1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመኑ የፊልም ፊስቲቫል በርሊናለና ኢትዮጵያዉያን

ሐሙስ፣ የካቲት 9 2009

የበርሊኑ ዓለም አቀፋዊ የፊልም መድረክ «በርሊናለ» ዘንድሮ እየተካሄደ ያለዉ ለ 67 ኛ ጊዜ ሲሆን ከ 400 በላይ ፊልሞች ለአስር ቀናት በሚዘልቀዉ የፊልም መድረክ ለእይታ ቀርቦአል።  የዘንድሮ የበርሊኑ ዓመታዊ የፊልም መድረክ በርሊናለ ወጣት የአፍሪቃ የፊልም ባለሞያዎችንም እንደሚያሳትፍ ተገልፆአል።

https://p.dw.com/p/2XgO1
Berlin - Berlinale
ምስል DW/M. Z. Haque

የጀርመን የፊልም ፌስቲቫል «በርሊናለ» እና ኢትዮጵያውያን

ዘንድሮ ለ67ኛ ጊዜ ጀርመን መዲና በርሊን ላይ የሚካሄደዉን ዓለም አቀፍ የፊልም ፊስቲቫል «በርሊናለ»ን በይፋ የከፈቱት ሆላንዳዊዉ የፊልም ሥራዋ አዋቂዉና የበርሊናለ ፊልም ፊስቲቫል የፊልም ምዘና ቡድን ፕሬዚዳንት ፓዉል ፈርሆቭን ነበሩ። በርሊን ከተማ የዓለምአቀፉን የፊልም መድረክ እያስተናገደች ነዉ። ባለፈዉ ሳምንት ሃሙስ የጀመረዉ የበርሊኑ ዓለም አቀፋዊ የፊልም መድረክ «በርሊናለ» ዘንድሮ እየተካሄደ ያለዉ ለ 67 ኛ ጊዜ ሲሆን ከ 400 በላይ ፊልሞች ለአስር ቀናት በሚዘልቀዉ የፊልም መድረክ ለእይታ ቀርቦአል።  የዘንድሮ የበርሊኑ ዓመታዊ የፊልም መድረክ በርሊናለ ወጣት የአፍሪቃ የፊልም ባለሞያዎችንም እንደሚያሳትፍ ተገልፆአል። በዚህ ዝግጅታችን ስለ ዘንድሮዉ የጀርመኑ ዓለም አቀፍ ዓመታዊ የፊልም መድረክ ስለ 67 ኛዉ በርሊናለ እያየን ኢትዮጵያዉያን የፊልም ሥራ አዋቂዎች ስለጀርመኑ የፊልም መድረክና ተሞክሮአቸዉ ይነግሩናል።  

Berlinale Guinea-Bissau Flora Gomes
ምስል DW/C. Vieira Teixeira

በርሊን ላይ ለ 67 ኛ ጊዜ እየተካሄደ ያለዉ ዓለም አቀፉ የፊልም ፊስቲቫል «በርሊናለ» በይፋ እንደተከፈተ ዓለምን እያነጋገረ ስላለዉ ስለአዲሱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንትና ፖለቲካቸዉ የበርሊኑ የፊልም መድረክም በቅድምያ ያነሳዉ ነጥብ ነበር ። የመድረክ አስተዋዋቂዎች መድረኩ ላይ ሲወጡ ያነሱት ርዕስ ይህ ነበር ።

«ለዓለም አቀፉ እንግዶች ጥያቄ አለኝ፤ ወደዚህ የመጣችሁት ለፊልም ፊስቲቫሉ ነዉ ወይስ ወደ ሃገራችሁ እንዳትመለሱ ያገዳችሁ ነገር አለን።? ምንም ሆነ ምንም ወደኛ እንኳን ደህና መጣችሁ፤ እዚህ እጃችንን ዘርግተን እንቀበላችኋለን።» ሌላዋ መድረክ ላይ የቀረበች የፊልም ሰራተኛ፤ ለከያኒዎች ቅድምያ እንዲሰጥ ስትል አስተጋብታለች። ትራምፕን አሜሪካ ትቅደም የሚለዉን አነጋገርን ዉድቅ ለማድረግ ያነሳችዉ ነበር።

ፖለቲካዉን በጥቂቱም ቢሆን በመዳሰስ የጀመረዉ የበርሊኑ የፊልም መድረክ በርሊናለ በቀድሞ ጊዜ በናዚ ተይዞ ከነበረዉ የፈረንሳይ ግዛት ለመዉጣት ጥረት ስላደረገዉ ስለታዋቂዉ ፈረንሳዊ የጊታር ተጫዋችን የጃንጎ ራይንሃርድት የሕይወት ታሪክን በሚያሳየዉ ፊልም ነበር የበርሊኑ የፊልም ፊስቲቫል የጀመረዉ።  ጃንጎ ራይንሃርድት በጎርጎረሳዊዉ 1943 በናዚ በተያዘችዉ ፓሪስ ከተማ ነዋሪ የነበረ ከሲንቲና ሮማ ማኅበረሰብ የሚወለድ ታዋቂዉ የጊታር ተቻዋች መሆኑ ይነገርለታል።  በርሊናለ ከዓለም ሃገራት ተመርጠዉ የተሰበሰቡትን  399 ፊልሞችን በከተማዋ በሚገኙ የተለያዩ ፊልም ቤቶች ማሳየቱን ቀጥሎአል።  ከነዚህ ፊልሞች መካከል ደግሞ 18 ፊልሞች መድረኩ ለሚሸልመዉ ለወርቅማዉና ለብርማዉ ድብ ይወዳደራሉ። ከወዲሁ የፊልም ዉድድሩ እጅግ ከፍተኛ መሆኑ እየተነገረ ነዉ። በዚህ ዉድድር ላይ ለእይታ ከሚቀርቡት ወደ 400 ከሚሆኑት ፊልሞች መካከል 125 የሚሆኑት ፊልሞች በፊልም ስራ አዋቂ ሴቶች የሚመራ መሆኑም ተመልክቶአል።   

በበርሊን በመካሄድ ላይ በሚገኘዉ ዓለም አቀፍ የፊልም መድረክ ላይ የዉድድር ከቀረቡት ፊልሞች መካከል ፊሊሲቴ የተሰኘዉ ፊልም ይገኝበታል። ይህ ፊልም በሲኔጋል በፈረንሳይ፤ ጀርመን ሊባኖን  እንዲሁም በቤልጂየም የፊልም ሠራተኞ ቅንብር የቀረበ ሲሆን አንድ ልጅዋ የታመበባት አፍሪቃዊት እናት ልጅዋን ለማሳከም ለሆስፒታል ገንዘብ ሲያስፈልጋት የሚተርክ ፊልም ነዉ። ይህ ፊልም ባለፈዉ የጎርጎሮሳዊው 2016 ዓ,ም በአዉሮጳ በተካሄደ የፊልም ዉድድር ላይ ሽልማቶችን አግኝቶአል መፈለግዋን ያሳያል።

Berlin - Berlinale
ምስል DW/M. Z. Haque

በበርሊናለ የፊልም ፊስቲቫል ላይ በየጊዜዉ በሚቀያየረዉና በሚያድገዉ የቴክኖሎጂ ዓለም የወደፊት የፊልም ሥራ እንዴት ሊሆን እንደሚችል የተለያዩ አዉደ ጥናቶችም ይካሄዳሉ። የአፍሪቃን ፊልም በተመለከተ ዘንድሮ እየተካሄደ ባለዉ ፊስቲቫል ላይ ከአህጉሪቱ የመጡት የሞሮኮ የፊልም ሠራተኞች ሲሆኑ ፊልም ቀረፃን በተመለከተ በፊልሙ ዓለም ሞሮኮ ከፍተኛ ተቀባይነትን ማግኘትዋ ተነግሮላታል። ከሞሮኮ ወደ በርሊን የመጡት የፊልም ሥራ ተንታኝ እንደተናገሩት፤

«የፊልም ፕሮጀክቶችን ወደ ሃገራችን እንዲገቡ በማድረግ ለምሳሌ ከፍል ቀረፃ ሊሆን ይችላል እንደምታዩት አሜሪካዉያን የተለያዩ ግዙፍ የፊልም ፕሮጀክቶችን ይዘዉ ይመጣሉ ስለባግዳድ አፍጋኒስታን ቀረፃን የሚያካሂዱት እዚህ ነዉ። እንደሚታወቀዉ ፊልም የሚሰራዉ ወቅታዊዉን ሁኔታ ተሞርኩዞ ነዉ። እና ወቅታዊዉ የፊልም ሥራም ስለጦርነት ነዉ።»  

በበርሊናለ የፊልም መድረክ «Berlinale Africa Hub” የአፍሪቃ መድረክ በሚል ርዕስ የተከፈተዉና በጀርመን የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሚደገፈዉ ይህ ፕሮጀክት በተለይ ከሰሃራ በታች ባሉ ሃገራት የሚሰሩ ፊልሞችን  አዲስ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ያስተዋዉቃል። ተሰጥኦ ያላቸዉን አፍሪቃዉያን የፊልም ሥራ አዋቂዎችን ድጋፍ ይሰጣል። ድጋፍን በተመለከተ በበርሊናለ የፊልም ፊስቲቫል ላይ የተገኘችዉ ኬንያዊት የፊልም ሥራ አዋቂ ከመንግሥት ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ተናግራለች።

በርሊናለ አፍሪካ ሁብ የተሰኘዉ ለአፍሪቃ ፊልም ኢንዱስትሪ መድረክን ዳይሬክተር ማትያስ ቮተር ክኖል እንደገለፁት መድረኩ በተለይ ለአፍሪቃዉያኑ ወጣቶች ጠቃሚ ነዉ።    

«አፍሪቃ ዉስጥ በርካታ ወጣት እንደሚገኘዉ በየትኛዉም የዓለም ክፍል አይገኝም። በርካታዉና 30 ዓመት በታች የሆነዉ የአፍሪቃ ወጣት የዓለምን እንቅስቃሴ የዓለምን ዉሎ በየጊዜዉ ለመከታተል የተንቀሳቃሽ ስልክን ይዞ ነዉ የሚታየዉ። በዚህም ምክንያት ባለፉት የመጨረሻ ዓመታት ላይ በርካታ ነገሮች ተለዋዉጠዋል። ይህ ለዉጥ በአዉሮጳ የፊልም ሽያጭ መድረክ ላይም ታይቶአል። በርካታ ወጣት ጠንካራና በርካታ ተለምዶን ያካበቱ ወጣት አፍሪቃዉያን የፊልም ሥራ አዋቂዎች በዚህ የፊልም ገበያ ላይ ተገኝተዋል። ከጀርመን የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር በኩል በዚህ ዓመት ከፍተኛ ተነሳሽነትና ድጋፍ ተገኝቶአል፤ ስለዚህ ዉጤቱ ምን እንደሚያስገኝ ለማወቅ ጓጉቻለሁ።»  

ከጀርመናዉያን የፊልም ሥራ አዋቂዎች ጋር በተለያዩ ጊዜያት ልምድን የቀሰመዉና በጎርጎረሳዊዉ 2015 ዓ.ም በተዘጋጀዉ በ 65 ኛዉ የበርሊኑ የዓለም አቀፍ የፊልም መድረክ «በርሊናለ» ላይ ኒሻን የተሰኘዉን ፊልሙ እንዲቀርብ ጥረት ተደርጎ እንደነበር የነገረን ወጣቱ የፊልም ስራ ባለሞያ እንዳልካቸዉ ሹመቴ በበርሊናለ የዓለም አቀፍ መድረክ በአካል ተገኝቶ ባያዉቅም በርሊናለን አስታኮ በሚዘጋጁ የፊልም አዉደጥናቶች ላይ ግን ተካፍሎአል። 

ወጣት እንዳልካቸዉ እዚህ ራድዮ ጣብያችን አጠገብ በምትገኘዉ ታዋቂ ከተማ ኮለኝ  በየዓመቱ በሚዘጋጀዉ የአፍሪቃ ፊልም ፊስቲቫል ላይ ኒሻን የተሰኘዉን ፊልሙን ለእይታ ቀርቦ ነበር። ወጣቱ የፊልም ስራ አዋቂ እንዳልካቸዉ ሹመቴ ለመጀመርያ ጊዜ ወደ ጀርመን የመጣዉም ኒሻን ይዞ ነበር። ሌላዉ ከጀርመናዉያን የፊልም ስራ አዋቂዎች ጋር ሰፋ ያለ የሞያ ልምድ ያለዉ የፊልም ሥራ አዋቂና የሥነ-ጥበብ ባለሞያ ወጣት እዝራ ዉቤ በኒዮርክ በፊልም ይማራል ያስተምራልም። ከዝያዉ ከሚኖርበት ከዩዜስ አሜሪካ ከኒዮርክ ወደ ከሥነ-ጥበብ ጋር የተሰራዉን «ሂሳብ» የተሰኘዉን ፊልሙን ይዞ እዚህ ጀርመን ዉስጥ በተደረገ የፊልም ፊስቲቫል ላይ ተካፍሎም ነበር። 

Berlinale | Eröffnungsgala und Filmpremiere "Django" | Emilia Schuele
ምስል Getty Images/AFP/J. MacDougall

ባገኘዉ አጋጣሚ ከጀርመናዉያን የፊልም ሥራ ባለሞያዎች ጋር በመገናኘት ብዙ የስራ ልምድን እንዳገኘ የገለፀልን ወጣት እንዳልካቸዉ አስመላሽ የጀርመናዉያንን የሥራ ትጋት ያደንቃል። እናም ይላል ወጣት እንዳልካቸዉ በመጨረሻ ሲኒማ ሞያ የተለያዩ መሠናክሎች ቢኖሩም ኢትዮጵያዉያን ገና ብዙ መሥራት ይጠበቅብናል።

ለ67 ኛ ጊዜ እየተካሄደ ያለዉ የጀርመኑ ዓለም አቀፍ የፊልም ፊስቲቫል «በርሊናለ» የፊታችን እሁድ ለምርጥ ፊልማ ለፊልም ሰራተኛ ለፊልም ተዋናይ የወርቅና የብር ሽልማትን በመስጠት የፊታችን እሁድ ይዘናቀቃል። የጀርመኑ በርሊናለ ፊስቲቫል የድብ ምስልን ይታወቃል። በበርሊኑ ዓለም አቀፍ የፊልም ፊስቲቫል ላይ ሥራቸዉን ለማቅረብ ጥረት በማድረግ ላይ የሚገኙትን ኢትዮጵያዉያን የፊልም ሥራ አዋቂዎች ጥረታቸዉ እንዲሳካ ምኞታችን በመግለፅ ቃለ-ምልልስ የሰጡንን በማመስገን ሙሉ ቅንብሩን የድምፅ ማዕቀፉን በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን።

 አዜብ ታደሰ

አርያም ተክሌ