የሱዳን የጦር ወንጀል ጉዳይ በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት
ቅዳሜ፣ ጥቅምት 10 2016ሱዳን ውስጥ ከ20 ዓመታት በፊት የተፈጸመ የጦር ወንጀል ለዓለም አቀፍ የጦር ወንጀል ተመልካች ፍርድ ቤት ቀርቧል። አሊ ሙሀመድ አሊ አብዲ አሊ ራህማን በ31 የጦር ወንጀል እና በሰብአዊነት ላይ በተፈጸመ ወንጀል ለቀረበበት ክስ በዴንሀግ ኔዘርላንድ በሚገኘው የዓለም አቀፍ የጦር ወንጀል ፍርድ ቤት ቀርቦ መልስ ይሰጣል። ከቀረበበት ክስ መካከል ሲቪሎች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት፤ አስገድዶ መድፈር እና ጅምላ ግድያ ይገኙበታል። ተጠርጣሪው የጃንጃዊድ ሚሊሺያ ከፍተኛ አመራር በነበረበት የጦር ወንጀሉን ከጎርጎሪዪሳዊው 2003 እስከ 2004 ባሉት ጊዜያት ዳርፉር ውስጥ ፈጽሟል ተብሏል። ጃንጃዊድ በዳርፉር የትጥቅ ትግል በተካሄደበት ወቅት በአፍሪካ ጎሳ አባላት እና በአማጽያን ላይ ጥቃት ያደረሰ የሚሊሺያ ቡድን ነው። የተመድ በጎርጎሪዮሳዊው 2008 ባወጣው መረጃ መሠረት ይኽ ታጣቂ ቡድን በዳርፉሩ ግጭት 300,000 ሰዎችን ፈጅቷል።
ክሱ የቀረበበት በቅጽል ስሙ አሊ ኩሸይብ በመባል የሚታወቀው አሊ መሀመድ አሊ አብዲ አል ራህማን ፤ ጥፋተኛ አይደለሁም ሲል ክሱን ተቃውሟል። ከአንድ ዓመት በፊት በመጋቢት ወር የአሊ ኩሸይብ ጠበቆች ደንበኛቸውን የተከላከሉበትን ምላሽ ለችሎት አቅርበዋል። በመከላከያቸውም ቡድኑ አልነበረም እንጂ ከነበረ አሊ የሚሊሺያው መሪ እንዳልነበር፤ እንደውም ተራ ሲቪል ዜጋ ነው በማለት የቀረበበትን ክስ አጣጥለዋል። እንደጠበቆቹ መከላከያ ከሆነ አሊ ኩሸይብ በጎርጎሪዮሳዊው 1990 ከወታደርነት ከተሰናበተ በኋላ መድኃኒት በመሸጥ ኑሮውን የሚገፋ ተራ ሰው ሆኗል። እናም በቀረበው መከላከያ መሠረት ከሆነ ተጠርጣሪው እሱ አይደለም ማለት ነው።
ዋና አቃቤ ሕግ ካሪም ካሀን ክሱን ባቀረቡበት የመክፈቻ ንግግር ግን ጉዳዩ እሱን እንደሚመለከት ግልጽ አድርገዋል። የዓይን እማኞች ተከሳሹን ተመልከተው እና ድምጹንም ሰምተው የተባለው ሰው እሱ መሆኑን ማረጋገጣቸውን፤ እማኞቹ አብዱራህማንን አስቀድመው እንደሚያውቁትም አብራርተዋል። በችሎቱ 56 እማኞችን በማስረጃነት አቅርበዋል፤ 600 ተጎጅዎችንም በምስክርነት ቆጥረዋል።
የዓለም አቀፉ የጦር ወንጀል ፍርድ ቤት ዋና አቃቤ ሕግ ስጋት
የዓለም አቀፉን የጦር ወንጀል ተመልካች ፍርድ ቤት ዋና አቃቤ ሕግ ያለፈው ብቻ ሳይሆን አሁን በሱዳን እየተፈጸመ የሚገኘው ጥፋት እንደሚያሳስባቸው ነው ያመለከቱት። ካሪም ካሀን ባለፈው ሐምሌ በተመድ የጸጥታው ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር ሱዳን ውስጥ የጦር ወንጀል ድርጊት እየቀጠለ መሄዱን አስታውቀዋል። ማንኛውም በሰብአዊነት ላይ ወንጀል የሚፈጽም፤ ባለው አቅም ተጽዕኖ አድርጎ የጦር ወንጀልም ሆነ የዘር ማጥፋት ቢፈጸም ምርመራ እንደሚካሄድበትም አጽንኦት ሰጥተዋል። ባለፈው ሚያዝያ ወር ነበር በሱዳን ጦር ኃይል መሪ ጀነራል አብደል ፈታህ አልቡርሀን እና በፈጥኖ ደራሹ ኃይል መሪ ጀነራል መሀመድ ሃምዳን ዳጋሎ መካከል ውጊያ የተቀሰቀሰው። ድርጊቱ ሀገሪቱን ወደሰብአዊ እልቂት እየገፋ እና የሰብአዊ መብቶች ጥሰትም እንዲባባስ እንዳደረገ እየተገለጸ ነው። በጉዳዩ ላይ ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸው በዓለም አቀፉ የመብት ተሟጋች የሂውማን ራይትስ ዎች የሰብአዊ መብቶች ባለሙያ ኤልስ ኬፕለር እንደሚሉት ዳርፉር ላይ ለተፈጸመው በተጠያቂነት የተያዘ አለመኖሩ አሁን ጥቃቱ ተባብሶ እንዲቀጥል አድርጎታል። እንዲህ ላለው ጥፋት ተጠያቂነትን ማስፈኑ ለሰለባዎች እጅግ አስፈላጊ እንደሆነም ነው የሚገልጹት።
ከተጠያቂዎቹ አብዛኞቹ ገና አልተያዙም
በዳርፉር የሴቶች የድርጊት ቡድን መሥራች የሆኑት ነኢማት አህመዲም በበኩላቸው የዳርፉር ጥቃት ሰለባቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ታሪካቸውን በፍርድ ቤት ቀርበው መናገር መቻላቸውን አድንቀዋል። ለድርጊቱ ተጠያቂዎቹ በሕግ ፊት መቅረባቸው አንድ ቀን ሱዳን ውስጥ ያለው ነገር መፍትሄ እንዲያገኝ እንደሚያደርግም ተስፋቸውን ተናግረዋል።
ምንም እንኳን ጥቂት ተጠያቂዎች በሕግ ቁጥጥር ስር ቢሆኑም አብዛኞቹ ገና አልተያዙም። የዓለም አቀፉ የጦር ወንጀል ተመልካች ፍርድ ቤት እስካሁን በአጠቃላይ ስድስት ክሶችን መስርቶ፤ ለሰባት ተጠርጣሪዎች ደግሞ የእስር ማዘዣ አውጥቷል። እስካሁን የአሊ ኩሸይብ ጉዳይ ነው በፍርድ ቤቱ መታየት የጀመረው። ግለሰቡ የዛሬ ሦስት ዓመት በፈቃደኝነት ወደ ፍርድ ቤቱ ቀርቧል። ከተፈጸመው ወንጀል እና ከተጠርጣሪዎቹ ብዛት አንጻር ሲታይ ኢምንት ነው ይሉታል የመብት ተሟጋቿ ኤልስ ኬፕለር።
አብዛኞቹ ተጠርጣሪዎች እስካሁን ወደ ችሎቱ ተላልፈው አልተሰጡም። ከተከሳሾቹ ጎልተው የሚታዩት የቀድሞው የሱዳን መሪ ኦማር አልበሽርሲሆኑ እዚያው በሀገራቸው ለተወሰኑ ጊዜያት ታስረው እንደነበር ይነገራል። አብዛኞቹ ተጠርጣሪዎቹ ከእስር መለቀቃቸውን እንደሰሙ የገለጹት ኬፕለር ተጎጂዎች ፍትህ ማግኘት ስላለባቸው ተፈላጊዎቹ ፍርድ ቤት መቅረብ እንዳለባቸው ነው የሚያሳስቡት። «ይኽ ፍትህ ወደፊት የሚሄድበት ብርቅዬ አጋጣሚ ነው። ኻርቱም ተፈላጊዊቹ ተላልፈው እንዳይሰጡ አግዳለች። የተመድ የጸጥታው ምክር ቤትም ቢሆን አልበሽርን ጨምሮ ተፈላጊዎቹ ወደፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ስለመተባበር ይኽ ነው የሚባል ግፊት አላደረገም። የሥልጣን ለውጥ በነበረ ሰሞን እነዚያ ተጠርጣሪዎች ከአንዳንድ ሂደቶች ጋር በተገናኘ ተይዘው ነበር። የሚያሳዝነው ግን እነዚያ ተፈላጊዎች አሁን በእስር ላይ እንዳልሆኑ ተረድተናል። ወደሌላ ስፍራ ተዛውረው በተከሰሱበት የፍርድ ሂደቱ እንዲቀጥል የማድረግ ፍላጎት አሁንም አለ።»
ሱዳን ውስጥ ከ20 ዓመታት በፊት የተፈጸመው የጦር ወንጀል በዓለም ዓቀፍ ፍርድ ቤት መታየት በጀመረበት በዚህ ወቅት በሀገሪቱ የቀጠለው ተመሳሳይ ወንጀል አሁን እያነጋገረ ነው።
ሸዋዬ ለገሠ/ሉሲያ ሹልተን
አዜብ ታደሰ