1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አብነት ዴላሞ፤ የተራቆተውን አከባቢውን የቀየረው ወጣት

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 15 2017

የተሻለ ኑሮን ለመያዝ የግድ ከተሜ መሆን አያሥፈልግም ያለው አብነት «እኔ ከተማ አካባቢ የነበርኩ ሰው ነኝ፡፡ ብዙዎች ምቾት ፍለጋ ወደ ከተሞች የመሄድ ዝንባሌ ይስተዋልባቸዋል፡፡ ከተሠራ መለወጥ የማይቻል ነገር የለም ብዬ አምናለሁ። በራስ ጥረት አካባቢንና ጓሮን በመለወጥ ለኑሮም ሆነ ለሥራ ተስማሚ ማድረግ እንደሚቻል ማረጋገጥ ችያለሁ»ብሏል፡፡

https://p.dw.com/p/4oWc9
አርሶአደር ወጣት አብነት ዴላሞ
አርሶአደር ወጣት አብነት ዴላሞ ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

የተራቆተውን አከባቢውን የቀየረው ወጣት አርሶ አደር አብነት ዴላሞ

ከባቢውን የቀየረው ወጣት 

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በታላቁ ስምጥ ሸለቆ ጫፍ የምትገኘው ሀሚዶ ቀበሌ ቆላማ የአየር ንብረት ይስተዋልባታል ፡፡ በክልሉ ከምባታ ዞን አዲሎ ወረዳ የምትገኘው ሀሚዶ ቀበሌ ነዋሪ ለሆነው ለወጣት አርሶአደር አብነት ዴላሞ ግን ነገሮች ተስፋ አላስቆረጡትም  ፡፡ ይልቁንም በቀበሌው የሚገኘውን ይዞታውን ለደን ልማትና ለአርሻ ሥራዎች አመቺ ወደሆነ ከባቢ ለመቀየር ከዓመታት በፊት የጀመረው ሥራ አሁን ላይ ውጤት ያስገኘለት ይመስላል ፡፡ባህላዊ የደን አጠባበቅ ስልት በጌዴኦ

የተቀናጀ የእርሻ አመራረት

ወጣት አርሶአደር አብነት ቀደምሲል እንደነገሩ የነበሩ ይዞታዎችን የተሻለ ጥቅም መስጠት ወደሚችሉበት ደረጃ ማሸጋገሩ ዛሬ ላይ  አካባቢው በበርካቶች በተሞከሮነት እንዲጎበኝ ምክንያት ሆኗል ። በአነስተኛ ይዞታ ላይ ከደን እስከ ምግብ ሰብል ፤ ከእንስሳት እርባታ እስከ አትክልትና ፍራፍሬ የሚታዩት ምርቶች የተቀናጀ የአመራረት ሥልትን የተከተሉ ናቸው ፡፡

በሀሚዶ ቀበሌ የሚገኘው ወጣቱ አብነት ዛፍ
በሀሚዶ ቀበሌ የሚገኘው ወጣቱ አብነት ዛፍምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

የአረንጓዴ ጀግናዋ ሱ ኤድዋርድስ
የተሻለ ኑሮን ለመያዝ  የግድ ከተሜ መሆን አያሥፈልግም የሚለው ወጣት አብነት  “ እኔ ከተማ አካባቢ የነበርኩ ሰው ነኝ ፡፡ ብዙዎች ምቾት ፍለጋ ወደ ከተሞች የመሄድ ዝንባሌ ይስተዋልባቸዋል ፡፡ ከተሠራ መለወጥ የማይቻል ነገር የለም ብዬ አምናለሁ ።በራስ ጥረት አካባቢንና ጓሮን በመለወጥ ለኑሮም ሆነ ለሥራ ተስማሚ ማድረግ እንደሚቻል በራሴ ማረጋገጥ ችያለሁ፡፡ ይህ ማለት ግን ሁሉም ነገር የተመቻቸ ነው ማለት አይደለም፡፡  እዚህ ለመድረስ ውጣ ወረዶች ነበሩት “ ብሏል ፡፡

የወጣት አብነት ዴላሞ አረንጓዴ መንደር
የወጣት አብነት ዴላሞ አረንጓዴ መንደርምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

የወጣቱ ጥረት እንደተሞክሮ

ወጣት አብነት በሀሚዶ ቀበሌ የተራቆተ አካባቢን በመቀየር ለግብርና ሥራዎች ምቹ ያደረገው በአቅራቢያው የሚገኘውን ወንዝ ስቦ ወደ ማሳዎች በማምጣት ነው ፡፡ ይህ በግብርናው ዘርፍ ትልቅ ተሞክሮ መሆኑን ሰሞኑን አካባቢውን የጎበኙት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ ሃላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር ገልጸዋል ፡፡ ውሃን ከርቀት ስቦ ለእርሻ ሥራ በማዋል  የተሠራው ሥራ ትልቅ አስተምሮ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ኡስማን “ አንዳንድ አርሶአደሮች ውሃ በአጠገባቸው እየፈሰሰ የማይጠቀሙ አሉ ፡፡ እነኚህ አርሶአደሮች ይህን አይተውና ተምረው ራሳቸውን ከድህነት መውጣት ይገባቸዋል ፡፡

ለዚህ ደግሞ በሀሚዶ ቀበሌ የሚገኙ ሌሎች አርሶአደሮች በአካባቢ ጥበቃና በግብርና ሥራ ከወጣት አብነት ተሞክሮ ለመውሰድ የተጀመሩ ጥረቶች መጠናከር አለባቸው  “ ብለዋል ፡፡አሁን መንግሥት ለያዘው ዓላማ ትልቁ እንቅፋት በመስክ ላይ የልማት ጣቢያ አለመጠናከርና በመስክ ላይ ምርምር ለማድረግ የሚያስችል ሁኔታ አለመኖሩ መሆኑን የሚናገረው ወጣት አብነት “ በእኛ በኩል አርሶአደሩ የልምድ ልውውጥ የሚያደርግበትን አንድ ሄክታር መሬት አዘጋጅተናል ፡፡ በዚህ ሥፍራ ለግብርና ምርምርና የልምድ ልውውጥ ለማከናወን የሚያገለግል ማዕከል አዘጋጅተናል “ ብሏል ፡፡

 “አገር አቀፍ የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ” እና የእንክብካቤ ጥያቄ

ሸዋንግዛው ወጋየሁ
ኂሩት መለሰ