1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በጋምቤላ የተሻለ የሠላም ሁኔታ እየመጣ ነው ተባለ

ዓለምነው መኮንን
ዓርብ፣ ጥቅምት 29 2017

በጋምቤላ ክልል ካለፈው ነሐሴ 2016 ዓ ም ወዲህ የአመራር ለውጥ ከተደረገ ወዲህ በክልሉ የነበረው የሠላም ሁኔታ እየተሻሻለ መምጣቱን አዲሱ አስተዳደር፣ ተፎካካሪ የፖልቲካ ፓርቲ አመራሮችና ነዋሪዎች ተናገሩ።d ባለፈው ዓመት በጋምቤላ ክልል በተለያዩ አካባቢዎችና ጊዜዎች ግጭቶች እየተከሰቱ በሰው ህይዎት ላይ ጉዳት ሲደርስ ቆይቷል።

https://p.dw.com/p/4mnPg
ጋምቤላ ከተማ
ጋምቤላ ከተማ ምስል Negassa Desalegn/DW

በጋምቤላ የተሻለ የሠላም ሁኔታ እየመጣ ነው ተባለ

በጋምቤላ የተሻለ የሠላም ሁኔታ እየመጣ ነው ተባለ
በጋምቤላ ክልል ካለፈው ነሐሴ 2016 ዓ ም ወዲህ የአመራር ለውጥ ከተደረገ ወዲህ በክልሉ የነበረው የሠላም ሁኔታ እየተሻሻለ መምጣቱን አዲሱ አስተዳደር፣ ተፎካካሪ የፖልቲካ ፓርቲ አመራሮችና ነዋሪዎች ተናገሩ።d ባለፈው ዓመት በጋምቤላ ክልል በተለያዩ አካባቢዎችና ጊዜዎች ግጭቶች እየተከሰቱ በሰው ህይዎት ላይ ጉዳት ሲደርስ ቆይቷል። ከሰብዓዊ ጉዳቱ ባሻገር በክልሉ ነዋሪዎች መካክል የነበሩ ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች በአንዳንድ ቦታዎች እስከመገደብ ደርሰውም እንደነበር ነዋሪዎቹ ይናገራሉ። የክልሉ ልማትና ሰላምም በእጅጉ ተጎደቶ እንደነበርም እነኚሁ አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬሌ የሰጡ የጋምቤላ ከተማ ነዋሪዎች ገልጠዋል። በተለይ ቀደም ባሉት ጊዜዎች የአኙዋክ ተውላጆች ወደ ኑዌር ሰፈር አይሄዱም፣ ኑዌሮችም በተመሳሳይ ወደ አኙዋክ ሰፈር ይሻገሩ እንዳልነበር የጋምቤላ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ጋትሏክ ሮን በስልክ ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋል።


አዲሱ አመራርና እየመጡ ያሉ ለውጦች በጋምቤላ
ችግሮችን ለማስተካክልና በክልሉ ሠላም ለማስፈንና ሀዝቡን ወደልማት ለማምጣት በክልሉ ከነሐሴ 2016 ዓ ም መጀመሪያ ሳምንት ላይ የአመራር ለውጥ በመደረጉ በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ሠላም መስፈኑን ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አመልክተዋል። በክልሉ በነበረው የሠላም እጦት ምክንያት የበጋምቤላ ከተማ የአኙዋክና የኑዌር በሚል ተከፍሎ አኙዋኮች ወደ ኑዌር ሰፈር፣ ኑዌሮችም ወደ አኙዋክ መንደር ለመሻገር ችግሮች እንደነብሩ ያስረዱት ዶ/ር ጋትሏክ፣ አሁን ያ ሁሉ ቀርቶ አዲሱ አመራር ወደ ሥራ ከገባና ህዝባዊ ውይይቶች ከተደረጉ በኋላ ሁሉም በሠላም በሁሉም ሥፍራ እንደሚንቀሳቀስ አመልክተዋል። ማሉት ዴቪድ የተባሉ የጋምቤላ ከተማ ነዋሪ የምክትል ርዕሰ መስተዳድሩን ሀሳብ ይጋሩታል፣ አሁን አንዱ ወደ ሌላው ያለስጋት እንደሚንቀሳቀስ ነው ያረጋገጡት። ከተማውም ሠላም እንደሆን አመልክተዋል።


ሕዘቡ በልማት መካስ አለበት ስለመባሉ
አዳዲስ ሹመቶችና ምደባዎች መሰጠታቸውን የገለፁት ዶ/ር ጋትሏክ ይህም የትምህርት ዝግጅትንና የሥራ ልምድን መሠረት ያደረገ እንደሆነ አብራርተዋል። ለውጥ ያመጣሉ ተብሎ የታመነባቸው ቀደም ሲል ስለጣን ላይ የነበሩና ህዝባዊ አመለካከት ያላቸው  በርከት ያሉ አመራሮችም  በአዲሱ ሹመትና ምደባ እንደገና መካተታቸውን ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጠዋል። “ሠላም ወርዶ ህዝቡ በልማት መካስ አለበት” በሚል እሳቤ እውቀት፣ ልምድና የተሻል አመለካክትና እይታ ያላችው ሠዎች ወደ አመራሩ እንደተካተቱ ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል።


“በኮታ መታሰር” ቀርቷል
ቀደም ሲል በነበረው አሰራር ወንጀል ያልሰሩ ሰዎች በኮታ ጭምር ይታሰሩ እንደነበር የተናገሩት ዶ/ር ጋትሏክ አሁን ግን በወንጀል የተጠረጠሩትን ብቻ ተጠያቂ የሚያደርግ አሰራር መዘርጋቱን ነው ያብራሩት።
“በፊት አንድ ኑዌር ቢያጠፋና ቢታሰር ሌላ አኙዋክ አብሮ እንዲታሰር ይደረግ ነበር፣ ሌላ አኙዋክ አጥፍቶ ቢታሰር  የኑዌር ተወላጅ ተደርቦ እንዲታሰር ይደረግ ነበር” ብለዋል፣ አሁን ግን ጠፋተኛው ከየትኛውም ወገን ይሁን ጠፋተኛ ከሆን ተጠርጣሪው ብቻ ተለይቶ ተጠያቂ እንደሚሆን ነው የገለጡት። “የኮታ እስር ቀርቷል” ብለዋል።

ጋምቤላ ከተማ
ጋምቤላ ከተማ ምስል Privat


“ከአዲሱ አመራር ጋር ለመስራት ዝግጁ ነኝ” ጋብዴን
የጋምቤላ ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ(ጋብዴን) ሊቀመንበር አቶ ኡባንግ ኡሞድ ቀደም ሲል የነበረው አመራር ህዝቡን መምራት እንዳልቻለና ለውጥ እንዲመጣ ሲታግሉ እንደንበር ገልጠዋል። ችግሩ የአመራሩ ሆኖ ሳለ ህዝቡን በከፍተኛ የሠላም እጦት ውስጥ ከትቶት ነበር ነው ያሉት። እንደ አቶ ኡባንግ በክልሉ የነበረውን ችግር እስከ የተፎካካሪ ፓርቲ የጋራ ምክር ቤት በማድረስ የነበረው የሠላም እጦት እንዲታወቅ መደረጉንና ለውጥ እንዲደረግ በግልም በጋራም ትግል ሲደረግ እንደነበር አስረድተዋል። አዲሶቹ አመራሮች በሕዝቡ ተቀባይነት ማግኘታቸውንና ፓርቲያቸውም በአዲሱ አመራር ደስተኛ መሆኑን አቶ ኡባንግ ተናግረዋል። ከአዲሱ አመራር ጋርም በጋራ ለመስራት ዝግጁ እንደሆኑም ነው የገለጡት። የጋምቤላ ክልል ምክር ቤት ነሐሴ 9/2016 ዓ ም ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ ወ/ሮ ዓለሚቱ ኡመድን የመጀመሪያዋ የክልል ሴት ርዕሰ መስተዳድር፣ ዶ/ር ጋትሏክ ሮንን ደግሞ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አድርጎ መሾሙ ይታወሳል።


ዓለምነው መኮንን

አዜብ ታደሰ 

ነጋሽ መሐመድ