ኢትዮጵያ በብሪክስ አባልነት "የተጋነነ ነገር" መጠበቅ የለባትም
ረቡዕ፣ ነሐሴ 24 2015ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ኢትዮጵያ ከመጪው ጥር ወር ጀምሮ የብሪክስ አባል እንድትሆን መጋበዟ "ትልቅ ኩራት እና የዲፕሎማሲ ድል" ሲሉ ገልጸውታል። ከነሐሴ 15 እስከ 18 ቀን 2015 በደቡብ አፍሪካ በተካሔደው የብሪክስ የመሪዎች ጉባኤ የተሳተፉት ዐቢይ "ኢትዮጵያ ባላት የዕድገት ተስፋ ለመመረጥ" እንደበቃች ገልጸዋል። ቻይና፣ ሕንድ፣ ሩሲያ፣ ብራዚል እና ደቡብ አፍሪካን በስም እየጠቀሱ ያመሰገኑት ጠቅላይ ሚኒስትሩ "በብዙ ትግል፣ በብዙ ንግግር የተገኘ ድል ነው" ሲሉ መንግሥታቸው ኢትዮጵያ ብሪክስን እንድትቀላቀል ዲፕሎማሲያዊ ጥረት እንዳደረገ ጠቁመዋል።
ብሪክስን በአባልነት ለመቀላቀል 23 አገራት በይፋ ሌሎች በርካቶች በተዘዋዋሪ ፍላጎታቸውን ቢያሳውቁም ኢትዮጵያ ጥያቄያቸው ተቀባይነት ካገኘ መካከል መገኘቷ ጉዳዩን በቅርብ ለሚከታተሉ ባለሙያዎች አስገራሚ ሆኗል። ብሪክስ ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ሳዑዲ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች፣ ግብጽ፣ አርጀንቲና እና ኢራንን በአባልነት በመቀበል ለመስፋፋት ያሳለፈውን ውሳኔ የቻይና ፕሬዝደንት ሺ ዢንፒንግ "ታሪካዊ" ብለውታል።
ኢትዮጵያ ብሪክስን ብትቀላቀል ምን ጥቅም ታገኛለች?
ኢትዮጵያ የሊግ ኦፍ ኔሽንስ አባል እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መሥራች አገር መሆኗ ለአባልነቷ መፋጠን አዎንታዊ አስተዋጽዖ ካበረከቱ ጉዳዮች አንዱ መሆኑን የቻይና አፍሪካ አማካሪ ተቋም መሥራች እና ዳይሬክተር የሆኑት አቶ አሌክሳንደር ደምሴ ያምናሉ። "ብሪክስ ኢትዮጵያን አባል አደረገ ማለት የአፍሪካ አገሮች ላይ ያለው ተጽዕኖ በጣም ከፍ ባለ ደረጃ ሊቀጥል ይችላል" የሚሉት አቶ አሌክሳንደር ውሳኔው ለቡድኑ ስልታዊ ጠቀሜታ እንደሚኖረው አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት በብሪክስ አባልነት ላቅ ያለ ትሩፋት ይገኛል ብለው ይጠብቃሉ። የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የብሔራዊ ደሕንነት አማካሪ አቶ ሬድዋን ሑሴን የብሪክስ አባል አገራት እርስ በርስ በሚያደርጉት የንግድ ልውውጥ ከዶላር ይልቅ የየራሳቸውን የመገበያያ ገንዘብ መጠቀም ከጀመሩ ለኢትዮጵያ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ለብሔራዊው የቴሌቭዥን ጣቢያ ተናግረዋል።
የብሪክስ የመሪዎች ጉባኤ ዋንኛ አጀንዳዎች የትኞቹ ናቸው?
በልማት ፋይናንስ፣ በድጋፍ እና ኢንቨስትመንት አማራጭ እንደሚያሰፋ የተናገሩት አቶ ሬድዋን "የፖሊሲ ነጻነት ዕድልን" እንደሚሰጥ ጠቁመዋል። ከዚህ በተጨማሪ የብሪክስ አባልነት አቶ ሬድዋን "በቅድመ ሁኔታዎች" የታሰረ ላሉት "የገንዘብ ምንጭ" አማራጭ የሚሰጥ ጭምር ነው። ይኸ የአቶ ሬድዋን አገላለጽ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እና የዓለም ባንክን የመሳሰሉ የምዕራቡ ዓለም የፋይናንስ ተቋማት ብሪክስ አማራጭ ሊሆን ይችላል የሚል እሳቤ በኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ዘንድ እንዳለ የሚጠቁም ነው።
ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ብሪክስን በአባልነት የምትቀላቀለው በጦርነት የወደመውን መልሶ ለመገንባት ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ጠቀም ያለ ገንዘብ በምትሻበት ወቅት ነው። የኢትዮጵያ መንግሥት የዕዳ አከፋፈል ማሻሻያ ለማድረግ የጀመረው ድርድር እስካሁን አልተጠናቀቀም።
ኢትዮጵያ ብሪክስን መቀላቀሏ በተረጋገጠበት የደቡብ አፍሪካው የመሪዎች ጉባኤ ቻይና ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ለአንድ ዓመት የዕዳ ክፍያ እፎይታ ሰጥታለች። "ይኸ ለኢትዮጵያ መንግሥትም ትልቅ እፎይታ ነው" የሚሉት ዶክተር ቀልቤሳ መገርሳ የኢትዮጵያ የብሪክስ አባልነት "ዘርፈ-ብዙ ጠቀሜታ" እንደሚኖረው ያምናሉ። የብሪክስ አባል የሆኑት ቻይና እና ሕንድ የኢትዮጵያ ቀዳሚ የመዋዕለ-ንዋይ ምንጭ መሆናቸውን የጠቀሱት የምጣኔ ሐብት ተማራማሪው "ያንን በማበረታታት ትልቅ ጥቅም አለው" ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ለኢትዮጵያ የውጭ ንግድ አማራጭ ገበያ ሊከፍት እንደሚችል የገለጹት ዶክተር ቀልቤሳ ለቴክኖሎጂ ሽግግር እና ለቱሪዝም ገበያ አዎንታዊ አስተዋጽዖ እንደሚኖረው ተናግረዋል።
አቶ አሌክሳንደር ግን "ብዙ ወይም የተጋነነ ነገር" መጠበቅ እንደማይገባ ይመክራሉ። ተቋማዊ አሰራሮች ጊዜ እንደሚወስዱ የጠቆሙት አቶ አሌክሳንደር ኢትዮጵያ በይፋ የብሪክስ አባል ስትሆን በብራዚል፣ ሩሲያ፣ ሕንድ፣ ቻይና እና ደቡብ አፍሪካ ለግዙፍ የመሠረተ-ልማት ግንባታዎች መዋዕለ-ንዋይ ከሚያቀርበው ኒው ዴቬሎፕመንት ባንክ የመጠቀም ዕድል እንደምታገኝ ተናግረዋል። "በጥር ኢትዮጵያ ገብታ በየካቲት ብሩ ይገኛል ማለት አይደለም" የሚሉት አቶ አሌክሳንደር "ይኸ ራሱን የቻለ ሒደት አለው" ሲሉ አስረድተዋል።
ነባሮቹ የብሪክስ አባላት በዓለም አቀፉ የጂዖፖለቲካ ትንቅንቅ አንድም ከአሜሪካ መራሹ የምዕራቡ ዓለም በተቃራኒ የቆሙ ናቸው አንድም እንደ ደቡብ አፍሪካ ወደ ገለልተኝነት ያዘነብላሉ። ደቡብ አፍሪካ፣ ሕንድ እና ብራዚል የምዕራቡ ዓለም ጭልጥ ያለ ደጋፊ ባይሆኑም ዶክተር ቀልቤሳ እንደሚሉት "ተቀናቃኝ" መሆን የሚፈልጉ አገራት አይደሉም። ባለፈው ሣምንት ይፋ የሆነው የብሪክስ ውሳኔ በተለይ ምዕራባውያን አገራትን ደስተኛ የሚያደርግ እንዳልሆነ አቶ አሌክሳንደር ይናገራሉ።
ዶክተር ቀልቤሳ የብሪክስ መስፋፋት በእርግጥም በምዕራቡ ዓለም በአዎንታ የሚታይ ጉዳይ እንደማይሆን ይስማማሉ። ምዕራባውያኑ ቻይና እና ሩሲያን በአባልነት የያዘው ብሪክስ ሲስፋፋ የሚሰጡት ግብረ ምላሽ ወደፊት የሚታይ ይሆናል። ዶክተር ቀልቤሳ ግን ኢትዮጵያ በብሪክስ ውስጥ እንደ ደቡብ አፍሪካ አይነት አቋም ልትከተል እንደምትችል ተናግረዋል።
ሙሉ ዘገባውን ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ
እሸቴ በቀለ
ነጋሽ መሐመድ