1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአማራ ክልል ስምምነቱን ገቢር ለማድረግ ቃል ገባ

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 29 2015

ስምምነቱ ለትግራይና ለአማራ ህዝቦች እንደ ዳግም ትንሣኤ ይቆጠራል ያለው የአማራ ክልል መግለጫ፣ ከቂምና ከቁርሾ የዘለለ ኅብረትን፣ አንድነትንና የጋራ እሴትን በጋራ የሚያያዳብሩበት መሰረት እንደሚሆንም አመልክቷል።

https://p.dw.com/p/4JCxd
Ätiopien  Tigray  Meeting Nairobi
ምስል African Union

«ከስምምነቱ አንቀፆች አንዳዶቹ ግልፅ አይደሉም»የባሕር ዳር ነዋሪ

በደቡብ አፍሪካ ለተደረገው የሰላም ስምምነት ተግባራዊነት እንደሚሠራ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት አስታወቀ። የክልል መንግሥት ትናንት ባወጣው መግለጫ የትግራይና የአማራ ክልሎች ህዝቦች የወንድማማችነትና የእህትማማችነት ትስስር ተጠናክሮ እንዲቀጥል የክልሉ መንግስት ቀደም ሲልም ትኩረት ሰጥቶ ሲሰራ እንደነበር አመልክቷል፣ የስምምነቱ አንዳንድ አንቀፆች ተግባራዊነት እንደሚያጠራጥራቸው አስተያየት የሰጡ የባሕርዳር ከተማ ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡
የአማራ ብሔራዊ ክልለላዊ መንግስት ትናንት ባወጣው መግለጫ እንዳመለከተው በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ከተማ በአፍሪካ ህብረት አሸማጋይነት በኢትዮጵያ መንግስትና  በሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) መካከል የተደረገው የሰላም ስምምነት ተግባራዊ እንዲሆን ተግቶ ይሰራል፡፡
የሰላም ስምምነቱ ኢትዮጵያውያንንና ኢትዮጵያን አሸናፊ ያደረገ እንደሆነም መግለጫው አመልክተዋል፡፡
“የተደረገው የሰላም ስምምነት የዜጎችን ዘላቂ ሰላም በማስጠበቅ በጋራ ለመበልፀግ የሚያስችል መሰረት የጣለ ነው” ሲል ለሰላም ድርድሩ ውጤት ድጋፉን ገልጧል፡፡
ስምምነቱ ለትግራይና ለአማራ ህዝቦች እንደ ዳግም ትንሳኤ ይቆጠራል ያለው የአማራ ክልል መግለጫ፣ ከቂምና ከቁርሾ የዘለለ ህብረትን፣ አንድነትንና የጋራ እሴትን በጋራ የሚያያዳብሩበት መሰረት እንደሚሆንም አመልክቷል፡፡የአማራ ክልል መንግስት ከጥቅምት 24 ቀን፣ 2013 ዓ.ም በፊት ጀምሮም ቢሆን በአማራና በትግራይ ክልሎች ህዝቦች መካከል ለዘመናት የዘለቀው  የወንድማማችነትና የእህትማማችነት ባህላዊና መንፈሳዊ ትስስር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሲሰራ እንደነበርም አስታውሷል፡፡
“ በጦርነቱ ምክንያት የወደመውን የህዝብ ሀብት መልሶ ለመተካትና የዘላቂ መልሶ ግንባታ ሥራው እንዲፋጠን ለማድረግ ከምንግዜውም በላይ የተፈጠረውን የሰላም አየር ተጠቅመን መረባረብ ይኖርብናል” ሲል የአማራ ክልል መንግስት ጥሪውን አቅርቧል፡፡
መግለጫው የሰላም  ስምምነቱ ለአገር ሉዓላዊነትና ለግዛት አንድነት ወሳኝ ርምጃ መሆኑን ጠቅሶ በአገሪቱና በቀጠናው ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን በሚደረገው  ጥረት የክልሉ ህዝብ አስፈላጊውን ሁሉ እንዲያደርግም ክልላዊ መንግስቱ በመግለጫው ጠይቋል፡፡
መግለጫው ሁለቱ ክልሎች (አማራና ትግራይ) ስለሚወዛገቡባቸው የወልቃይትና የራያ አካባቢዎች እንዲሁም  ከኢትዮጵያ ከመከላከያ ሠራዊት ጎን ተሰልፈው በጦርነቱ ውስጥ ተሳትፎ ስለነበራቸው የክልሉ ኃይሎች ያለው ነገር የለም፡፡ ተጨማሪ አስተያየት ከክልሉ የኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊዎች ለማግኘት ያደረግሁት ጥረት ስልክ ባለመነሳቱ አልተሳካልኝም፡፡ 
አንድ የአማራ ክልል ነዋሪ የሰላም ስምምነቱን እንደሚደግፉ ገልፀው የስምምነቱ አንቀፅ 10፣ ቁጥር 4 ላይ   የይገባኛል ጥያቄ ስለሚነሳባቸው አካባቢዎች የተቀመጠው ሀሳብ ተግባራዊነቱ አጠራጣሪ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡የጃራ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው እየተመለሱ ነው
“… ግልፅነት የጎደለው አንድ የመደራደሪያ ሀሳብ ተቀምጧል፣ የግጭት ቀጠና የሆኑ አካባቢዎች ላይ ሕገመንግስታዊ በሆነ መልኩ ይፈታል የሚል፣ … የወልቃይትና የራያ ጉዳይ ደግሞ ከሕገመንግስቱ በፊት ፖለቲካዊ ውሳኔ ተወስኖ የሄዱ ቦታዎች ናቸው። ሕገመንግስቱ ከመረቀቁ በፊት በ”ሴራ” የተወሰዱ መሬቶችን በሕገመንግስቱ ይመለሳሉ ማለት ለእኔ አግባብ መስሎ አይታየኝም።”
ሌላ አስተያየት ሰጪ በበኩላቸው የሰላም ስምምነቱ ተግባራዊ የሚሆን ከሆነ ለትግራይ ህዝብና ለአጎራባች አካባቢዎች እፎይታን ይፈጥራል ብለዋል፡፡
 በአማራ ክልል በርካታ ጥፋቶች መከሰታቸውን ያነሱት አስተያየት ሰጪው ስምምነቱ ወደ ትጥቅ ማስፈታት ያተኮረ ቢሆንም የተጎዱ ትምህርት ቤቶች፣ ጤና ተቋማትና መሰረተ ልማቶች መኖራቸውን ተናግረዋል፣ በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖች የሚካሱበት መንገድ አልተቀየሰም፣ መንግስት በዚህ ረገድ ግልፅ ማድረግ ያለበት ጉዳዮች መኖራቸውን ጠቅሰዋል፡፡ ሆኖም በጦርነት አካባቢ ያሉ ሰዎች የጥይት ድምፅ እንዳይሰሙ መደረጉ መልካም ርምጃ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡በሰሜን ሸዋ ዞን የሚገኙ ተፈናቃዮች “የምግብ እጥረት አጋጥሞናል” አሉ፡፡
“ስምምነቶችን ለማየት ሞክሬያለሁ፣ … ይህ ይበል የሚያሰኝ ነው፣  የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ህዝብም የትግራይ ህዝብም ሰላማዊ እረፍት ማግኘታቸው፣ ወደ ማህበራዊ ኑሯቸው መመለሳቸው፣ ከጦርነትና ከጥይት ጩኸት ነፃ መሆናቸው እንደ አንድ ሰላም እንደሚፈልግ ግለሰብ እሰይ የሚያስብል ነው፣ ተፈፃሚነቱን እግዚአብሔር ያሳካው፣ ሰላም መዘመሩ፣ ፍትህ መዘመሩ፣ ጦርነት መቆሙ፣ ልጆች ከለቅሶ፣ ከርሀብ፤ እናቶች ከሰቆቃ፣ ከስደት መዳናቸው፣ የትግራይ ህዝብም ይሁን አጠቃላይ የኢትዮጵያ ህዝብ የሰላም መዝሙር መዘመር መቻላችንና መስማታችን ለተፈፃሚነቱ ያብቃን፡፡”
በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የተካሄደው የሰላም ስምምነት አንድ አካል የሆነና የሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ ታጣቂዎችን ትጥቅ ለማስፈታት የሚያስችል ውይይት በከፍተኛ ወታደራዊ አዛዦች ደረጃ ከትናንት ጀምሮ በኬንያ ናይሮቢ ከተማ እየተደረገ ነው፡፡
ዓለምነው መኮንን

Äthiopien - IDPs in Debark, Amhara Region
በጦርነቱ ከተፈናቃሉ ጥቂቱምስል Debark Woreda Food Security/Disaster prevention Office
በጦርነቱ ከተፈናቀሉ የአማራ ክልል ነዋሪዎች ገሚሱ ወደ ቀያቸዉ ሲመለሱ
በጦርነቱ ከተፈናቀሉ የአማራ ክልል ነዋሪዎች ገሚሱ ወደ ቀያቸዉ ሲመለሱምስል Sintayehu Seid/Alamata Youth League

ነጋሽ መሐመድ

ማንተጋፍቶት ስለሺ