1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኤች አይቪ ዛሬም ትኩረት ይሻል

ማክሰኞ፣ ኅዳር 24 2017

በያዝነው ዓመት በዓለም አቀፍ ደረጃ ኤች አይቪ ኤይድስ በታሰበበት ዕለት፤ «ኤድስ እንዲያበቃ ትክክለኛውን መንገድ እንከተል» የሚለው መልእክት ተላልፏል። ምንም እንኳን ዛሬ በኤች አይቪ ምክንያት ሕይወታቸው የሚቀጠፈው ሰዎች ቁጥር መቀነሱ ቢነገርም የተሐዋሲው ስርጭት ግን አሁንም አልተገታም።

https://p.dw.com/p/4nhih
የሙኒክ የዓለም የኤድስ ጉባኤ
በጀርመን ሙኒክ ከተማ የዓለም የኤድስ ቀን የተካሄደውን ጉባኤ መራሄ መንግሥት ኦላፍ ሾልስ ከፍተውታል። ምስል Sabine Dobel/dpa/picture alliance

ጤና እና አካባቢ

 

ኤች አይቪ ኤይድስ በመላው ዓለም ከ42 ሚሊየን በላይ ለሚሆኑ ሰዎች ሕይልፈተ ሕይወት ምክንያት እንደሆነ UNAIDS ሰሞኑን ይፋ አድርጓል። ባሳለፍነው እሑድ ዕለት በዓለም አቀፍ ደረጃ ኤች አይቪ ኤይድስ ሲታሰብ፤ በመጪው ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት 2030 ኤድስ የጤና ስጋትነቱ እንዲያበቃ አሁንም በጋራ በቁርጠኝነት መሥራት ያስፈልጋል ነው የተባለው። «ኤድስ እንዲያበቃ ትክክለኛውን መንገድ እንከተል» ነው የዘንድሮው መሪ ቃል። 

ዓለም አቀፍ ይዞታ

በመላው ዓለም በኤች አይቪ ኤይድስ ምክንያት የሚከሰተው ሞት በ70 በመቶ መቀነሱን የUNAIDS ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አንጀሊ አሺከር ሰሞኑን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ይፋ አድርገዋል። በመላው ዓለም ከ30 ሚሊየን በላይ ሰዎች መድኃኒት በመውሰድ ላይ መሆናቸውንም በአዎንታዊነት አንስተዋል። እንዲያም ሆኖ ግን ዛሬም የዓለም ኤድስ ቀን ሲታሰብ በዚህ ምክንያት የረገፉትን ከ42 ሚሊየን በላይ የሚሆኑ ወገኖችን ማሰብ ይገባል ነው ያሉት።

ኤችአይቪ በደማቸው ውስጥ የሚገኝ ወገኖች የሚወስዷቸው መድኃኒቶች እየተሻሻሉ፤ ማለትም ቀደም ባሉት ጊዜያት በርከት ያሉ እንክብሎችን መውሰዱ እየቀነሰ በቀን አንድ ኪኒን ብቻ ከሚወሰድበት ደረጃ ተደርሷል። መድኃኒቱን ለማሻሻልም ጥናቶችና ሙከራዎች ቀመጠላቸውም ይነገራል።  

ኢትዮጵያ

ኢትዮጵያ ውስጥ የጤና ሚኒስቴር ከኅብረተሰብ ጤና ተቋም ጋር ያስጠናው ጥናት በሀገሪቱ በኤችአይቪ ተሐዋሲ በአሁኑ ጊዜ ከሚያዙት መካከል 70 በመቶ የሚሆኑት በአፍላ እድሜ ላይ ያሉ ወጣቶች መሆናቸውን ማመላከቱ ተገልጿል። ከተጠቀሱት አፍላ ወጣቶች በቁጥር የሚበዙት ሴቶች ወጣቶች መሆናቸውም ነው የተነገረው።

ይህን በመጥቀስ ያስተዋሉትን እንዲያጋሩን የጠየቅናቸው፤ በአዲስ አበባ ዘውዲቱ መታሰቢያ ሀኪም ቤት በኤች አይቪ ላይ ለረዥም ዓመታት የሠሩት የህክምና ባለሙያ ዶክተር አስቴር ሸዋአማረ፤ እንዲህ ያሉትን አጠቃላይ መረጃዎች የሚገልጽ አካል መኖሩን በመጠቆም፤ መድኃኒት ለመውሰድ ወደ እነሱ የሚሄዱት ሴቶችም ወንዶችም፤ አዋቂዎችም ወጣቶችም ናቸው ይላሉ። ዛሬም ቢሆን ሰው እራሱን ሊጠብቅ ይገባል ያሉት ዶክተር አስቴር አሁንም ቢሆን በኤችአይቪ ምክንያት የሚሞት ሰው መኖሩንም አመልክተዋል። መድኃኒቱን የሚወስዱ ሰዎች በጤናማነት ሲንቀሳቀሱ መመልከቱ የመዘናጋት አዝማሚያን ሊያስከትል እንደሚችልም ነው የጠቆሙት ባለሙያዋ።

ኢትዮጵያ ውስጥ በበሽታዎች ክትትና ቅኝት በየወሩ ዘገባ ይፋ ከሚደረግባቸው በሽታዎች አንዱ መሆኑን ነው ዶክተር መሳይ ኃይሉ የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ተቋም ዋና ዳይሬክተር የተናገሩት። እሳቸው እንደገለጹትም ከ800 በላይ በሚሆኑ ጤና ተቋማት ላይ ኤችአይቪን በተመለከተ በጣም ጥልቅ የሆኑ የቅኝት መረጃዎች ትንተናም ይሠራል። በዚህ መሠረትም ተሐዋሲው በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ ያለበት ደረጃ የመለየት፤ ያንን ትኩረት ያደረገ የምላሽና የመከላከል ስልቶችን የመቀየስ እንዲሁም የመተግበር እንቅስቃሴዎች እንደሚከናወኑም አመልክተዋል።  

የዓለም ኤች አይቪ ኤድስቀንን ምክንያት በማድረግ የጤና ሚኒስቴር ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት የኤች አይ ቪ ስርጭት በጎርጎሮሳዊው 2010 ከነበረበት 1.26 በመቶ አሁን ወደ 0.87 በመቶ ዝቅ ብሏል። ለዚህ ደግሞ የመድኃኒት አቅርቦት እየተሻሻለ መምጣቱና በተፈለገበት አጋጣሚ የመገኘቱ እድል መኖሩ እንደሆነ ነው የተገለጸው። ዶክተር አስቴር እንደገለጹን ኢትዮጵያም ውስጥ ሁኔታው ተመሳሳይ ነው።

ምንም እንኳን የመድኃኒቱ አቅርቦት በተሻለ ደረጃ ላይ መገኘቱ በችግሩ ውስጥ ላሉት ወገኖች አዎንታዊ ቢሆንም መድኃኒት አለ በሚል መዘናጋት መኖሩ ግን ይነገራል።

የተቀዛቀዘው የግንዛቤ ማስጨበጫ እንቅስቃሴ

ቀደም ባሉት ዓመታት ሀገራዊ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትና ተሐዋሲው በደማቸው ውስጥ የሚገኝ ወገኖች ያቋቋሟቸው ማኅበራት ኅብረተሰቡን በማንቃትና በማስተማሩ ረገድ የሚታይና ንቁ እንቅስቃሴዎችን ያደርጉ ነበር። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን እንዲህ ያሉት እንቅስቃሴዎቻቸው አይታዩም፤ ምናልባት ለመዘናጋቱም ሆነ በተለይ በእድሜ ለጋ የሆኑት ወጣቶች ለዚህ ተጋላጭነታቸውን አስፍቶት ይሆን? 

«ትክክለኛውን መንገድ ተከል»
lከዘንድሮው የዓለም የኤድስ ቀን መሪ ቃሎች «ትክክለኛውን መንገድ ተከል» የሚለው አንዱ ነው። ምስል UNAIDS

በደቡባዊ ኢትዮጵያ ኤች አይቪ በደማቸው የሚገኙ ማኅበራት ጥምረት ፕሬዝደንት በተለይ በደቡባዊ ኢትዮጵያ በሦስት ክልሎች ውስጥ ያሉት ማኅበራት በአዲስ አደረጃጀት በደቡብ ኢትዮጵያ፤ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ፤ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ እና ሲዳማ በጥቅሉ በአራት ክልሎች ውስጥ የሚገኙ ማኅበራት ስብስብ ነው። የዚህ ስብስብ ፕሬዝደንት የመቶ አለቃ ይስሐቅ ታንጋ፤ ጥምረቱ በደቡባዊ ኢትዮጵያ የሚንቀሳሱ 89 ማሕበራትን እንደያዘ ነው የገለጹልን። በማሕበራቱ ውስጥም ባጠቃላይ 68,535 የሚሆኑ HIV በደማቸው የሚገኝ ወገኖች ይገኛሉ። ጥምረቱ በአራቱም የደቡባዊ ኢትዮጵያ ክልሎች የሚያከናውናቸውን ተግባራትም ዘርዝረዋል።

ከግሎባል ፈንድ በሚያገኙት የገንዘብ ድጋፍ ከመንግሥት ተቋማት ጋር አብረው እንደሚሠሩ ያመለከቱት መቶ አለቃ ይስሐቅ፤ በዋናነት መድኃኒት የሚወስዱ HIV በደማቸው የሚገኝ ወገኖች እንዳያቋርጡ ክትትል እንደሚያደርጉም አስረድተዋል። ምንም እንኳን የማሕበራቱ እንቅስቃሴ ባይቆምም ቀደም ባሉት ዓመታት ይታይ የነበረው የማስተማርና የማንቃት ሥራ ደብዝዟል፤ ለምን ይሆን? የመቶ አለቃ ይስሐቅ እንደሚሉት በአሁኑ ጊዜ እንዲህ ላሉት ማኅበራት የሚደረገው ድጋፍ ያን ያህል አይደለም። እንዲያም ሆኖ ግን ማሕበራቱ በሚችሉት አቅም እየተንቀሳቀሱ ነው ባይ ናቸው።

የኤች አይቪ ስርጭት ማንሰራራት

ኢትዮጵያ ውስጥ ከ500 ሺህ በላይ ኤች አይቪ ተሐዋሲ በደማቸው የሚገኝ ወገኖች መኖራቸውን፤ በደቡባዊ ኢትዮጵያ ክልል ውስጥ ያሉት ከ68 ሺህ በላይ መሆናቸውን፤ ከእነዚህ ውስጥ 54,630 የሚሆኑት ተመርምረው ራሳቸውን ያወቁ መሆናቸውን፤ 52,055ቱ ደግሞ መድኃኒት የሚወስዱ እንደሆኑ ነው የገለጹልን።

UNAIDS እንዳመለከተው በአሁኑ ወቅት የHIV ተሐዋሲ ስርጭት በወጣቶች አካባቢ መጨመሩ እየታየ ነው። በ28 ሃገራት ውስጥ ደግሞ በጥቅሉ የተሐዋሲው ስርጭት ከፍ ብሏል። 40 ሚሊየን ገደማ ሰዎችም ከተሐዋሲው ጋር ይኖራሉ፤ ከእነዚህ መካከልም 9,3 ሚሊየኑ መድኃኒት አሁንም የሚያስፈልጋቸው ናቸው።

በነገራችን ላይ አድማጮች ይህን መሰናዶ ሳዘጋጅ እንደተለመደው መረጃዎችን ይሰጡኝ ከነበሩ ወገኖች የተወሰኑትን በሕይወት አላገኘሁም። ስልኮቻቸውን በቤተሰቦቻቸው እጅ በመሆናቸው በእነሱ አማካኝነት ከዚህ ዓለም ድካም ማረፋቸውን ተረዳሁ። እነዚህ ወገኖች ሌሎች እነሱ የገጠማቸው የሕይወት ዕጣ ፈንታ እንዳያጋጥማቸው አደባባይ ወጥተው በእኛ ይብቃ ትውልድ ይዳን! በማለት በተለያዩ መድረኮችና በመገናኛ ብዙሃን ስለኤችአይቪ ተሐዋሲ የስርጭት መንገዶች ያለማሰለስ ያስተምሩ ይመክሩ ነበር። ነፍሳቸው በሰላም ትረፍ! ለዚህ ዝግጅት ማብራሪያ የሰጡንን እናመሰግናለን።

ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ