1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ባንኮች እርስ በርስ ብድር የሚሰጣጡበት አሠራር ተፈቀደ

ሰለሞን ሙጬ
ዓርብ፣ ጥቅምት 22 2017

ባንኮች ከአንድ ቀን እስከ ሰባት ቀናት መቆየት የሚችል ገንዘብ መበደር እና ማበደር የሚችሉበትን ገበያ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ይፋ አድርጓል። ግብይቱ በኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ ብቻ የሚከወን ነው። በባንኮች መካከል የሚደረግ የገንዘብ ግብይት የወለድ ተመን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባስቀመጠው የፖሊሲ የወለድ ተመን ክልል ውስጥ ይሆናል።

https://p.dw.com/p/4mUN6
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባንኮች እርስ በርሳቸው ብድር የሚሰጣጡበትን የገንዘብ ገበያ ሥርዓት ፈቀደ። ምስል Solomon Muche/DW

ባንኮች እርስ በርስ ብድር የሚሰጣጡበት አሠራር ተፈቀደ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባንኮች እርስ በርሳቸው ብድር የሚሰጣጡበትን የገንዘብ ገበያ ሥርዓት ፈቀደ። ንግድ ባንኮች የዕለት-ተዕለት የገንዘብ ፍሰታቸዉን በአግባቡ እንዲያስተዳደሩ ያግዛል የተባለለት አሠራር፣ የአንድ ቀን ወይም የሰባት ቀናት የመክፈያ ጊዜ ያላቸው ብድሮችን የሚያካትት ስለመሆኑም ተገልጿል።

መመርያው ጠቃሚ መሆኑን የገለፁ አንድ የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያ ያም ሆኖ ባንኮቹ መልሰው በምን ያህል ወለድ ለደንበኞቻቸው ብድር ይሰጣጣሉ የሚለው ጉዳይ መሠረታዊ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ባንኮች ያላቸው ሀብት 3.5 ትሪሊየን መድረሱን ትናንት ፓርላማ ውስጥ የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ "ባንክ በሚል ስም አራጣ የሚሠሩ" ያሏቸው ባንኮች መኖራቸውን ጠቅሰው ያንን በሚያደርጉት ላይ ከፍተኛ ክትትል እና እርምጃ ይወሰዳል ብለዋል።

በመመርያው ላይ የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያ አስተያየት 

የፖሊሲ ባንክ የሆነው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ትናንት ጥቅምት 21 ቀን 2017 ዓ.ም ያስተዋወቀው መመሪያ ዘርፉን ለማጠናከር ይረዳል፣ ባንኮች "የአጭር ጊዜ የገንዘብ ጉድለትን በመሸፈን ወይም ትርፍ ገንዘብን ለሌሎች ባንኮች በማበደር የገንዘብ ፍሰትን በብቃት እንዲያስተዳደሩ ያስችላቸዋል" ተብሎለታል።

 በብሔራዊ ባንክ መመሪያ ላይ የባለሙያዎች አስተያየት

በባንክ ዘርፍ "ጤናማ ውድድርን በመፍጠር"፣ የገበያ መረጋጋትን ማሻሻል፣ የገንዘብ እጥረት ሥጋትን መቀነስ እና በተረጋጋ የወለድ ተመን ለደንበኞች የተሻለ አገልግሎት መስጠት ያስችላልም" ተብሏል። 

ብር
ንግድ ባንኮች የዕለት-ተዕለት የገንዘብ ፍሰታቸዉን በአግባቡ እንዲያስተዳደሩ ያግዛል የተባለለት አሠራር፣ የአንድ ቀን ወይም የሰባት ቀናት የመክፈያ ጊዜ ያላቸው ብድሮችን የሚያካትት ስለመሆኑም ተገልጿል።ምስል MICHELE SPATARI/AFP

የገንዘብ አስተዳደር እና የምጣኔ ሐብት አማካሪና መምህር የሆኑት አቶ ዳዊት ታደሰ እርምጃው በተለይ ከፍተኛ የገንዘብ ክምችት አቅም ባላቸው እና በሌላቸው ባንኮች መካከል በጎ የንግድ ትስስር እና ሥራ ለመፍጠር እንደሚያስችል ለዶቼ ቬለ አብራርተዋል።  "ተበዳሪዎች የተሻለ ዕድል ሊያገኙ ይችላል" 

የብድር ወለድ ተመን ምጣኔው ጉዳይ መሠረታዊ ነው - ባለሙያ 

ብሔራዊ ባንክ መመሪያውን "በባንክ ዘርፉ ያለውን የገንዘብ ፍሰት አስተዳደርን በማጎልበት፣ የፋይናንስ ዘርፍን ለማረጋጋት የተወሰደ ትልቅ እርምጃ ነው" ብሎታል። 

የወለድ ተመኑ ብሔራዊ ባንክ ባስቀመጠው የወለድ ተመን ክልል ውስጥ እንደሚሆን" ይጠበቃልም በሚል ተገልጿል።

የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች ፈቃድ

ሕጋዊ ማዕቀፍ የነበረው ባይሆንም ሥራው የነበረ መሆኑን የሚገልፁት የገንዘብ አስተዳደር እና የምጣኔ ሐብት አማካሪና መምህሩ አቶ ዳዊት ታደሰ፣ ባንኮቹ የሚበዳደሩበት የወለድ ምጣኔ ምን ያህል ነው ? የሚለው ባንኮች ከደንበኞቻቸው አንፃር ቁልፍ ጉዳይ መሆኑ ሊዘነጋ አይገባም ባይ ናቸው።

"እርስ በርሳቸው ሲበዳደሩ በምን ያህል ወለድ ነው የሚበዳደሩት ነው" ሲሉ ይጠይቃሉ።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ
በዚህ ወቅት 32 የደረሱት የኢትዮጵያ ባንኮች ያላቸው ሀብት 3.5 ትሪሊየን ብር መድረሱን ትናንት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያስታወቁት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ 450 ቢሊየን ብር ብድር መልቀቃቸውን ጠቅሰዋል።ምስል Solomon Muche/DW

ሥራው በሰነደ ሙዓለ ንዋይ የግብይት ሥርዓት ላይ ብቻ  የሚከወን ነው

ይህ አሠራር በኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ የግብይት ሥርዓት ላይ ብቻ እንዲሆን የተፈቀደ ነው። ይህም ከግብይቱ ደህንነት፣ ቅልጥፍና እና ግልጽነት ጋር የተገናኘ መሆኑ ታምኖበታል።

የብሪክስ አዲስ የመገበያያ ገንዘብ ውጥን፣ እድል ወይስ ፈተና?

በዚህ ወቅት 32 የደረሱት የኢትዮጵያ ባንኮች ያላቸው ሀብት 3.5 ትሪሊየን ብር መድረሱን ትናንት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያስታወቁት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ 450 ቢሊየን ብር ብድር መልቀቃቸውን ጠቅሰዋል። ሆኖም ዘርፉ ከወንጀል ድርጊቶች የነጻ እንዳልሆነ ጠቁመዋል። 
"ባንክ በሚል ስም የአራጣ ሥራ የሚሠሩ ከሆነ ችግር ነው"። 

ባንኮች እርስ በርሳቸው ገንዘብ ወይም ብር ለመበዳደር ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ፍቃድ ማግኘት እና የሚጠበቅባቸውን መስፈርቶች ማሟላት እንደሚኖርባቸው በመመርያው ተገልጿል።

ሰለሞን ሙጬ

እሸቴ በቀለ

ዮሐንስ ገብረእግዚዓብሔር