የዓለም ምግብ ፕሮግራም ጀርመን ለኢትዮጵያ ድንገተኛ አደጋ 8.5 ሚሊዮን ይሮ መለገስዋን አወደሰ
ማክሰኞ፣ ሰኔ 1 2013የተባበሩት መንግስታት የዓለም ምግብ መርኃ ግብር (WFP) ከጀርመን ሕዝብ 8.5 ሚሊዮን ዩሮ በኢትዮጵያ በግጭት እና በአየር ንብረት ለውጥ የተጎዱ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ሕይወት ለመታደግ ያደረገዉን መዋጮ አወደሰ። የተጠቀሰዉ ገንዘብ ከጎርጎረሳዉያኑ 2021 እስከ 2023 ዓ.ም ድረስ የሚሰጥ ሲሆን ድጋፉ ጀርመን ለምስራቅ አፍሪቃ ቀጠና በምታደርገዉ የገንዘብ ድጋፍ አካል ዉስጥ የተካተተ ነዉ። ይህ ከጀርመን ሕዝብ የተገኘዉ ርዳታ በትግራይ የዓለሙ የምግብ መርኃ ግብር «WFP» የአስቸኳይ የምግብ እና የተመጣጠነ ምግብ ከሚሰጠዉ ድጋፍ ጋር የተያያዘ ነዉ። ልገሳዉ እስከ 2.1 ሚሊዮን ሕዝብ የአስቸኳይ ጊዜ ርዳታ ምላሽን ለመስጠት አስተዋፅዖ ያደርጋል ተብሎሏል። በትግራይ በአጠቃላይ 5.2 ሚሊዮን ሕዝብ ወይም ከጠቅላላው የትግራይ ሕዝብ 91 በመቶ የሚሆነው አካባቢዉ ላይ በሚታየዉ ግጭትና ጦርነት ምክንያት አስቸኳይ የምግብ ርዳታን ፈላጊ ነዉ።
ልገሳዉ በተጨማሪ በሀገሪቱ የዓለም ምግብ መርኃ ግብር (WFP) ለስደተኞች በሚሰጠዉ ርዳታ እና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ውስጥ በከፍተኛ የአየር ንብረት መዛባት ለተጎዱ ማኅህበረሰቦች ሕይወት አድን እና ሕይወትን የሚቀይር የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ ርዳታን ለማድረስ ያለመ ነዉ።
«ይህ የጀርመን ሕዝብ ወቅታዊ የሆነ ርዳታ በመላ ኢትዮጵያ በጣም አስቸኳይ የሰብዓዊ ርዳታ ለሚያስፈልጋቸዉ ማኅበረሰቦች ምላሽ ለመስጠት ያስችለናል» ሲሉ በኢትዮጵያ የ «WFP» ተወካይ እና የሀገሪቱ ዳይሬክተር ዶ / ር ስቴቨን ዌር ኦማሞ አመስግነዋል።
«WFP ከጀርመን ፌዴራላዊ ሪፐብሊክ ጋር በነበረው የቆየ አጋርነት እጅግ በጣም የሚያኮራ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ የምግብ ዋስትናን ለማሻሻል እና በምግብ እጦት ተጋላጭ ለሆኑ ማህበረሰቦች ምግብ እንዲያገኙ ለማድረግ ብሎም የምግብ ዋስትና እንዲኖራቸዉ እና በራሳቸዉ መቆም እንዲችሉ ከእኛ ጋር አብሮን በመስራት ላሳየን ቁርጠኝነት በጣም እናመሰግናለን» ሲሉ ዶ / ር ስቴቨን ዌር ኦማሞ አክለዋል።
ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር እስቴፋን አውር በአዳማ የሚገኙትን የ «WFP» የእህል መጋዘኖችን እና ጽ / ቤቶችን ጎብኝተዋል። አምባሳደሩ የአስቸኳይ የምግብ ርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ማህበረሰቦች የሚላከዉንም ምግብም ተመልክተዋል። በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር እስቴፋን አውር «WFP» በመላ አገሪቱ የነፍስ አድን ድጋፍ አሰረጫጨት እንዴትነትን ከድርጅቱ ሠራተኞች አዳምጠዋል።
«የ WFP ሥራ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ አሁን እጅግ አስፈላጊ ነው ያሉት በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር እስቴፋን አውር፤ ጀርመን የዓለሙ የምግብ መርኃ ግብር «WFP» በኢትዮጵያ እና ከዚያ ባሻገር በዓለም ዙሪያ የድርጅቱ ሁለተኛ ለጋሽ ሃገር በመሆኗ ኩራት ይሰማታል» ሲሉም ተናግረዋል።
የገንዘብ ድጋፍ እጥረት ላለበት «WFP» የጀርመን ያሰጠችዉ ይህ ልገሳ የተገኘዉ ወሳኝ በሆነ ወቅት ነዉ። የዓለም የምግብ ድርጅት «WFP» እስከ ዓመቱ መጨረሻ ድረስ በትግራይ ክልል ርዳታዉን ለማዳረስ 203 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ያስፈልገዋል። ከዚህ በተጨማሪ በሚቀጥሉት ስድስት ወራት በሶማሌ ክልል የሚደረገውን የምግብ ርዳታ ሥራ ለማካሄድ ተጨማሪ 97 ሚሊዮን ዶላር ይፈልጋል።
አዜብ ታደሰ
ማንተጋፍቶት ስለሺ