1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ዓርብ፣ ጥር 3 2016

«ይህ ቲያትር የታገደው በግለሰቦችም ይሁን በተቋም ተቀባይነት የሌለው የቁልቁለት መንገድ ነው።የሃሳብ ገበያውን መዝጋት፤ የጉልበት እና የጠመንጃ ገበያውን ከማስፋፋት ያለፈ ፋይዳ የለውም።»በማለት ጠንከር ያለ አስተያየት ፅፈዋል።

https://p.dw.com/p/4bAyF
የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች
የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎችምስል Nicolas Economou/NurPhoto/picture alliance

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት


 የዛሬው የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት ዝግጅት የትምህርት ሚንስቴር የዩንቨርሲቲ ተማሪዎች ወደ አማራ ክልል እንዲሄዱ ውሳኔ ማሳለፉ፣ እያዩ ፈንገስ «ቧለቲካ» የተባለው ቲያትር መታገዱ እና የወደብ አጠቃቀም ስምምነቱን ተከትሎ በሶማሊያ እና በሶማሌ ላንድ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጥቃት እየደረሰባቸው ነው በመባሉ ላይ የተሰጡ አስተያየቶችን ይዳስሳል።

በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል  በድሮን ጭምር የታገዘ  ውጊያ  ለወራት  እየተካሄደ  ባለበት  የአማራ ክልል፤ የትምህርት ሚንስቴር በክልሉ በሚገኙ ዩንቨርሲቲዎች ተቋርጦ የነበረው  የመማር ማስተማር ሂደት እንደገና እንዲቀጥል መወሰኑን ገልጿል።በክልሉ በሚገኙ የዩንቨርስቲዎች ትምህርታቸውን የሚከታተሉ ተማሪዎችም ወደ ክልሉ ሄደው እንዲመዘገቡ ሚንስቴር መስሪያ ቤቱ በቅርቡ አስታውቋል። ይህንን ተከትሎ ጉዳዩ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች መነጋገሪያ ሆኖ ነው የሰነበተው። 
መሰረት ሀይሉ የተባሉ አስተያየት ሰጪ «መንግስት ከለላ የሚያደርግ ከሆነ ጊዚያቸውን ተጠቅመው በተለይ ተመራቂዎች ተምረው ቢመረቁ ጥሩ ነው።ለረዥም ጊዜ መቀመጡ ለተማሪዎች የሥነ-ልቡናም ጫናው ቀላል አይደለም።»ብለዋል።
ሃና ነኝ  በሚል የፌስቡክ ስም የሰፈረው አስተያየት ደግሞ «እኔ እንደ ወላጅ ከትምህርቱ በፊት የልጆች ደህንነት ይቀድማል ባይ ነኝ።»ሲሉ፤ይህንኑ አስተያየት በመደገፍ «ማንም ወላጅ በዚህ ወቅት  ልጁን በመኪና ወደ ክፍለ ሀገር አይልክም።»ያሉት ደግሞ ካሌብ ገነቱ ናቸው።
 ቴዲ ማን በሚል የፌስቡክ ስም ደግሞ «ተምሮ ለመቀመጥ ይህን ያህል ዋጋ መክፈል አያስፈልግም።»የሚል አስተያየት ተሰጥቷል። ተሰማ ተገኘ «ቤተሰብ በፍፁም ልጁን መላክ የለበትም።» ብለዋል።

የኢትዮጵያ የትምህርት ምንስቴር ዋና ህንፃ አዲስ አበባ
የኢትዮጵያ የትምህርት ምንስቴር ዋና ህንፃ አዲስ አበባ ምስል Alemnew Mekonnen/DW

ሳልሳዊ ሳልሳዊ የተባሉ የፌስ ቡክ ተከታታይ ደግሞ «ከዚህ በፊት በተለያዩ ዩንቨርስቲዎች አደጋ የደረሰባቸው እና ታግተው ደብዛቸው የጠፉ ተማሪዎች ላይ መንግስት ምንም ሳይል አሁን በማን ኪሳራ ፖለቲካ ለመስራት ነው ልጆቻችሁን ውጊያ ወዳለበት ክልል ለኩ የሚለው።» የሚል አስተያየት ሰጥተዋል።
አንማው ሰኢድ«ክልሉ ሰላም ነው። ሟርተኞች የሚሉትን አትስሙ።»ሲሉ፤ቀን ያልፋል በሚል የፌስቡክ ስም ደግሞ «የክልሉ ህዝብ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ እንደልቡ የማይዘዋወርበት ሁኔታ ተፈጥሮ እያለ ተማሪዎችን ሂዱ ማለት ቀልድ ነው።»የሚል ምላሽ ተሰጥቷል። 
ሱፐር ኪንግ ጥላሁን በሚል ስም ደግሞ «ከዚህ በፊት በትግራይ በነበረው ጦርነት እኮ የዩንቨርሲቲ ተማሪዎችን የትግራይ ህዝብ ጠበቃቸው እንጅ መንግስት እማ ትቷቸው ነው የወጣ። ሾርት ሚሞሪዎች አይደለንም» የሚል አስተያየት አስፍረዋል።
«ሰላም ሆኖ ወደ ትምህርት ገበታ ቢመለሱ እሰየው ነበር።ግን ምን ያደርጋል» ።ያሉት ደግሞ ወንድወሰን ወርቁ  ናቸው።

ሌላው በዚህ ሳምንት በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች አነጋጋሪ ከነበሩ ጉዳዮች አንዱ በኢትዮጵያ  የመጀመሪያው ነው የሚባለው የአንድ ሰው የሙሉ ጊዜ ቴአትር የሆነው እያዩ ፈንገስ "ቧለቲካ" ቴአትር ታገደ መባሉ ነው። በበረከት በላይነህ ተደርሶ በጥበብ ሰው ግሩም ዘነበ ብቸኛ ተዋናይነት ዘወትር ሀሙስና እሁድ በዓለም ሲኒማ እየታየ የነበረው ይህ ቲያትር የመንግስት የፀጥታ አካላት ለዓለም ሲኒማ የሥራ ኃላፊዎች ባስተላለፉት ትዕዛዝ ከትናንት ሀሙስ ጀምሮ  ለህዝብ እንዳይታይ ተከልክሏል መባሉን በዚሁ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተመልክተናል።ይህንን ተከትሎ ጉዳዩ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች  በሁለት ጎራ ከፍሎ አከራክሯል።በዓለም ሲኒማ ሲታይ የነበረው የእያዩ ፈንገስ “ቧለቲካ” ቴአትር ታገደ
ፓውሎስ ግርማ «ባይታገድ ነው የሚገርመው»ሲሉ፤አሸናፊ አሰፋ «መንግስት ሀሳብ መፍራት ጀምሯል።ይህ  ህዝብን መተንፈሻ ማሳጣት ነው ።አንድን ነገር ስታፍነው መቼ እንደሚፈነዳብህ አታውቅም።»የሚል አስተያየት አስፍረዋል።

የእያዩ ፈንገስ “ቧለቲካ” በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኘው ዓለም ሲኒማ በሣምንት ሁለት ቀናት ሲታይ ቆይቷል
የእያዩ ፈንገስ “ቧለቲካ” በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኘው ዓለም ሲኒማ በሣምንት ሁለት ቀናት ሲታይ ቆይቷልምስል DW

ቅዱስ ማርቆስ ሂርፓ «መታገድ አለበት ሁሉም እየተነሳ መንግስትን መተችት ሆነ ኢትዮጵያ ውስጥ። ሀገር የጠ/ሚ ብቻ መስለህ?»ብለዋል።
ኤርሚያስ ከብራ «ኑሮ አይታደግብኝ እንጂ» ሲሉ፤አሜን ዓለሙ ደግሞ «እኛንስ መች ነው የሚያግዱን?»በማለት ነገሩን ወደ ቀልድ ወስደውታል። ሻፊ ደሊል «በነገራችን ላይ ትክክል ናቸው። የነሱን ቲያትርስ ማን ያይላቸዋል።»ሲሉ፤ ዛሬ ምን አለ በሚል የፌስቡክ ስም የሰፈረው አስተያየት ደግሞ«ሰው ኑሮ ውድነቱንና ብሶቱን በቴያትር እንኳን ቢተነፍስ ምን አለበት»ብለዋል።ቴድሮስ አምደፅዮን«አሽሙር እና በማላገጥ ሳይሆን ስራ እና ለውጥ ነው ሀገሪቱ የምትፈልገው።»የሚል አስተያየት ሰጥተዋል።

እዮብ ገዛኸኝ «ችግርን ማውራት መፍትሔ አያመጣም የአገራችን አርቲስቶች ችግር አውሪ እንጂ መፍትሔ አምጪዎች አይደሉም። ይህ ሕዝብ ደሞ የሚያክለት ይፈልጋል እውነትን ተጋፍጦ ማሸነፍ ያደክመዋል።እንኳን ታገደ!!!!»በማለት አስተያየት ሰጥተዋል።መስፍን እዮብ በበኩላቸው «አርቲስቶቻችን እኮ ያለውን ችግር በጥበብ አዋዝተው ማቅረብ እንጂ እንዴት መግባት የማይችሉበት ቦታ ገብተው መፍትሔ ያመጣሉ። ያለውን ሁኔታ እየተጋፈጡ ሳይፈሩ መንቀፍ ያለባቸውን ለሚነቅፋ አድር ባይ ላልሆኑ ከመጣው ከሄደው ጋር ለማይገለባበጡ ምስጋና ና ክብር ይገባቸዋል።»ሲሉ ሞግተዋል።«እያዩ ፈንገስ» ባለአንድ ገጸባሕሪ ተውኔት
ታሪክ ይለወጣል በሚል የፌስቡክ ስም ደግሞ «ያው ኑሯችንም ትያትር ነው።»የሚል አስተያየት ሰፍሯል። ራምፍ ሮቤል «ትያትር ቤቶች መዝናኛ እንጂ የጦርነት መጎሰሚያ፣የዘረኝነት መዕከል መሆን የለባቸውም፤ስለዚህ ትክክል ነው።»ሲሉ ፤ነጻ እመኑ «እያዩ ጦርነት አልጎሰመም፣ ዘረኝነትን አልሰበከም። ሀቅና እውነት ነው ያነሳው።» በማለት መልስ ሰጥተዋል።
ኡሉማ ኤም ወዳጆ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ «አንድ መንግስት ቲያትር፣ ሙዚቃ፣...የመሳሰሉትን የሃሳብ ገበያዎች ማገድ ከጀመረ፤ እጅጉን ከሰረ! ማገድ የመሸነፍ...ተሸንፎም...ልጆች ሆነን እንደምንለው "እፍርታም" መሆን ነው! ይህ ቲያትር የታገደው በግለሰቦችም ይሁን በተቋም ተቀባይነት የሌለው የቁልቁለት መንገድ ነው።የሃሳብ ገበያውን መዝጋት፤ የጉልበት/የጠ'መንጃ ገበያውን ከማስፋፋት ያለፈ ፋይዳ የለውም! ዜጎች በሰላማዊ መንገድ ሐሳባቸውን የሚገልፁበትን እና የሚገበያዩበትን መንገድ ሁሉ እየዘጉ፤ "እነ እከሌ ጦርነት ከፈቱብኝ" ማለትም አያስኬድም።»በማለት ጠንከር ያለ አስተያየት ፅፈዋል።

በኢትዮጵያ እና እንደ ሀገር  እውቅና ባላገኘችው ሶማሊላንድ መካከል በቅርቡ የተፈራረሙት  የወደብ አጠቃቀም የመግባቢያ  ስምምነት በዚህ ሳምንትም ማነጋገሩን ቀጥሏል።
ያለ በቂ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት የተደረገ ተብሎ በመተቸት ላይ ያለው ይህ ስምምነት በሶማሊላንድ እና በሶማሊያ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በሀገሬው ህዝብ በክፉ እንዲታዩ አድርጓል ተብሏል። 
ዘገባዎች እንደሚያሳዩት በሁለቱ ሀገራት በሚኖሩ በኢትዮጵያውያን ላይ ስምምነቱ ከተፈረመ ወዲህ አካላዊ ጥቃት፣ የንብረት መዘረፍና ዛቻ እየደረሰባቸው ነው። 

የኢትዮጵያ እና የሶማሌ ላንድ መሪዎች  የወደብ አጠቃቀም ስምምነት የመግባቢያ ሰነድ ሲፈራረሙ
የኢትዮጵያ እና የሶማሌ ላንድ መሪዎች የወደብ አጠቃቀም ስምምነት የመግባቢያ ሰነድ ሲፈራረሙምስል TIKSA NEGERI/REUTERS

በሶማሊያ የሚኖሩ ከፍተኛ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጭምር የተሳተፉበት በተባለው ዘመቻ ኢትዮጵያውያን ከሃገሪቱ እንዲባረሩ  በመገናኛ ብዙሃን ከፍተኛ ቅስቀሳ እየተካሄደ ነው ተብሏል። በዚህ የሰጉ ኢትዮጵያውያንም መንግስት አስፈላጊውን ክትትል በማድረግ ዜጎቹን እንዲታደግ እየጠየቁ ነው። 
 ይህንን ተከትሎ ቢታንያ «እንኳን በሰው ሀገር፤ መንግስት በሀገር ውስጥ ያሉትንም ከጥቃት አልተከላከለ»ሲሉ፤አባይ ታደሰ «አይደለም በዜጎች ላይ የፈለገው ቢመጣ የባህር በር ያስፈልገናል ።»በማለት አስተያየት ሰጥተዋል።
ሹሩላ ሙዘይን  ደግሞ «ከሞቋድሾ ውጪ ማንም አልነካቸውም።የሶማሌ ላንድ ፓርላማም በሙሉ ድምፅ ተቀብሎ አፅድቆታል። የዲፕሎማሲውም ስራ የሚደነቅ ነው።»
አዛሪያ አራጌ«እኔ የምኖረዉ እዛዉ አካባቢ ነዉ ከሶማሊያ እያስወጡ ነዉ።»ብለዋል።አብርሃም መንገሻ «ያለማስተዋል እና ግድየለሽነት ያመጣዉ ጣጣ።»ሲሉ፤አዋሽ ሽዋመኔ ደግሞ «ትንንሽ ነገሮች ይኖራሉ አሁን መመለስ አይቻልም አገራዊ ውርደት ያመጣል ።የሚጠበቅ ነው።»ብለዋል።
አይናለም አብርሃም ጥቃቱ አይደለም የገረማቸው «እኔን የገረመኝ ሶማሊያ ውስጥ ኢትዮጵያዊያን መኖራቸው ነው»ብለዋል። አበበ ታምሩ«በፖለቲካና የዲፕሎማሲ ስህተት በተፈጠረ ችግር በኢትዮጵያውያን ላይ አንዲህ አይነት አስከፊ በደል መድረሱ፣ ያሳዝናል፣።»ብለዋል።ቶሚ ማን « ያሳዝናል ፈጣሪ ይድረስላቸው።»ብለዋል።

በኢትዮጵያ እና በሶማሌ ላንድ የተፈረመውን የወደብ አጠቃቀም ስምምነት በመቃወም በሶማሊያ የተደረገ ሰልፍ
በኢትዮጵያ እና በሶማሌ ላንድ የተፈረመውን የወደብ አጠቃቀም ስምምነት በመቃወም በሶማሊያ የተደረገ ሰልፍ ምስል Farah Abdi Warsameh/AP/picture alliance

ሰለሞን ገብረ እግዚአብሄር «ለኢትዮጵያ የወደብ ስምምነት አስፈላጊና ወሳኝ ነው። በመሆኑም ለሚመጡ አንዳንድ ችግሮች ድንጋጤ ቢኖርም፤ ብዙ ቦታ መስጠት አያስፈልግም !!»ሲሉ ነገሩን አጣጥለውታል።የከርሞ ሰው «እስካሁን በሰሞኑ ጉዳይ ላይ መንግስት ከሶማሊያ መንግስት ጋር ሊነጋገር አልፈቀደም።በዚህ ጉዳይ ኦነግ መግለጫ አውጥቶ አይቻለሁ ።መንግስት ያን ያህል ያስጨነቀው አልመሰለኝም።»ሲሉ፤ ኢትዮጵያ ትቅደም የተባሉ የቲውተር ተከታታይ «ሶማሊያ የምትጠበቀው በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ነው።»በማለት ጉዳዩ እንደማያስጨንቅ ገልፀዋል።«ኢትዮጵያዊ በሀገሩም በሰው ሀገርም ተፈናቃይ መሆኑ ያሳዝናል።መንግስታችን ደግሞ ግድ አይሰጠውም።»ያሉት ደግሞ እዮባ እዮባ የተባሉ አስተያየት ሰጪ ናቸው።
ለሀቅ ልናገር በእንጝሊዝኛ በቱዊተር በፃፉት «ሶማሊያውያን  በዓለም ላይ ብዙ ቦታ ነው በስደት የሚኖሩት። ኢትዮጵያ ውስጥም ብዙ ስደተኞች አሉ።ስለዚህ ስደትን ያውቁታል እና ስደተኛን ማጥቃት ተገቢ አይለም።»ብለዋል። አቡ ፈውዛን ሀይክ«አላህ ያግራው እንጂ ነገሩስ ውስብስብ ነው።»የሚል አስተያየት ሰጥተዋል።

 

ፀሀይ ጫኔ
ማንተጋፍቶት ስለሺ