1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ውዝግቦችአፍሪቃ

በኦሮሚያ ክልል ለሰላም ጥሪ የቀረበባቸው ሰልፎች

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 14 2017

ኦሮሚያ ክልል ከሰሞኑ የተጀመረው ሰላማዊ ሰልፍ ዛሬም በተለያዩ ዞኖች ተካሂዷል። በጎጂ ዞን በተለያዩ ወረዳዎች እና ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዛሬ ሰላማዊ ሰልፉ ከተካሄደባቸው አካባቢዎች ተጠቃሽ ነው።

https://p.dw.com/p/4oWfc
ኦሮሚያ ክልል
የኦሮሚያ ክልል መልክአ ምድር በከፊል ፎቶ ከማኅደርምስል Seyoum Getu/DW

ለሰላም ጥሪ የቀረበባቸው ሰልፎች

 

ታጣቂዎች በስፋት በሚንቀሳቀሱበት የጉጂ ዞን  ሰልፍ

ከባለፈው ቅዳሜ ጀምሮ ትናንት በምዕራብ ጉጂ ምሥራቅ ሸዋ መታሃራ እና ሌሎችም አካባቢዎች መካሄድ የጀመረው ስለሰላም የተጣራው ሰላማዊ ሰልፉ ዛሬም ቀጥሎ ከተካሄደባቸው አካባቢዎች አንዱ ጉጂ ዞን ነው። ዛሬ በዞኑ ዋደራ እና ሰባቦሩ ወረዳዎች ሲካሄድ የዋለው ሰልፍም ተመሳሳይ መልእክቶች ማስተጋባቱን አንዲት የዋደራ ወረዳ ነዋሪ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል፡፡

አስተያየት ሰጪዋ ሰልፈኞቹ በዋናነት ያነገቡትን መልእት ስያስረዱ፤ «ሰልፈኞቹ በመልእክታቸው ያው በሰላም ዙሪያ ስለተቸገርን መታጠቅ ያለበት አንድ የመንግሥት ኃይል ብቻ ሊሆን ይገባል በሚል ያው ጦርነት ይቁም የሚል ነው ዋና መልእክቱ» ነው ያሉት። ከከዚህ በፊቶቹ የሰላም ጥሪ ውጤት መገኘቱን የሚስረዱት አስተያየት ሰጪዋ በጎሮዶላ፣ ዋደራ እና ነገሌ ከሰሞኑ እንኳ ከጫካ የተመለሱ በርካታ ታጣቂዎች መኖራቸውን አስረድተዋል።

በምሥራቅ ሸዋ ዞን መታሃራ ከተማ በተደረገው ሰልፍ የተሳተፉ አስተያየት ሰጪ እንዳሉትም፤ «ጫካ ያሉ ወንድሞቻችን እንደሌሎች አካባቢዎች እንዲገቡ ነው የሰላም ጥሪው የተላለፈው።»

አንጻራዊ መረጋጋት ተገኝቶበታል የተባለው ምዕራብ ሸዋ

በተደጋጋሚ የታጣቂዎች ጥቃት ክፉኛ ሲፈተኑ ከነበሩ አካባቢዎች አንዱ በሆነው ምዕራብ ሸዋም ተደጋጋሚ ሰልፎች ባለፉት ጊዜያት ተደርጓል። ከዞኑ ባኮ ወረዳ አስተያየታቸውን የሰጡን ነዋሪ አሁን አሁን ለውጦችን እየተመለከቱ መሆኑን ይናገራሉ። «አሁን መልካም ነው ምንም አይልም። ከዚህ አካባቢ ብዙ ታጣቂዎች ወደ ሰላም ቢመለሱም ወደ ላይ ወደ ጅባት ስላሳለፏቸው በቁጥር እንኳ ለመግለጽ ትንሽ ይከብዳል። ታጣቂዎቹ በብዛት ጫካውን ለቀው ከወጡ በኋላ ለውጥ ግን አለ።»

ዛሬም ሰላምን ናፍቆ ያላገኘው የሰላሌ ሕዝብ

ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪ በተደረገበትና ከፍተኛ ትኩረትን ስቦ በነበረው ሰሜን ሸዋ ዞን (ሰላሌ) ተደጋጋሚ ሰላማዊ ሰልፉ ባይቋረጥም፤ ጥሪው ግን አመርቂ ውጤት አለማምጣቱን ነው ነዋሪዎች የሚገልጹት። አስተያየታቸውን የሰጡን የደብረጽጌ ከተማ ነዋሪ፤« እንዴት እንደሆነ ግራ የሚገባ ነው። ይሄ ጦር የኦሮሞን ሕግ ባህል የሚውቅ ነው። እንዴት እንደሆነ ግራ የሚገባ ነው» በማለት፤ ጦርነቱ በሰላሌ እንኳን ሊቆም ብሶበት ቀጥሏል ብለዋል። በአካባቢው ሰው እየተዘረፈ እየተገደለም እንደሆነ ያስረዱት አስተያየት ሰጪዋ፤ የአካባቢው ነዋሪ ሰላም ቢለመንለትና ቢማለድለት እንደሚፈልግ ተናግረዋል።  

በዛሬው ዕለት ስለሰላም ጥሪ ያቀረቡ ሰልፎች በምሥራቅ ወለጋ እና ሆሮጉዱሩ ወለጋ ዞኖችም በተለያዩ ወረዳዎች ተካሂደዋል።  በቅርቡ በቁጥር በርከት ያሉ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ታጣቂዎች ትጥቃቸውን እንዳነገቡ ከመንግሥት ጋር እርቅ ማውረዳቸውን ተከትሎ በርካታ ስፍራዎች ላይ እፎይታ መገኘቱን መንግሥት ያስረዳል። የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ከፍተኛ አመራሮች በፊናቸው መንግሥት በተናጠል እያደረገ ያለው ድርድር ላይ ውኃ በመቸለስ ወደ እርቁ እየተመለሱ የሚገኙት ታጣቂዎጥ ሠራዊቱን አይወክሉም ሲሉ በተደጋጋሚ ገልጸዋል። መንግሥት ከታጣቂዎቹ ጋር ከተናጠል ይልቅ አጠቃላይ ከሠራዊቱ ጋር በመወያየት ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ የሚወተውቱም ጥቂት አይደሉም።

ሥዩም ጌቱ

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ