በሰብአዊ መብት ላይ የሚሠሩ ሁለት ሲቪክ ድርጅቶች ታገዱ
ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 17 2017ሰብአዊ መብት ላይ የሚሠሩ ሁለት ሲቪክ ድርጅቶች ታገዱ
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባዔ ( ኢሰመጉ ) እና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል መታገዳቸው ተገለፀ።
ከሦስት አሥርት ዓመታት በላይ በሰብአዊ መብት ላይ ሲሠራ የቆየው የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ ድርጅት- ኢሰመጉ ትናንት ስለመታገዱ ደብዳቤ እንደደረሰው ዶቼ ቬለ አረጋግጧል።
በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል "ከተቋቋመበት ዓላማ ውጪ መንቀሳቀሱ፣ ገለልተኛ አለመሆኑ፣ ግልጽ የሆነ የአደረጃጀት መዋቅር የሌለው እና ኃላፊነት በጎደለው መልኩ የተንቀሳቀሰ" መሆኑ ተጠቅሶ እግድ እንደተጣለበት ድርጅቱ ለዴቼ ቬለ ገልጿል።
ይህንን እርምጃ የወሰደው የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጠን የመብቶች እና ዲሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (ካርድ) እና የሕግ ባለሙያዎች ለሰብዓዊ መብቶች የተባሉ ሀገር በቀል ሲቪል ድርጅቶችንም ከዚህ ቀደም ማገዱ ይታወቃል።
እያነጋገረ ያለው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ረቂቅ ማሻሻያ አዋጅ
ለሲቪክ ድርጅቶቹ መታገድ የተሰጡ ምክንያቶች
በ1984 ዓ.ም ተመሥርቶ ዳግም በ2011 ዓ.ም ተመዝግቦ እየተንቀሳቀሰ ያለው መንግሥታዊ ያልሆነው የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት - ኢሰመጉ በኢትዮጵያ ለዴሞክራሲ ሥርዓት መጎልበት፣ ለሕግ የበላይነት መስፈን እና ለሰብዓዊ መብቶች መከበር የበኩሉን ለማገዝ ስለመቋቋሙ ይገልጻል።
ስለ እግዱ የተሰጠው ምክንያት ምን እንደሆነ ከድርጅቱ ዝርዝር መረጃ ለማግኘት ባንችልም ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ጋር በታገደበት ጉዳይ ዙሪያ እየተነጋገረ ስለመሆኑ በዚህም ምክንያት ለጊዜው ለመገናኛ ብዙኃን መረጃ የመስጠቱ ተገቢነት አስፈላጊ እንዳልሆነ ማመኑን ለማወቅ ችለናል።
የአውሮፓ ኅብረት ለስምንት ኢትዮጵያዊያን የመብት ተሟጋቾች ሽልማት ሰጠ
ኢሰመጉ ባለፈው ሳምንት የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኪሚሽን የሰብአዊ መብት ተሟጋች ተቋማት እና ግለሰቦች ላይ ያጋጠሙ የመብት ጥሰቶችን እና ችግሮችን በተመለከተ አዲስ አበባ ውስጥ ባደረገው "ግልጽ ብሔራዊ ምርመራ" በተደጋጋሚ በተቋሙ ላይ ደረሰብኝ ያለውን ማዋከብ፣ ያልተገባ ክትትል እና ጫና በዝርዝር ያቀረበ ሲሆን፣ የተቋሙ የበላይ ኃላፊ የነበሩት አቶ ዳን ይርጋን ለስደት የዳረጋቸውን ሁኔታም በዝርዝር አቅርቦ ነበር።
ሌላኛው ትናንት በፈቃድ ሰጪው እና ተቆጣጣሪው የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን እግድ የተጣለበት ሀገር በቀል የሲቪክ ድርጅት የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል ሲሆን ለሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ጥበቃ ለማድረግ በሚል ነው ህዳር 2013 ዓ .ም የተመሠረተው። የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ያሬድ ኃይለማርያ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ባቀረባቸው ክሶች ላይ "በማስረጃ የተደገፈ ማብራሪያ እንዲሰጠን ዛሬ በደብዳቤ ጠይቀናል" ብለዋል።
የሰብአዊ መብት ድርጅቶች እና የኢትዮጵያ መንግሥት ፍጥጫ
"በትናንትናው ዕለት ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ተደውሎ ደብዳቤ እንድንወስድ ነው የተነገረን። በደብደቤውም ድርጅቱ እገዳ የተጣለበት መሆኑ ተነግሮናል"።
የቀረቡት ክሶች አይገልጹኝም - የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል "ከተመሠረተበት ጊዜ አንስቶ ከተቋቋመበት ዓላማ ውጪ በየትኛውም ያልተገባ ወይም ከሕግ የሚጻረር እንቅስቃሴ ላይ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ተሳትፎ የማያውቅ መሆኑን" ባወጣው መግለጫ ጠቅሷል። ሥራውንም "በገለልተኝነት፣ ኃላፊነት በተሞላው ጥንቃቄ" ሲያከናውን መቆየቱ ይታወቅልኝ ብሏል።
የቀረቡብኝ ክሶች "ግልጽ" አይደሉም ያለው የሲቪክ ድርጅቱ "ለማን ነው የወገንነው"? የሚለውም ግልጽ አይደለም ሲል እግዱ በአፋጣኝ ተቀልብሶ ወደ ሥራው እንዲመለስ እና በነፃነት የሚንቀሳቀስበት ሁኔታ እንደሚፈጠር እምነቱን ገልጧል። የቀረበበት የተቋማዊ አደረጃጀት ክስም ተገቢ እንዳልሆነ እና ተቋሙ በቦርድ የሚመራ፣ ሥራ አሥፈፃሚ ኮሚቴ እና የጽ/ቤት ኃላፊዎችም ያሉት ስለመሆኑ አቶ ያሬድ ኃይለማርያም ተናግረዋል።
"በቀጣይ ከባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ጋር የምናደርጋቸው ቀጣይ ውይይቶች ይኖራሉ። ግን አሳሳቢ ሁኔታ እንዳለ ማመላከቻ ነው"። ሲሉ ሲቪክ ምህዳሩ የገጠመውን ሁናቴ ገልፀዋል።
ከ60 በላይ የመብት ተሟጋቾች በኢትዮጵያ መንግስት ላይ
ሌሎች የሲቪክ ድርጅቶችም ቀደም ብሎ ታግደዋል
ሁለቱን የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ያገደው የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጠን ከሳምንታት በፊት የመብቶች እና ዲሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (ካርድ) እና የሕግ ባለሙያዎች ለሰብዓዊ መብቶች የተባሉ መሠል የመብት ተቆርቋሪነት ሥራ ላይ የተሰማሩ ሀገር በቀል ሲቪል ድርጅቶችንም ማገዱ ይታወቃል።
ሰለሞን ሙጬ
ታምራት ዲንሳ
ኂሩት መለሰ