1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሩጫ እና ስኬት

ልደት አበበ
ዓርብ፣ የካቲት 15 2016

ከሁለት ሳምንት ገደማ በፊት በፈረንሳይ ሊቫ በተለያዩ ርቀቶች በተካሄዱ የቤት ውስጥ የሩጫ ውድድሮች ኢትዮጵያውያን አሸናፊ ሆነዋል። ከእነዚህ አሸናፊ አትሎቶች መካከል ሁለቱ የዛሬው የወጣቶች ዓለም ዝግጅት እንግዶቻችን ናቸው።

https://p.dw.com/p/4ckvl
አትሌት ሂሩት መሸሻ
አትሌት ሂሩት መሸሻ እጎአ ሐምሌ 16 ቀን 2023 ዓ ም ፖላንድ በተካሄደው የዲያመንድ ሊግ ውድድር በ 1500 ሜትር ሩጫ አሸናፊ ሆናለች።ምስል Artur Widak/NurPhoto/IMAGO

የ3000 ሜትር አሸናፊዎቹ ሂሩት እና ሰለሞን

 በፈረንሳይ ሊቫ ከተማ በተካሄዱ የቤት ውስጥ የሩጫ ውድድሮች ኢትዮጵያውያን በርካታ አትሌቶች አሸናፊ መሆናቸውን ሰምታችሁ ይሆናል። በተለይ በ3000 ሜትር የወንዶችና በ1500 ሜትር  የሴቶች የሩጫ ውድድሮች ድሉ የኢትዮጵያውያን ብቻ ነበር። በጠቅላላው ዘጠኝ ኢትዮጵያውያን ከአንድ እስከ ሶስት ያለውን ቦታ ተቆጣጥረዋል። ከእነዚህ መካከል አትሌት ሂሩት መሸሻ እና አትሌት ሰለሞን ባረጋ ይገኙበታል። 

አትሌት ሂሩት መሸሻ በፈረንሳይ ሊቫ ከሁለት ሳምንት ገደማ በፊት በተካሄው የ3000 ሜትር የቤት ውስጥ የሩጫ ውድድር ሁለተኛ በመሆን አሸንፋለች። ውጤቱ « ጥሩ እና በጣም የተደሰትኩበት» ነበር የምትለው ሂሩት ለዚህም ውድድር በደንብ እንደተዘጋጀች እና በቂ ጊዜ እንደነበራት ገልፃልናለች። «3000 ሜትር ስሮጥ ደግሞ የመጀመሪያዬ ነበር። ለመሞከር ነበር የገባሁት። እና ጥሩ ሰዓት ስለሮጥኩ ደስ ብሎኛል» ስትል ደስታዋን ትገልፃለች። ጉዳፍ ጸጋይ 1ኛ በመሆን አሸንፋለች በድል የተመለሰው የአትሌቶች ቡድን አቀባበል


ሂሩት ርቀቱን ለማጠናቀቅ የወሰደባት ጊዜ 8 ደቂቃ ከ 29 ሰከንድ ነው። በ3000 ሜትር ልምዱ የሌላት ሂሩት ይህ ስኬቷ ወደፊት በሌሎች መሰል ውድድሮች እንድትሳሰፍ ብርታት ሆኗታል። ከዚህ ቀደም በብዛት ትካፈልባቸው የነበሩት ውድድሮች 1500 ሜትር ነበሩ።  «  ለሶስት  ወይም  አራት ዓመታት ያህል 1500 እሮጫለሁ። ሰዓቶቼን እያሻሻልኩ ነው የቆየሁት። 3000 ከ 1500 ይሻላል። ምክንያቱም 1500 ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ፈጣን ነው። »

የሊቫን ውድድር ለየት የሚያደርገው


አትሌት ሰለሞን ባረጋ በአንፃፉ ለ 3000 ሜትር ውድድር አዲስ አይደለም። ሊቫ የተካሄደውን ውድድር  ግን የተለየ የሚያደርገው አንድ ነገር አለ። የ24 ዓመቱ ወጣት የወርቅ ተሸላሚ መሆኑ ብቻ ሳይሆን  ርቀቱን ለማጠናቀቅ የወሰደበት ጊዜ ነው።  7 ደቂቃ ከ31 ሰከንድ ። « ከሌላ ጊዜ የተሻለ ጊዜ በመሮጥ ነው ዘንድሮ የጀመርኩት። መጀመሪያ ፖላንድ ነው የሮጥኩት ከዛ በኋላ በአራት ቀናት ልዩነት ወደ ፈረንሳይ ሄድኩ። ሁለቱንም አሸነፍኩ። በጣም ደስ የሚል እና ካቀድኩት አንዱ ነበር እና አሳክቸዋለሁ» ይላል። ፖላንድ የሮጠውም 3000 ሜትር ነው።

አትሌት ሰለሞን ባረጋ
አትሌት ሰለሞን ባረጋ ጃፓን ቶኪዮ ላይ እጎአ 2021 ዓ ም በ 10000 ሜትር አሸናፊ ነበርምስል Charlie Riedel/AP Photo/picture alliance

ትምህርት ቤት የጀመረ ስኬት

አትሌት ሂሩት መሸሻ 22 ዓመቷ ነው። ተወልዳ ያደገችው ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ በምትገኘው ቦንጋ ከተማ ነው። ጉብዝናዋም የታወቀው ገና ታዳጊ ወጣት እያለች ነው።

«ሩጫ የጀመርኩት ትምህርት ቤት ሳለሁ ነው። ከዛ ወደ ሐዋሳ መጣሁ። ማጣሪያ ወስጄ ወደ ማሰልጠኛ ገባሁ። እዛ አራት አመት ከቆየሁ በኋላ ወደ ክለብ ተቀላቀልኩ። 2009 ላይ ነው ወደ ውጤት መምጣት የጀመርኩት። »  ከዛን ጊዜም አንስቶ ሂሩት የተለያዩ ውድድሮችን ለማሸነፍ ችላለች። « 2017 ናይሮቢ በተደረገው ውድድር እዛ ነው ለመጀመሪያ ጊዜ ከሀገር ወጥቼ የተወዳደርኩት። ከዛን ጊዜ አንስቶ ከሜዳሊያ ወጥቼ አላውቅም። ብዙ ነው ለሀገሬ ሜዳሊያ ያስገኘሁት። ትልቁ ውድድር ብዬ የምለው ደግሞ 2022 ዓ ም በቤት ውስጥ ሩጫ ያገኘሁት ነው። »

አትሌት ሰለሞን ባረጋም በልጅነቱ ነው መሮጥ የጀመረው። ይህም ደቡብ ክልል ጉራጌ ዞን  በሚገኘው ቋንጤ ትምህርት ቤት ውስጥ። « በስፖርት ትምህርት ማርክ ለማግኘት ስንሮጥ ጥሩ ነጥብ አገኘሁ። ከዛ ክፍሌን በመወከል፣ ከዛ ትምህርት ቤቴን በመወከል፣ ቀጥሎ ደግሞ ወረዳውን በመወከል ወደ ዞን ሄድኩ። ከዛ በኋላ ነው ወደ ሩጫ የገባሁት። ቤተሰብም ወደ ትምህርቱ እንዳተኩር ነበር የሚፈልገው እና ፍቃደኛ አልነበረም። ሜዳሊያ ይዤ ስመጣ ነው ሀሳባቸውን የቀየሩት» ዛሬ አትሌት ሰለሞን ወላጆቹን ብቻ ሳይሆን የሀገሩን ዜጎችም በተደጋጋሚ ማኩራት ችሏል።   እሱስ በራሱ እና በሯጭነቱ የኮራበት ጊዜ መቼ ይሆን? « ቶኪዮ ኦሎምፒክ ሳሸንፍ እና ለመጀመሪያ ጊዜ ሀገሬን ወክዬ የአለም ወጣቶች ሻምፒዮና ሀገሬን ወክዬ ወርቅ ያገኘሁበት ናቸው።» ይላል። ቀጣዩ ውድድር በመጋቢት ወር ዩናይትድ ኪንግደም ይሆናል።

በአጭር ጊዜ ውስጥ በተለያዩ ውድድሮች መካፈል አድካሚ አይሆንም?  

ሰለሞን የሚካፈልባቸውን ውድድሮች በሙሉ አስቀድሞ ከአሰልጣኙ ጋር እንደሚማከር ገልፆልናል። «ብዙ አትሌቶች ስላሉን ነገ ሄዶ አንዱ የተሻለ ሰዓት ስለሚሮጥ ሰዓታችንን ለማስጠበቅ ብለን ነው በተደጋጋሚ የምንወዳደረው እንጂ በአለም ሻምፒዮና እና ኦሎምፒክ ወቅት ብዙ ውድድሮች አንድ አትሌት ባይወዳደር የተሻለ ነው ብዬ አስባለሁ።« ይላል።

በፈረንሳዩ ሩጫ ለምሳሌ በተለያዩ ርቀቶች በርካታ ኢትዮጵያውያን ተወዳዳሪ ሆነው ቀርበዋል። ተከታትለው በመግባትም አሸናፊ ሆነዋል። ሰለሞን ከሀገሩ ልጆች ጋር በአንድ ውድድር መሳተፍ በአንድ በኩል የሀገራቸውን ስም ለማስጠራት በጋራ ለመስራት ብርታት እንደሚሆናቸው ይናገራል። ሌላው ደግሞ ዕርስ በራሳቸው የሚያደርጉት ፉክክር ጥንካሬ ነው ይላል።  «ውጤታማ የምንሆነውም  ለዛ ይመስለኛል።»

በፓሪስ ኦሎምፒክ የሚሳተፉ የኢትዮጵያ አትሌቶች በፈረንሳይ የሚለማመዱበት ቅድመ ሥምምነት ተፈረመ


አትሌት ሂሩት ባለ ትዳር ስትሆን አሰልጣኟ ደግሞ ባለቤቷ እንደሆነ ነግራናለች። ስኬታማ ለመሆን ብዙ ጥረት እና ልምምድ እንደሚጠይቅ የሂሩት ውሎ ስኬታማ ሯጭ  ለመሆን ለሚፈልጉ ወጣቶች ምሳሌ ሊሆን ይችላል። «ጠዋት መደበኛ ፕሮግራም ከሰራን ከሰዓት ደግሞ እሱን ለመበተን እንሮጣለን። በየቀኑ ፕሮግራሙ የተለያየ ነው። » የምትለው ሂሩት በብዛት ስፖርት ቤት ሄዳ እንደምትሰራ ገልፃልናለች። ከውድድር በኋላም አንድ ሁለት ቀናት ዕረፍት አድርገው ወዲያው ወደ ልምምድ ወይም ስልጠና እንደሚመለሱ ገልፃልናለች።

አትሌት ሂሩት መሸሻ
አትሌት ሂሩት መሸሻ በ 1500 ሜትር ውድድር ቡዳፔስት ላይ እጎአ 2023 ስታሸንፍምስል Chai v.d. Laage/IMAGO

መሮጥ ለሚወዱ ወጣቶች የአትሌቶች ምክር

« ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ በርትተው ከሰሩ የማይደረስበት ነገር የለም» ትላለች ሂሩት። አትሌት ሰለሞንም የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ በቀን ሁለት ጊዜ ይለማመዳል። «ዕረፍት ያለኝ እሁድ ብቻ ነው» ይላል። እሱም ለሌሎች ወጣቶች የሚያክለው አለ። « በስፖርቱ ዓለም ላለ ሰው ብቻ ሳይሆን የትኛውም ስራ ላይ ያለ ሰው በተሰማራበት ሙያ ጠንክሮ ከሰራ ውጤታማ እንደሚሆን ፣ ነገ የተሻለ ቦታ እንደሚደርስ አምኖ አሳካዋለሁ ብሎ ለአዕምሮው መንገር አለበት።» ይላል ሰለሞን።  ወደፊት  5000 ሜትር ውድድሮች ላይ አተኩሮ መስራት ይፈልጋል።  ሂሩት ከ 3000 ሜትር ወደ 5000 ሜትር እያለች የተለያዩ ርቀቶችን የመሞከር ሃሳብ አላት።  

ልደት አበበ

ኂሩት መለሰ