቢው በፀጥታ ችግር የተገደበው እንቅስቀሴ ነዋሪዎችን ለሰቆቃ ዳርጓል። “እንደ አሙሩ ወረዳ አሁን ኔትዎርክ ሙሉ በሙሉ በመቋረጡ በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ እኛ ነዋሪዎች እርሰ በራሳችን እንኳ መረጃ መለዋወጥ ተስኖናል፡፡ አሁን እንኳ በስልክ አግኝተህኝ የማውራህ አጋጣሚ ወደ ተራራ ወጥቼ ከጎጃም-ቡሬ አልፎ አልፎ በሚገባ የሚቆራረጥ ኔትዎርክ ነው” ብለዋልም፡፡

“አሁን አንድ ወር ያስቆጠርንበት የፀጥታ ችግር ከገጠመን ወዲህ ዉኃ የለም፣ መብራት እና የባንክ አገልግሎት ብሎም እንደ ሱቅ ያሉ የንግድ አገልግሎት ምንም የለም። በዚህ ላይ በመንግስት በኩል የሚገባልን ርዳታም የለም፡፡ ከወለጋ ዩኒቨርሲቲ የደረሰን በቆሎ እንኳ በኤሌክትሪክ እጦት ማስፈጫ አጥተን ኅብረተሰቡ ያው አማራጭ ስለሌለው ቀቅሎ ነው የበላው፡፡ በርግጥ መንግስት የፀጥታ ጉዳይን በተሻለ መልኩ ጥበቃ ቢያደርግልንም ከአስከፊው ችግር መውጣት አልቻልንም” ሲሉም አስተያየታቸውን አክለዋል፡፡

እኚሁ ነዋሪን እሳቸው ከሚኖሩበት አገምሳ ከተማ ወጣ ብሎ ወደሚገኙ አጎራባች አከባቢዎች አሁናዊ ሁኔታ ተጠይቀው፤ “ባለፈው እሁድ የታጣቂዎች ሰለባ የሆኑ እንደ ጎቡ፣ ኦቦራ፣ ሃሮጉዲና፣ ወልቂጤ፣ ሪገቴ በሚባሉ አከባቢዎች በደረሰው ጥቃት በርካታ ዜጎች መሞታቸውን እየሰማን ነው፡፡ ከዚህ ወጣ ለማለት መንገድ ትራንስፖርቱ አስቸጋሪ ስለሆነ ግን ሁሉንም ነገር ማወቅ ከባድ ነው፡፡ የመሰረታዊ የፍጆታ እቃ እና የአገልግሎት ተቋማት መቋረጥ ግን አገምሳም ላይ እንደከፋ ነው ያለው” በማለት ስለሁኔታው አስረድተዋል፡፡

እኚው አስተያየት ሰጪ የአሙሩ ወረዳ ዋና ከተማ የሆነችው ኦቦራ የፀጥታ ችግር ተደቅኖባት የወረዳዋ አመራሮች ከትናንት በስቲያ ሰኞ መስከረም 16 ቀን፣ አመሻሽ ጀምሮ እስከ ዛሬ ጠዋት በዚህች አገምሳ ከተማ ተጠልለው ዛሬ ወደዚያች ወደ ወረዳዋ ከተማ ሲመለሱ መመልከታቸውንም አንስተውልናል፡፡

ዶይቼ ቬለ ከትናንት በስትያ ሰኞ የእሁዱን ጥቃት በማስመልከት በአሙሩ ወረዳ ጎቡ ሲርባ ቀበሌ በስልክ ነጋገራቸው ነዋሪ ቢያንስ 80 የሚሆኑ ሰላማዊ ዜጎች የአማራ ታጣቂዎች ባሏቸው መገደላቸውን አመልክተዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ከኪረሙ ወረዳ ሀሮ ቀበሌ አስተያየታቸውን የሰጡን የአማራ ተወላጅ ነዋሪ ንጹሃን ዜጎች ላይ አነጣጥሮ ለሚፈጸመው ጥቃትና ግድያ መንግስት ‘ሸነ’ ያለውና እራሱን “የኦሮሞ ነጻነት ጦር” ብሎ የሚጠራውን ታጣቂ ቡድንን ተጠያቂ ያደርጋሉ፡፡

Äthiopien | Wahlen | Oromia

በምስራቅ ወለጋ እና ሆሮጉዱሩ ወለጋ ዞኖች አማራ ክልልን በሚያዋስኑ አከባቢዎች ነዋሪዎች ለሚፈጸምባቸው ጥቃትና ግድያ የአማራ ታጣቂዎች እና የኦሮሞ ነጻነት ጦር (በተለምዶ ኦነግ ሸነ) ያሉትን ታጣቂ ቡድኖች ሲከሱ ይህ የመጀመሪያው አይደለም፡፡ 

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከትናንት በስቲያ ሌሊት ባወጣው መግለጫ በአሙሩ፣ ሆሮ ቡሉቅ እና በጃርደጋ ጃርቴ ወረዳዎች ከነሐሴ 25 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ባሉት ሦስት ሳምንታት በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (በተለምዶ ኦነግ ሸኔ)፣ በአማራ ኢመደበኛ ታጣቂ ኃይሎች እና ግለሰቦች በተከታታይ በተፈጸሙ ጥቃቶች ከ100 በላይ ሲቪል ሰዎች መገደላቸውን አረጋግጧል። 

የኮሚሽኑ የአከባቢው ምርመራ ኃላፊው አቶ ኢማድ አብዱልፈታ ለዶቼ ቬለ በዚሁ ላይ በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያም፤ ሰላማዊ ዜጎች በእነዚህ አጎራባች የሆሮጉዱሩ ዞን ወረዳዎች ብሔራቸው ተለይተው ተጠቅተዋል ነው ያሉት፡፡ 

ኮሚሽኑ ከዚህም በተጨማሪ ነዋሪዎች ሃብት ንብረታቸውን መዘረፋቸው፣ በሺዎች የሚቆጠሩም ቀዬያቸውን ጥለው ለመፈናቀል መገደዳቸውን ብሎም አስፈላጊው የመንግስት ድጋፍ አጥተው አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ መሆናቸውን በመግለጫው አብራርቷል፡፡

ስለእነዚህ አከባቢዎች ጥቃት እና መፍትሄው ዶይቼ ቬለ ከየአከባቢው ባለስልጣናት፣ ከኦሮሚያ ክልል እና ከፌዴራል መንግስት ባለስልጣናት ለማጣራት ያደረገው ጥረት እስካሁን አልሰመረም። የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስቴር ቅዳሜ ባወጣው መግለጫ ግን በጃርደጋ ጃርቴ ወረዳ ሸነ ያሉት ታጣቂ ቡድን (ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ብሎ የሚጠራው ታጣቂ) በሰላማዊ ዜጎች እና ሚሊሻ ላይ ግድያ መፈጸሙን በማመልከት ስለሁኔታው ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ግን ተቆጥበዋል፡፡

ሥዩም ጌቱ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ታምራት ዲንሳ