ምያንማር ውስጥ ለፈተና የተዳረጉት ኢትዮጵያውያን ጉዳይ
ዓርብ፣ ኅዳር 27 2017እነዚህ ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ዜጎች «በሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች» ተታለው መሄዳቸውን የሚገልፀው የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር «ለችግር የተጋለጡ ዜጎችን ለማስለቀቅ ጃፓን የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከምያንማር የውጭ ጉዳይ እና የሀገር ውስጥ ሚኒስቴሮች ጋር የበይነ መረብ ስብሰባ» ማድረጉን አስታውቋል።
በጉዳዩ ላይ የተገኘ ለውጥ ይኖር ይሆን?
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ባልተለመደ ሁኔታ ወደ ደቡብ - ምሥራቅ እስያዋ ምያንማር ለተሻለ ሥራ በሚል ከምያንማር- ታይላንድ አዲስ አበባ በተዘረጋ የሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር መረብ ውስጥ እየገቡ ያሉት ኢትዮጵያውያን አንድም ወጣቶች፣ በሌላ በኩል ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተምረው የወጡ፣ በሥራም ተሰማርተው የነበሩ ዜጎች ናቸው። ወይዘሮ አበበች ሽመልስ ወንድ ልጃቸው ወደዚህች ሀገር ሆዶ የገጠመውን ችግር ከዚህ በፊት ገልፀው እኛም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን ደጋግመን ጠይቀን ነበር። ምን ያገኛችሁት አዲስ ለውጥ አለ በሚል ዛሬ ጠይቀናቸዋል።
«አሁን ለውጥ ተብሎ ብዙም የሚቆጠር ነገር የለም።» ብለዋል።
የሌሎች ሃገራት ዜጎች ከአስከፊው እገታ እየወጡ ነው
እነዚህ ኢትዮጵያዊያን በደላሎች እየተጭበረበሩ የአውሮፕላን ቲኬት ተቆርጦላቸው፣ ሕጋዊ ተጓዥ ሆነው ታይላንድ ይገባሉ። ከዚያም ወደ ምያንማር። የአክስቷ ልጅ ከዩኒቨርሲቲ ወጥቶ ሥራ ባለማግኘቱ ወደዚህች ሀገር መሄዱን የምትናገረው እህት ቤተሰቧ «በጣም የከፋ ነገር ውስጥ» መግባቱን፣ እዚያ ከመካከላቸው አስገድደው በቀን እስከ 18 ሰዓት ከሚያሰሯቸው መካከል የሌሎች ሃገራት ዜጎች እየወጡ ስለመሆኑ እንደገለፀላት ተናግራለች።
የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለጉዳዩ መፍትሔ ለመስጠት «ክትትል እና ጥረት እየተደረገ» መሆኑን ከዚህ በፊት አስታውቆ ነበር። ሆኖም ባለው ዳተኝነት ምክንያት ኢትዮጵያዊያኑ እስካሁን ከገቡበት ያልታሰበ አደጋ ሊወጡ እንዳልቻሉም ትገልፃለች።
«ትንሽ የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ ቢጀመር ያን ያህል ከባድ ነው ብየ አላምንም። ለምን በመሥሪያ ቤቶቹ በኩል ዳተኝነት እንዳለ አይገባኝም»። በማለትም ሃሳቧን አካፍላናለች።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ምላሽ
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል ዐቀባይ አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው ጃፓን የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከምያንማር መንግሥት ጋር ንግግር መጀመሩን ትናንት አስታውቀዋል።
«በሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ተታልለው ወደ ምያንማር የገቡ እና ለችግር የተጋለጡ ዜጎቻችንን ለማስለቀቅ ከምያንማር መንግሥት ጋር ጃፓን የሚገኘው ኤምባሲያችን የበይነ መረብ ስብሰባዎች አካሂዷል»።
ጉዳዩ ተገቢውን ትኩረት እንዲያገኝ ተጠይቋል
ወላጆች እና የእነዚህ ዜጎች ቤተሰቦች የሀገሪቱ ከፍተኛው የአስፈፃሚ አካል - የሚኒስትሮች ምክር ቤት ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጠው ጠይቀዋል። በጃፓን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከምያንማር መንግሥት ጋር ንግግር መጀመሩን እና ጉዳዩ በመገናኛ ብዙኃን ትኩረት መሳቡን ተከትሎ «በተወሰነ መጠን በፊት ልጆች ላይ ይደርስ የነበረው ግርፋት እና የከፉ እንግልቶች መቀነስ እንዳሳዩ» ወይዘሮ አበበች ገልፀዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ስደተኞችን መርዳት አልቻለም
እንዲያም ሆኖ ግን አሁንም ከከባባድ የሥራ ቅጣት ሙሉ በሙሉ አለመውጣታቸውን፣ በዚህ ምክንያት ከመካከላቸው የኩላሊት መድከም ችግር የደረሰባቸው እንዳሉ፣ ሴቶች ላይ ፆታዊ ጥቃት እንደሚደርስባቸው መስማታቸውን ገልፀዋል።
ኢትዮጵያዊያኑ ለተሻለ ሥራ ተብለው ወደ ምያንማር ተወስደው በተለያዩ ድርጅቶች ውስጥ ገብተው ሌላ ሕገ ወጥ የገንዘብ ምዝበራ እና መሰል ድርጊቶች ውስጥ ተገደው እንደሚሳተፉ ተደጋግሞ ተገልጿል።
በጉዳዩ ላይ ይመለከታቸዋል የተባሉ አንድ የአካባቢው የተበበሩት መንግሥታት የሥራ ባልደረባ ዴቼ ቬለ ላቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ «የመንግሥታቱ ድርጅት ምያንማር ውስጥ የሚገኙ ስደተኞችን ለመርዳት መግባት እንዳልቻለ» ገልፀው ሆኖም በጉዳዩ ላይ በቀጣይ ምላሽ ለመስጠት እንደሚጥሩ ተናግረዋል።
ሰሎሞን ሙጬ
ሸዋዬ ለገሠ
አዜብ ታደሰ