የተኩስ ልውውጥ በባሕር ዳር ከተማ
ዓርብ፣ የካቲት 22 2016
የአማራ ክልል ርዕሠ-ከተማ ባሕርዳር ዛሬ ከማለዳዉ ጀምሮ እስከ ማርፈጃዉ ዉጊያ ሲደረግባት አርፍዷል።የኢትዮጵያ መንግሥት በአማራ ክልል ላይ የጣለዉን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በቅርቡ ካራዘመ ወዲሕ በመንግስት የፀጥታ ኃይላትና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል በተለያዩ የአማራ ክልል አካባቢዎች የሚደረገዉ ዉጊያ ተጠናክሮ ቀጥሏል።ሰሞኑን በምዕራብ ጎጃመ ዞን በፈረስ ቤት፣ በሰሜን ሸዋና በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር አንዳንድ አካባቢዎች ዉጊያ ሲካሄድ ነበር፡፡ ዛሬ ባሕርዳር ዉስጥ እስከረፋዱ በቀጠለዉ ዉጊያ በሰዉ ሕይወት፣አካልና በንብረት ላይ የደረሰዉ ጉዳት መጠን በዉል አልታወቀም።የባሕርዳሩ ወኪላችን ዓለምነዉ መኮንን ዝርዝር ዘገባ ልኮልናል።
ዛሬ ከጠዋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ እስከ ረፋድ 4 ሰዓት አካባቢ የዘለቀ የተኩስ ልውውጥ በባሕርዳር ከተማ ሲደረግ አርፍዷል፣ በተኩስ ለውውጡ የከባድ መሳሪያዎች ድምፅም ይሰማ ነበር፡፡ የተኩስ ልውውጡን ተከትሎ ነዋሪዎቹ ከቤታቸው ሳይወጡ ሁኔታዎችን ሲከታተሉ ማርፈዳቸውን ዶይቼ ቬሌ ተመልክቷል፡፡
የተኩስ ልውውጡ በዋናነት በከተማው ቀበሌ 14ና በተለምዶ ዓባይ ማዶ በተባሉት የከተማው አካባቢዎች እንደነበር ነዋሪዎቹ አመልክተዋል፡፡አንድ የባህር ዳር ከተማ ነዋሪ ለዶይቼ ቬሌ እዳሉት ሰው በየቤቱ በርአፍ አካባቢ ከመንቀሳቀስ ውጪ ርቆ መሄድ አልቻለም፡፡
ነገሮችን በእርቀት ሲከታተሉ እንደነበርና 4 ሰዓት አካባቢ ተኩሱ መብረዱን ገልፀዋል፣ የጉዳት ሁኔታውንም መውጣት ባለመቻሉ አይታወቅም ብለዋል፡፡
ሰላማዊ እንቅስቃሴ የለም
በባሕር ዳር ከተማሁሉም ዓይነት እንቅስቃሴዎች የሉም፣ የመንግስት ሰራተኞች ወደ ቢሮ አልገቡም ተማሪዎችም ወደ ትምህርት ቤት አልተንቀሳቀሱም፡፡ ከነበረው የተኩስ ልውውጥ ጋር ይገናኝ አይገናኝ ባይታወቅም፣ ዛሬ ከሰዓ በፊት በነበረው ጊዜ አውሮፕላኖች ከባሕር ዳር አየር ማረፊያ ሲወርዱም ሆነ ሲነሱ አላየንም፣ አንዳንድ ብዙሀን መገናኛ ተቋማትም ይህን ዘግበዋል፡፡እንዲሁም በነበረው የተኩስ ልውውጥ በሰዎችና በንብረት ላይ የደረሰውን ጉዳት ማወቅ አልተቻለም፡፡
የሌሎች አካባቢዎች ዉጊያና ዉጥረት
ይህ በእንዲህ እንዳለ ሰሞኑን ውጊያ በነበረባት የምዕራብ ጎጃም ዞን ፈረስ ቤት ከተማ የተኩስ ድምፅ ባይሰማም ውጥረት እንዳለ አንድ የከተማዋ ነዋሪ አመልክተዋል፣ የተሸከርካሪ እንቅስቃሴም የለም ነው ያሉት፡፡
እንደነዋሪው፣ ሰው በእግር ወዲያ ወዲህ መንቀሳቀስ ቢችልም ምንም ዓይነት ተሸከርካሪ ወደ የትኛውም አቅጣጫ አይሄድም ሲሉ አስረድተዋል፣ ሆኖም ህዝቡ “ነገ ምን ይመጣ ይሆን?” በሚል ስጋት ውስጥ እንደሆነ ነው ያብራሩት፡፡
በሰሜን ሸዋ ዞን የአጣዬ ከተማ ነዋሪ በአካባቢው አሁን የተረጋጋ ሁኔታ ቢኖርም የትራንስፖርት አገልግሎት ካለፈው የካቲት 16 ቀን ጀምሮ በመዘጋቱ ግን ሰዎች ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሰው ስራ መስራት አልቻሉም ብለዋል፡፡
በአማራ ክልል ካለፈው ነሐሴ መጨረሻ ጀምሮ በፋኖ ታጣቂዎችና በኢትዮጵያ የፀጥታ ኃይሎች መካከል በተነሳው ጦርነት በርካታ ሰዎች መገደላቸውንና የአካል ጉዳት መድረሱን የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ገልፀዋል::በተከሰተው የፀጥታ መደፍረስ ምክንያት የአማራ ክልል ከሐምሌ 2015 ጀምሮ ለ6 ወራት በአስቸኳ ጊዜ አዋጅ ስር ቆየ ሲሆን የጊዜ ገደቡ ከተጠናቀቀ በኋላም አዋጁ ሰሞኑን ለሌላ የ4 ወራት ጊዜ እንዲራዘም ተወስኗል፡፡
ባለስልጣኑ ተገደሉ
በሌላ ዜና ትናንት በአማራ ክልል የወልዲያ ከተማ አገልግሎት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ዓለማየሁ ካሳሁን ባልታወቁ ታጣቂዎች መገደላቸውን ከሟች ጓደኞች አንዱ አመልክተዋል፡፡ተጠርጣሪዎቹ በባለሶስት እግር (ባጃጅ) ተሽከርካሪ ሆነው “ሆርማት”ግድያውን በተባለ አካባቢ መፈፀማቸውንና ለጊዜው ማምለጣቸውን እኚሁ አስተያየት ሰጪ ገልፀዋል፡፡
ሌላው ጓደኛቸው “በ30ዎቹ መጀመሪያ የእድሜ ክልል ይገኛሉ” ያሏቸው አቶ ዓለማየሁ ሙስናን ይታገሉ እንደነበር ጠቅሰው ግድቸውም ከዚህ ጋር ሳይያያዝ አይቀርም የሚል ግምት እንዳላቸው ተናግረዋል፣ በሰው እጅ የተገደሉት ጓደኛቸው ቀብርም ትናንት በወልዲያ በቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን መፈፀሙን አመልክተዋል፡፡
ዓለምነዉ መኮንን
ነጋሽ መሐመድ
ማንተጋፍቶት ስለሺ