አዲሱ ዓመት ለተቀጣሪው ሰራተኛ ተስፋ ወይስ ስጋት ?
እሑድ፣ መስከረም 6 2016ኢትዮጵያ በበርካታ ፖለቲካዊ ማሕበራዊ እና ኤኮኖሚያዊ አለመረጋጋት ውስጥ ሆና የ2016 አዲስ ዓመትን ተቀብላለች ። ኢትዮጵያውያን ሲወርድ ሲወራረድ በመጣው ትውፊታቸው አዲስ ዓመት በመጣ ቁጥር በአሮጌው ዓመት ያጋጠማቸው የህይወት ስንክሳር ዳግም እንዳይመለስ ብሎም አዲሱ ዓመት የተሻለ ነገር ይዞ እንዲመጣ መልካም ምኞታቸውን ይለዋወጣሉ ። አዲስ ዓመት በመጣ ቁጥር የበዓላት መደራረብ ከሚፈጥርባቸው የፋይናንስ ቀውስ በተጨማሪ የዓመቱ ትምህርት መጀመሪያ እንደ መሆኑ መጠን ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት ለመላክ የሚፈተኑበት ወቅትም ነው። በዚህ ሂደት በተለይ ወር ጠብቀው ህይወታቸውን የሚገፉት የመንግስት ሰራተኞች፤ መምህራኑ ፣ ብሎም በአጠቃላይ ተቀጣሪ ሆነው በዝቅተኛ ደመወዝ የሚተዳደሩ የሕብረተሰብ ክፍሎች መጣፊያ የታጣለት የዋጋ ግሽበት እና የኑሮ ውድነት የህይወት ፈተናን እንዳከበደባቸው ይታያል ፤ ይሰማል። የትግራይ ክልል የመንግሥት ሰራተኞች አቤቱታበሀገሪቱ በተለይ የመሰረታዊ ፍጆታ ቁሶች እና የቤት ኪራይ በየጊዜው ያለከልካይ እጅግ በተጋነነ ሁኔታ ጭማሪ ሲያሳዩ ሰራተኛው በወር በሚያገኘው ደመወዝ ላይ ጭማሪ ስለመደረጉ ብዙም አይሰማም ወይም ቢኖርም ያለውን የገበያ እና የኑሮ ሁኔታ የሚመጥን ሆኖ አለመገኘቱ ነው የሚነገረው ። በሀገሪቱ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በበርካታ አካባቢዎች ግጭት ፣ ጦርነት መበርታቱ ያስከተለው ሀገራዊ ማሕበራዊ እና ኤኮኖሚያዊ መመሰቃቀል ለወትሮም ዓለማቀፋዊ ወቅታዊ ሁኔታ ያሳደረው የኤኮኖሚ ጫና መሸከም ለከበዳት ሀገር እና ህዝብ ችግሩን ከድጡ ወደ ማጡ አድርጎባቸዋል። መንግስት ለሀገራዊ ችግር ዘላቂ መፍትሔ ለመሻት እየጣረ መሆኑን ከመናገር በዘለለ በተለይ ለተቀጣሪው ሰራተኛ በተግባር የሚገለጥ እና መሰረታዊ ለውጥ የሚያመጣ መፍትሔ አለመቀመጡም በተደጋጋሚ ሲገለጽ ቆይቷል።የመንግሥት እና የግል ድርጅቶች የጡረታ ክፍያ መጠን ጥያቄ ምንም እንኳ ጊዜው የአዲስ ዓመት መባቻ ቢሆንም ፤ የመልካም ምኞት እና ተስፋ የሚነገርበት ጊዜ ቢሆንም የገንዘብ የመግዛት አቅም መዳከም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየበረታ በሄደበት ሀገር ፤የቤት ኪራይ እና መጓጓዣን ጨምሮ የመሰረታዊ ፍላጎቶች ዋጋ በየጊዜው እየናረ በሄደበት በዚህ ጊዜ፤ የገቢ ለውጥ ማየት የተሳነው እና በተለያየ ሞያ ስለተሰማራው ተቀጣሪ ሰራተኛ መጻኢ ዕጣ ፈንታ መወያየት ባላስፈለገም ነበር። የኾነ ሆኖ ችግሩ ብርቱ ፤ መትሔውም መቅርብ አለበት እና የውይይት አጀንዳ አድርገነዋል።ወርሃዊ ደሞዝ ያላገኙ የመንግሥት ሰራተኞች በሃዲያ ዞን «የዋጋ ግሽበት እና የኑሮ ውድነት ያማረረው የተቀጣሪ ሰራተኛ የገቢ ሁኔታ በአዲሱ ዓመት ተስፋ እና ስጋት » ደግሞ የሳምንቱ የእንወያይ ዝግጅታችን ርዕስ ነው።
ታምራት ዲንሳ