1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ፈረንሳይ ውስጥ እጅግ የተስፋፋው ኮቪድ-19

ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 21 2014

ፈረንሳይ ውስጥ ባለፈው ማክሰኞ ብቻ በተደረገ ምርመራ 208,000 ሰዎች ላይ የኮሮና ተሐዋሲ ተገኝቷል። የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) ከፍተኛ የተሐዋሲ ሥርጭቱን «ሱናሚ» ሲል ገልጦታል። የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት (AFP) በእየ ቀኑ በዓለም ዙሪያ በኮሮና ተሐዋሲ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ዛሬ ለመጀመሪያ ጊዜ ከ1 ሚሊዮን ማለፉን ዘግቧል።

https://p.dw.com/p/44zvx
Illustration Mikroskop Coronavirus
ምስል picture-alliance/M. Schönherr

የተሐዋሲ ሥርጭቱ «ሱናሚ» ተብሏል

ፈረንሳይ ዳግም ከፍተኛ የኮሮና ተሐዋሲ ሥርጭት እየተስተዋለባት ነው። ባለፈው ማክሰኞ ብቻ በተደረገ ምርመራ 208,000 ሰዎች ላይ የኮሮና ተሐዋሲ ተገኝቷል። የዓለም ጤና ድርጅት (WHO)  ከፍተኛ የተሐዋሲ ሥርጭቱን «ሱናሚ» ሲል ገልጦታል። የሀገሪቱ ጤና ሚንሥትርም ሥርጭቱ እጅግ ከፍተኛ መኾኑን ገልጧል። እንደ ፈረንሳይ ዜና አገልግሎት (AFP) ዘገባ ከኾነ በእየ ቀኑ በዓለም ዙሪያ በኮሮና ተሐዋሲ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ዛሬ ለመጀመሪያ ጊዜ ከአንድ ሚሊዮን አልፏል። ባለፉት ሰባት ቀናት ውስጥ ብቻ  በዓለም ዙሪያ 7.3 ሚሊዮን ሰዎች በኮሮና ተሐዋሲ ተጠቅተዋል። ለመሆኑ የኮሮና ተሐዋሲ ሥርጭት ፈረንሳይ ውስጥ በአሁኑ ወቅት ምን መልክ አለው፤ ስለሥርጭቱስ ምን እየተባለ ነው?

ክርስቲያን አላርድ የተባሉ ሐኪም እንደተናገሩት ከኾነ ፈረንሳይ ውስጥ ከዚህ ቀደም ሁለት ጊዜ የተከተቡ በርካታሰዎች የኮሮና ተሐዋሲ ስለተገኘባቸው ሦስተኛውን የማጎልበቻ ክትባት ለመውሰድ የነበራቸውን ቀጠሮ ለመሰዘረዝ ተገደዋል። ፈረንሳይ ከህዝብ ብዛቷ አንጻር በርካታ ሰዎችን  በመከተብ ትታወቃለች። አስፈላጊ የተባለውን የሁለት ጊዜ ክትባት የተወጉ ሰዎችንም ጭምር ፈረንሳይ ውስጥ የኮሮና ተሐዋሲ በብዛት ያጠቃበት ምክንያቱ ምንድን ነው እየተባለ ነው?

Coronavirus Antigen-Schnelltest
ምስል Jakub Porzycki/NurPhoto/picture alliance

የአውሮጳ እና ሰሜን አሜሪካ የጤና ባለሞያዎች በተለይ የልውጡ ኦሚክሮን ተሐዋሲ ሥርጭትን ለመግታት የማጎልበቻ ማለትም ለሦስተና ጊዜ የሚሰጠውን ክትባት ሰዎች እንዲከተቡ አጥብቀው ይመክራሉ እጅግም ያበረታታሉ። ለመሆኑ የፈረንሳይ መንግሥት በከፍተኛ ፍጥነት እየተሰራጨ ያለውን የኮሮና  ተሐዋሲ ለመግታት ምን አይነት ርምጃዎችን እየወሰደ ነው፤ ወደፊትስ ምን አስቧል?

ፈረንሳይ ውስጥ በከፍተኛ ፍጥነት እየተሰራጨ የሚገኘው የኮሮና ተሐዋሲ ጉዳይን በተመለከተ ከፖሪስ ወኪላችን ሃይማኖት ጥሩነህ ጋር የተደረገ ቃለ መጠይቅ ነው። ሙሉ ቃለ መጠይቁን ከድምጽ ማጫወቻው ማድመጥ ይቻላል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ
ሃይማኖት ጥሩነህ
ሸዋዬ ለገሰ