1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጨፌ ኦሮሚያ ጉባኤ እና የፀጥታ ጥያቄ

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 4 2015

«ታጥቆ በኤክስካቫተር ወርቅ የሚያወጣው ኃይልም ከዚያ አከባቢ መውጣት አለበት፡፡ ይህ ከተስተካከለ ወደ ኬንያ የሚላከውን ኮንትሮባንድ መቆጣጠር ቀላል ነው፡፡»

https://p.dw.com/p/4TjJ7
Äthiopien Sitzung des Regionalrats von Ormia
ምስል Seyoum Getu/DW

ጨፌ ኦሮሚያ ጉባኤ እና የፀጥታ ጥያቄ

በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን ታጣቂዎች በወርቅ ማዕድን ንግድ ላይ ከመሳተፍ እስከ እራሳቸው በመቆፈሪያ ማሽን ወርቅ ማውጣት እንደደረሱ የጨፌ ኦሮሚያ ምክርቤት አባላት ተናገሩ። በኮንትሮባንድ ንግዱ የመንግስት ባለስልጣናት ተሳታፊ ናቸውም ተብሏል። ትናንትና እና ዛሬ በአዳማ ከተማ ገልማ አባ ገዳ ጨፌ አዳራሽ ሲካሄድ በቆየው የጨፌ ኦሮሚያ መደበኛ ጉባኤ ላይ ጎልቶ ከተነሱ ሃሳቦች ክልሉን እየፈተነ ያለው የሰላምና ፀጥታ ጉዳይ ተጠቃሽ ነው፡፡
የክልሉ ፕሬዝዳት አቶ ሽመልስ አብዲሳ መንግስታቸው አሁንም ለሰላም ያለው በር ክፍት መሆኑን ጠቅሰው፤ “«ነግ ሸነ» ካሉት «የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት» ጋር የተጀመረው የሰላም ሂደት እንዲቀጥል ፍላጎት መኖሩን ጠቁመዋል፡፡
ትናንት ሰኞ ተጀምሮ ዛሬም ቀጥሎ በተካሄደው የጨፌ ኦሮሚያ ስድስተኛ ዘመን 2ኛ ዓመት 5ኛ መደበኛ ጉባኤ በጉልህ ከተንሸራሸሩ ሃሳብ አንደኛው በክልሉ ከጊዜ ወደ ጊዜ አሳሳቢነቱ ያልቀነሰው የሰላምና ፀጥታ ጉዳይ ነው፡፡ የጨፌው አባላትም ይህን የፀጥታን ጉዳይ የክልሉ ስራ አስፈጻሚ ሪፖርት ላቀረቡት ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ ደጋግመው አንስተዋል፡፡ በዚህ ጉባኤ የተሳተፉት ወ/ሮ መሰረት የተባሉ የሰሜን ሸዋ ዞን ተወካይ በዞኑ ሰዎች በየጊዜው እየታገቱ ገንዘብ እየከፈሉ እንደሚለቀቁ በማንሳት አስከፊ የፀጥታ ችግር መኖሩን ነው የተናገሩት፡፡  
“በልዩ ሁኔታ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት መፈታት አለባቸው ብዬ ከማነሳው ጉዳዮች አንደኛው በሰላሌ ዞን የሚስተዋለው አስከፊ የፀጥታ ችግር ነው፡፡ ዞኑ በጽጥታ ችግሩ ውስጥ የወደቀው በሁለት መንገድ ነው፡፡ አንደኛው በውስጥ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ከሚያጎራብተን ክልል በሚነሱ ፅንፈኞች ነው፡፡ ህዝባችን በየቀኑ ነው ይህን የጸጥታ ችግር የሚጋፈጠው፡፡ በየቀኑ መታፈን፣ ገንዘብ መክፈል ከዚያም አልፎ መገደል የህዝባችን እጣፈንታ ሆኗል፡፡ ከዚህ በፊት በ5 ወረዳዎች ብቻ ይስተዋል የነበረው የፀጥታ ችግሩ አሁን ላይ ሁሉንም ወረዳዎች አዳርሷል፡፡” ዳዲ ዳዳቻ የተባሉ ሌላኛው የጨፌ አባል በጉጂ ዞን ውስጥ ታጣቂዎች በወርቅ ማዕድን ንግድ ላይ ከመሳተፍ እስከ በመቆፈሪያ ማሽን ወርቅ ማውጣት መድረሳቸውን ነው የተናገሩት፡፡ “ከጉጂ የሚወጣው ወርቅ የኦሮሞን ህዝብ ማልማት አለበት፡፡ ከባድ የኮንትሮባንድ ንግድ ነው በዚያ አከባቢ ያለው፡፡ ከጋምቤላ እና ቤኒሻንጉል ድረስ የሚመጣ ወርቅ ጉጂ ውስጥ ነው የሚሸጠው፡፡ እንደ ግል እኔ በዚህ አከባቢ ያለኝ ትዝብት አንደኛው የፀጥታ ችግር ነው፡፡ ይህ የፀጥታ ችግር ምንጩ ሁለት ነው፡፡ የኮንትሮባንድ ንግዱ ውስጥ የመንግስት ባለስልጣናትም ሆነ ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ ሸማቂዎች ተሳታፊ ናቸው፡፡ ይህ ችግር መፍትሄ ይሻል፡፡ ታጥቆ በኤክስካቫተር ወርቅ የሚያወጣው ኃይልም ከዚያ አከባቢ መውጣት አለበት፡፡ ይህ ከተስተካከለ ወደ ኬንያ የሚላከውን ኮንትሮባንድ መቆጣጠር ቀላል ነው፡፡ የዚህ አገር ሃብት ተጠቃሚ መሆን ያለበት የዚህ አገር ህዝብ እንጂ ኬንያ ልትበለጽግበት አይገባም፤ መስተካከል አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡”
የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ በተነሱት ጥያቄዎች ላይ መልስ እና ማብራሪያ ሲሰጡ፤ ማዕድናት በህገወጥ መንገድ ከአገር እየወጡ መሆኑን አረጋግጠው፤ በእየለቱ ይፈጸማል ስለተባለው የሰዎች መታገት ላይ ግን በተለየ መልክ የሰጡት ማብራሪያ የለም፡፡ በኦሮሚያ እገታ ይፈጸምብናል ያሉ ሰዎች በክልሉ ታጥቆ መንግስትን የሚወጋው የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ወይም መንግስት ሸነ ያለውን ታጣቂ ቡድን ይከሳሉ፡፡ ታጣቂ ቡድኑ ግን ክሱን በተደጋጋሚ ያስተባብላል፡፡ 
 ፕሬዝዳንት ሽመል  መንግስታቸው አሁንም በሰላማዊ መንገድ ለሚደረግ መፍትሄ ዝግጁ መሆኑን ነው ያስረዱት፡፡ “ከጦርነቱ የሚጠቀም አንድም አካል የለም፡፡ ከኦነግ ሸነ ጋር ደጋግመን መክረናል፡፡ አሁንም ቅድሚያ የምንሰጠው ለሰላም ነው፡፡ ደግመን ደጋግመን በኦሮሞ ህዝብ እና በዚህ በተከበረው ጨፌ ስም በሰላም ግቡ፣ ነገራችሁን በውይይትና እርቅ ፍቱ የሚል ጥሪ እናቀርብላቸዋለን፡፡ በግል ይሁን በቡድን በሰላም እስከመጣ ድረስ መንግስት መሄድ ከሚገባውም በላይ ለመሄድ ዝግጁ ነው፡፡ ምክኒያት ብትሉ በዚህ ግጭት ህዝባችን ተጎዳ እንጂ ማንም አልተጠቀመም፡፡ በርግጥ ጠላቶቻችን ተጠቅመውበት ይሆናል፡፡ የክልላችን መንግስት ግን ከዚህ ሊጠቀም አይችልም፡፡ ይህን ነገር በሰላም ቋጭተን የፈለገ ልዩነት እንኳ ቢኖረን ለቀጣይ ትግል መስራት አለብን፡፡ በሃይል የሚፈታ ችግር የለም፡፡ ባለፈው ጥሪ ካቀረብን በኋላ የሄድንበት መልካም ውይይቶች ነበሩ አሁንም እሱ እንዲቀጥል ነው የምናበረታታው፡፡ መንግስታችን ለዚህ ዝግጁ ነው፡፡ ለሰላም በራችን አይዘጋም፡፡ ህዝባችንም በጫካ ያሉ ልጆች ወደ ሰላማዊ ትግል እንዲገቡ ማበረታታት ይጠበቅበታል፡፡ ከዚህ ውጪ ግን የክልልም ሆነ የፌዴራል መንግስት የህግ የበላይነትን የማረጋገጥ ግዴታ አለባቸው፡፡ ሰው ወጥቶ መግባት አለበት፡፡ በመሆኑም ጎን ለጎን የጸጥታ ማስከበር ስራው በየደረጃው የሚሰራ መሆኑን መግለጽ እፈልጋለሁ፡፡” 
አቶ ሽመልስ አክለውም ጽንፈኛ ያሏቸው ሃይሎች ያደርሳሉ ያሉትን አለመረጋጋት መንግስታቸው "ብስለት ባለውና በዘለቄታው ለመ ፍታት" እየጣረ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በጨፌ ኦሮሚያው ጉባኤ ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ያደርጋሉ የተባሉ ፕሮጀክቶች፣ የኑሮ ውድነት እና የግብርና ግብዓት አቅርቦትን የገጠመው ተግዳሮት ላይም ሀሳቦች ተነስቶ መፍትሄ የተባሉ አስተያየቶች ተሰጥቶባቸዋል፡፡
ስዩም ጌቱ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሔር
ነጋሽ መሐመድ

Äthiopien Sitzung des Regionalrats von Ormia
ምስል Seyoum Getu/DW