1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ናዋዥ -የወጣት ኢትዮጵያዉያንን ህይወት የሚበላው የስደት መንገድ

ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 10 2017

«በሕገ-ወጥ ስደት በጣም ብዙ ሰዎች ምድረ በዳ ላይ ቀርተዋል። ሊቢያ ዉስጥ ደብዛቸዉ ጠፍቶ ቀርቷል። ብዙ ስደተኞች አካላቸዉ ጎልዋል። የሰዎችን አካል እየቀደዱ ኩላሊት የሚዘርፉ ሁሉ አሉ። በዚህ ጉዳይ የሰለጠኑ ሰዎች የተደራጁ ሐኪሞችም ጭምር ያሉበት ይህን ስራ የሚሰራ ቡድን በረሃ ላይ አለ።

https://p.dw.com/p/4oNoJ
Äthiopien | Autobiografie "NawaJ" von Eyayu Dagnaw
ምስል Eyayu Dagnaw

ናዋዥ -የኢትዮጵያዉያንን ህይወት የሚበላው የስደት መንገድ

ናዋዥ -የወጣት ኢትዮጵያዉያንን ህይወት የሚበላው የስደት መንገድ

«በሕገ-ወጥ ስደት በጣም ብዙ ሰዎች ምድረ በዳ ላይ ቀርተዋል። ሊቢያ ዉስጥ ደብዛቸዉ ጠፍቶ ቀርቷል። ብዙ ስደተኞች አካላቸዉ ጎልዋል። የሰዎችን አካል እየቀደዱ ኩላሊት የሚዘርፉ ሁሉ አሉ። በዚህ ጉዳይ የሰለጠኑ ሰዎች የተደራጁ ሐኪሞችም ጭምር ያሉበት ይህን ስራ የሚሰራ ቡድን በረሃ ላይ አለ። በጉዞ ላይ ደመከልብ ሆነዉ የቀሩትን ሰዎች አያይም ሰዉ። የገቡትን ብቻ ነዉ የሚያስበዉ። አዉሮጳም ከገቡ በኋላ በጣም ብዙ ሰዎች የሥነ-ልቦና ችግር አጋጥሟቸዋል። በአገር ዉስጥ የተለያየ ችግር እንዳለ ይታወቃል፤ ግን ከህይወት አይበልጥም።»

ከሀገራቸዉ ወጥተዉ በሕገ-ወጥ መንገድ ሊብያን አቋርጠዉ፤ አዉሮጳ ለመግባት አልመዉ፤ በሜዲተራንያን ባህር እና ሰሃራ በረሃ ሕይወታቸዉን ላጡ እንዲሁም በዚሁ መንገድ ሲጓዙ ብዜ ሰቆቃ ለደረሰባቸዉ ስደተኞች መታሰብያ ይሆን ዘንድ የስደት አስከፊ ገጠመኙን «ናዋዥ»  ሲል በመጽሐፍ መልክ ለአንባቢ ያቀረበዉ በጀርመን ነዋሪ የሆነዉ የ36 ዓመቱ ኢትዮጵያዊ ስደተኛ ደራሲ እያዩ ዳኛዉ ነዉ። እንግዳችን እያዩ ዳኘዉ ከጎርጎረሳዉያኑ 2014 ዓ.ም ጀምሮ በጀርመን ሃገር በስደት እየኖረ ነዉ። ከአገሩ በመተማ ገዳሪፍ ሱዳን ቤንጋዚ ትሪፖሊ ሊቢያ፤ ትራፓኒ ጣልያን በኩል ጀርመን እስኪደርስ ድረስ ወደ ስድስት ዓመት ገደማ ፈጅቶበታል። በጎዞ ላይ ከባድ ችግር  ፤ስቃይ ድብደባን ረሃብ እና በሽታን አልፎ እዚህ ላይ መድረሱን ሲያስበዉ ለሱም እንቆቅልሽ ነዉ። ግን ለምን ይህ ሁሉ መንከራተት ሲልም ራሱን በተደጋጋሚ ይጠይቃል። ህሊናዉን ለማከም የጉዞ ገጠመኙን ናዋዥ በሚል ርዕስ  ክፍል አንድ መጽሓፉን አሳትሞ ለአንባቢ አቅርቧል።

« ናዋዥ ማለት የሚናዉዝ ከአገር አገር ተንከራታች ማለት ነዉ። ይህን ቃል የመረጥኩት የህይወት ታሪኬን የሚገልፅ ቃል ሆኖ ስላገኘሁት ነዉ ለመጽሐፊ ርዕስ ያደረኩት። ያደኩት እና የተወለድኩት ክምር ድንጋይ እና ንፋስ መዉጫ ከተሞች ነዉ ፤ ደብረታቦር ዙርያ የሚገኙ ከተሞች ናቸዉ። ጎንደር ክፍለ ሐገር» እያዩ በትዉልድ አካባቢዉ በልብስ ስፊት ይተዳደር እንደነበር እና ነገሮች አልሳካ ሲሉ ኑሮን ማሸነፍ ወደ ሱዳን ተሰዶ እንደነበር፤ ከዝያም ከሱዳን ተጠርዞ መመለሱን፤  ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ሱዳን መሰደዱን የስደት ጉዞዉም ከባድ እንደነበር አጫዉቶናል። 

እያዩ ዳኛዉ - አደገኛዉ የስደት ጉዞ ማስታወሻ 

« ከባድ ነበር ፤ መጀመርያ ወደ ጎንደር ከዝያ በኋላ፤ ወደ አብርሃ ጅራ ፤ አብደራፊ ፤ ማይካድራ ፤ እያልኩ ነዉ ፤ በመተማ እና ሁመራ አካባቢ ፤ በጉልበት ስራ ፤ በሰሊጥ አጨዳ፤ በአረም በማረም ሁሉ ሰርቻለሁ። መጀመርያ የሄድኩት ወደ ሱዳን ጠረፍ ነበር። ከዝያም ወደ ሱዳን በእግሬ ነዉ የገባሁት።የጉልበት ሰራተኞች ሁሉ የሚገቡት በእግራቸዉ ነበር የሚገቡት። ሱዳን ዉስጥም የተለያዩ እርሻ ያላቸዉ ባለሃብቶች ጋር በአጨዳ በአረም በመሳሰሉ ስራዎች ላይ ተሰማርቼ ነበር። ይህን ስራ እየሰራሁ በሱዳን ገዳሪፍ እንደገባሁ በፖሊስ ተይዤ ወደ አገሪ ተጠርዣለሁ። ይሁና በአገር ቤት የነበረኝ ትዳር ስኬት ስላልነበረዉ ተመልሼ ወደ ሱዳን ተሰደድኩ። » በሱዳን የእርስ በእርስ ጦርነት ከመቀስቀሱ በፊት መዲና ካርቱም ተጉዞ የደረሰዉ እያዩ ካርቱም ላይ በመጀመርያ ስራ ማግኘት አልቻለም ነበር ።

እያዩ ዳኛዉ - አደገኛዉ የስደት ጉዞ ማስታወሻ
እያዩ ዳኛዉ - አደገኛዉ የስደት ጉዞ ማስታወሻ ምስል Eyayu Dagnaw

ሞያ የሌላቸዉ ወንዶች በሱዳን ስራ የማግኘት እድላቸዉ እጅግ የመነመነ ነዉ። ሴቶች ኢትዮጵያዉያን ስደተኞች ፤ በሰዉ ቤት ተቀጥረዉ አልያም በመንገድ ላይ ቡና ሻይ በማፍላት ይተዳደሩ ነበር። ወንዶች ግን ስራ ለማግኘት አይችሉም ነበር። የኋላ የኋላ እኔ በልብስ ስፊት ሞያዬ ስራ አገኘሁ። በመጀመርያ የትምህርት ቤት የተማሪዎች የደንብ ልብስ እሰፋ ነበር። ከዝያም የሱዳን ፖሊሶች ደንብ ልብስ ሁሉ እሰፋ ነበር። በሱዳን ይህን እየሰራሁ ወደ አራት አመት ተኩል ኖርያለሁ። ከዝያ ነዉ ተነስቼ ወደ ሊቢያ ለማምራት የወሰንኩት»

ሱዳናዉያን በኢትዮጵያዊዉ ዓይን 

እያዩ ዳኘዉ ናዋዥ በተሰኘዉ መጽሐፉ፤ ስለሱዳናዉያን ጽፏል። ሱዳናዉያን በመካከላቸዉ አለመግባባት ተከስቶ ሲዛዛቱ ለጠብ ሲጋበዙ  ሲያይዋቸዉ ምድርን ቀዉጢ የሚያደርጓት እንደሚመስሉ፤ ግን ቢሞቱ እንደማይጣሉ ፤ እጅ እንደማይሰናዘሩ ለክፉ ነገር እንደማይቸኩሉ፤ የካፈርኩ አይመልሰኝ ነገር እንደማያስራቸዉ፤ በሰዎች ዘንድ ፊሪ መባል እንደማይገዳቸዉ፤ ክብርን ለመጠበቅ ክብር ነክ ጠብ ዉስጥ እንደማይገቡ፤  ስደተኛዉ ደራሲ እያዩ ዳኛዉ በሰፊዉ ስለሱዳናዉያን በብዕሩ ከትቧል። ሱዳናዉያን ለኢትዮጵያዉያን ያላቸዉ ፍቅርም ልዩ መሆኑን በተደጋጋሚ ነግሮናል። በሱዳን ጦርነቱ ከመቀስቀሱ በፊት በርካታ ኢትዮጵያዉያን ካርቱም ዉስጥ ይኖሩ እንደነበርም እያዩ ዳኛዉ አጫዉቶናል። አሁን በጦርነቱ ወቅት በሱዳን በተለይ በካርቱም ይኖሩ ኢትዮጵያዉያን አብዛኞቹ ወደ ኢትዮጵያ መመለሳቸዉን አልያም ወደ ሌሎች የድንበር ከተሞች መፈናቀላቸዉን ነግሮናል።» አራት ዓመት ከስድስት ወር በስደት መዲና ካርቱን የኖረዉ እያዩ ዳኘዉ፤ ኢትዮጵያ የመሰረተዉ ትዳሩ መፍረሱን ሰማና  አሁንም ኑሮን ለማሸነፍ ከካርቱም ተነሳ ወደ ሊቢያ።   

« ካርቱም ኖሬ ወደ ሊቢያ ተነሳሁ። ደላሎች በመንገድ ላይ የምንበላዉን ምግብ እንድንቋጥር የምንጠጣዉን ዉሃ እንድንይዝ ነግረዉን ጎዞ ጀመርን። መንገዱ ከጠበኩት በላይ በጣም አስፈሪ ፤ በጣም ከባድ ሆኖ ነዉ ያገኘሁት። ሰሃራ በረሃን ለማቋራጥ ጉዞዉ ከሳምንታት በላይ ሁሉ ሊወስድ ይችላል። እና ስድስት ቀናቶች ነዉ የፈጁብን። ስድስት ቀን ሙሉ ምንም የማይታይበት ምድረበዳን ማቋረጥ ማለት ነዉ። በዝያ ላይ በረሃ ዉስጥ አጋቾች ሽፍቶች አሉ። ድንበር ጠባቂዎች አሉ በነሱም መያዝ አለ። መንገድ ላይ አግተዉ ኩላሊት የሚያወጡ በቡድን የተደራጁ ሃኪሞች ሁሉ አሉ። አግተዉ ገንዘብ የሚቀበሉ ሽፍቶች ሁሉ አሉ። በዚህ ምክንያት በርካታ ስደተኞች ይሞታሉ። በጉዞ ላይ የሰዎችን አፅም የደረቀ አስክሬን ሁሉ አይተናል። መንገድ ላይ መኪና ቢበላሽ ፤ ደላሎች ባይመጡልን ፤ በረሃ ላይ ቀልጠን ልንቀር ሁሉ እንችል ነበር።»

እያዩ ዳኛዉ - አደገኛዉ የስደት ጉዞ ማስታወሻ
እያዩ ዳኛዉ - አደገኛዉ የስደት ጉዞ ማስታወሻ ምስል Eyayu Dagnaw

 

ግን ለምን ሥደት

በመቀጠል እያዩ ቤንጋዜ ደረሰ ቤንጋዚ ፤ በረኝነት በአትክልተኝነት ብሎም በልብስ ሰፊነት  አገልግሏል። በቤንጋዚ ከአስር ወራቶች ቆይታ በኋላ ከቤንጋዚ አንድ ሺህ ኪሎሜትር ወደሚርቀዉ ወደ ሊብያዋ መዲና ወደ ትሪፑሊ በደላላ ጉዞን ጀመረ።  በጉዞ ላይ የደላላ ድብደባ ብሎም የጉዞ አድካሚነት እጅግ ፈታኝ እንደነበር እያዩ አጫዉቶናል። ወጣቱ ስደተኛ እያዩ ዳኛዉ ትሪፑሊ የባህር ጠረፍ ሲደርስ መጋዘን ዉስጥ ጉዞዎዋቸዉን የሚጠባበቁ ኢትዮጵያዉያንን ጨምሮ ከተለያዩ አፍሪቃ ሃገራት የመጡ በመቶዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችን አገኘ። እያዩ ገንዘብ ስላልነበረዉ ለጓዳ ሰራሽ ጀልባ የሚሆነዉን ገንዘብ ከፍሎ ሜዲተራንያን ባህርን ለመሻገር ወሰነ።  የናዋዥ የስደት ጉዞ ታሪክ ፀሐፊ ወጣቱ ስደተኛ ፤ በመጽሐፉ ያስቀመጠዉከኢትዮጵያ ሱዳን ሊብያ እስከ ጣልያን ያለዉን የጉዞ ማስታወሻ ነዉ። በቀጣይ ያልገመተዉን ከባዱን የአዉሮጳ ኑሮ ተሞክሮ በሁለተኛ የጉዞ ማስታወሻ መልክ ለአንባብያን ለማቅረብ ዝግጅቱን እያጠቃለለ ነዉ።  የስደት ጉዞ ታሪኩን በጽሑፍ መልክ ለአንባብያን ናዋዥ በሚል መጽሐፉ ያስነበበን እያዩ ዳኛዉን ለቃለምልልሱ እያመሰገንን፤ ሁለተኛ መጽሐፉ ለአንባብያን እንደቀረበ፤ እያዩ ዳኛዉን የአዉሮጳ ተሞክሮዉን እንዲያካፍለን በእንግድነት ይዘነዉ እንቀርባለን።

ከእያዩ ዳኛዉ ጋር ያደረግነዉን ሙሉዉን ቃለምልልስ የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን!

አዜብ ታደሰ

ሸዋዬ ለገሠ