የህወሓት ልዩነት የፕሪቶሪያን ሥምምነት “ባለቤት አልባ” ሊያደርግ እንደሚችል ጌታቸው ተናገሩ
እሑድ፣ ነሐሴ 12 2016ለሁለት ተከፍሎ በመወዛገብ ላይ ያለው ህወሓት፥ ዛሬ እሁድ በአንድ ኪሎ ሜትር ልዩነት በሚገኙ ሁለት አዳራሾች፥ በተለያዩ ስብሰባ ላይ ውሏል። ካለፈው ማክሰኞ ጀምሮ እነ ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል የሚገኙበት ቡድን በሐወልቲ ሰማእታት አደራሽ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ያለ ሲሆን፥ እነ አቶ ጌታቸው ረዳ ያሉበት ሌላኛው ቡድን ደግሞ በትግራይ ምክርቤት አደራሽ 'የህወሓት ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ማእከል ያደረገ' የተባለ ስብሰባ ሲያደርጉ ውለዋል።
በዚሁ መድረክ የህወሓት ቁጥጥር ኮምሽን አባላት፣ ከጉባኤው ራሳቸው ያገለሉ የህወሓት ማእከላይ ኮሚቴ አባላት፣ የዞን እና ወረዳ አመራሮች ጨምሮ በርካታ የፓርቲው አባላት የተገኙበት ሲሆን፥ ተሰብሳቢዎቹ 'በህወሓት ስም እየተካሄደ ነው' ብለው የገለፁት ጉባኤ አውግዘውታል።
የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት እና የህወሓት ምክትል ሊቀመንበር አቶ ጌታቸው ረዳ፥ በስብሰባው ረዥም ንግግር ያደረጉ ሲሆን በህወሓት ከፍተኛ አመራር መካከል ያለ ልዩነት "ጉባኤ ይደረግ አይደረግ" የሚል ሳይሆን፥ እንዴት ይደረግ የሚል መሆኑ አብራርተዋል።
የህወሓት እውቅና ጉዳይ ከፌደራል መንግስት ጋር በሚደረግ ፖለቲካዊ ውይይት መፍትሔ እንዲገኝለት ሁሉም ተግባብቶ እያለ፥ የተወሰኑ ግለሰቦች በጎን በመንቀሳቀስ ወደ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ወረቀት በማስገባት ከመግባባቱ ያፈነገጠ ስራ ከውነዋል በማለት ሌላው የህወሓት ቡድን አመራሮችን ተችተዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ህወሓት ውስጥ በተፈጠረ አለመግባባት እና ክፍፍል፥ የፕሪቶርያ የሰላም ስምምነት ባለቤት አልባ እንዳይሆን ስጋት መኖሩ ያነሱት አቶ ጌታቸው ረዳ ይህ አደጋ ለመቀልበስ ጥረት እንደሚደረግ ተናግረዋል።
አራተኛ ቀኑን የያዘው የሕወሓት ጉባኤ እና የተቃዋሚዎች መግለጫ
አቶ ጌታቸው "ይህ የፕሪቶርያ የሰላም ስምምነት ሂደት ባለቤት አልባ ሊያደርግ የሚችል መሆኑ መረዳት ያስፈልጋል። ይህ ጉባኤ የፌደራል መንግስት አልተቀበለውም። ፌደራል አለመቀበሉ የራሱ ትርጉም አለው። ዋናው ነገር ግን በፓርቲያችን ውስጥ አንድነት እና መቀራረብ፣ በሐሳቦች ዙርያ አብሮ መስራት ሳይሆን መከፋፈል እና መራራቅ የሚያስከትል አደገኛ መድረክ ነው ተብሎ የሚወሰድ ነው። ይህም ፕሪቶሪያ ያለባለቤት የሚቀርበት ዕድል የሚፈጥር ነው" ብለዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ህወሓት ውስጥ የተፈጠረው ልዩነት አስጊ እና 'ጠላቶች' ብለው የገለጿቸው ኃይሎች ሊጠቀሙበት የሚችሉ ሲሉ አቶ ጌታቸው ረዳ ተናግረዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ትላንት ለክልሉ መገናኛ ብዙሐን ማብራርያ በሰጡት ጊዜ፥ የህወሓቱ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ጌታቸው ረዳ አሁን ላይ ጉባኤ በማድረግ ላይ ያለ የህወሓት ቡድን ማንነቱ ካልታወቀ የውጭ ኃይል ጋር ግንኙነት ሊኖረው እንደሚችል ጠቁመው ነበር።
አቶ ጌታቸው "የህዝብ የሰላም ፍላጎት ወደጎን በመተው፣ ለግዜው ማን መሆኑ በግልፅ ከማይታወቅ እና እነሱ ደጀን ይሆነናል ያሉት የውጭ ኃይል ተማምነህ፥ ያለ የሆነ ዝግጅት፣ የተወሰነ ግለሰቦች ጠባብ ፍላጎት ሲባል የትግራይ ህዝብን ዳግም ወደ አደጋ ለመዳረግ የሚደረግ እንቅሰቃሴ ነው እየተካሄደ ያለው" ሲሉ ተናግረዋል።
የህወሓት 14ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ቃል አቀባይ አቶ አማኑኤል አሰፋ ግን “ይኸ አገላለጽ ትክክል አይደለም” ሲሉ አቶ ጌታቸው ያቀረቡትን ክስ አስተባብለዋል። “ህወሓት እምነቱ በትግራይ ሕዝብ፣ በፕሪቶሪያው የሰላም ሥምምነት በተቋማዊ አሰራር ነው” ያሉት አቶ አማኑኤል “ሁሉም ችግሮች በሰላማዊ ፖለቲካዊ መንገድ ይፈታሉ ብለን ነው የምናምነው” ሲሉ ተናግረዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በ14ተኛ ጉባኤ ላይ ያለው ህወሓት፥ በፓርቲው ስም ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ እንዳያደርጉ በማለት የቆየው ማእከላይ ኮሚቴ እና የህወሓት ማእከላዊ ቁጥጥር ኮምሽን ማገዱ ትላንት ማስታወቁ ይታወሳል።
ሚሊዮን ኃይለሥላሴ
እሸቴ በቀለ