የአውሮጳ ኅብረት በጋዛ ሰብአዊ ርዳታ እንዲደርስ የተኩስ ፋታ ጠየቀ
ዓርብ፣ ጥቅምት 16 2016የአውሮጳ ኅብረት መሪዎች ከትናንት ጀምሮ ለሁለት ቀናት ባካሄዱት ጉባኤ ለጋዛ ሰብአዊ ርዳታ እንዲደርስ ለማስቻል የተኩስ ፋታ መኖሩ ላይ ተስማምተው ውሳኔ አሳለፉ ። ሆኖም በዩክሬን ጉዳይ በአብዛኛው ወጥ አቋም ሲያንጸባርቁ የነበሩት የአውሮጳ ኅብረት አባላት በተኩስ ፋታው ጉዳይ መከፋፈል ታይቶባቸው ነበር። በተለይም ስፔንና አየርላንድ የመሳሰሉ አገሮች የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግና የሰብአዊ ርዳታ ወደ ጋዛ እንዲገባ የሚጠይቅ ውሳኔ እንዲተላለፍ ሲጠይቁ ነበር ። ጀርመንና ኦስትሪያን የመሳሰሉ አባል አገሮች በበኩላቸው የተኩስ ማቆሙ ጥያቄ የእሥራኤልን እራስን የመከላከል ዘመቻ የሚያደናቅፍ እንዳይሆን በመጠየቅ ሲከራከሩ ቆይተዋል።
27ቱ የአውሮጳ ኅብረት አገሮች መሪዎች ብራስልስ ውስጥ በተካሄደውና ዛሬ በተጠናቀቀው የሁለት ቀን ጉባኤያቸው፤ በጋዛ የሰብአዊ ርዳታ ለማድረስ የሚያስችል የተኩስ ፋታ እንዲኖር ጥሪ አቅረበዋል ። በዩክሬን ጦርነት ላይ አንድ አቋም በማራመድ የሚታወቁት የኅብረቱ መሪዎች በመካከለኛው ምስራቅ የሀማስ እስራኤል ጦርነት ላይ ግን ተለያይተው ሲወዛገቡ ነው የከረሙት።
ኅብረቱ በአጠቃላይ የሀማስን አሸባሪ ጥቃት በማውገዝ እስራኤል በጋዛ ላይ የምትወስደው ርምጃ አለማቀፍ ሕግን ያከበረ እንዴሆን የሚጠይቅ ነው ቢባልም፤ ይህ ግን በሁሉም አባል አገሮች በተመሳሳይ ስሜት ሲንጸባረቅ እንዳልታየ ነው የሚገለጸው። ሐማስ በአሜሪካ፣ በአውሮጳ ኅብረት፣ በጀርመን እና በሌሎች «አሸባሪ ድርጅት» በሚል የተሰየመ ድርጅት ነው ።
የኅብረቱ ተረኛ ፕሬዝደንት የሆነችው ስፔንና አየርላንድ የመሳሰሉ አገሮች የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግና የሰብአዊ ርዳታ ወደ ጋዛ እንዲገባ የሚጠይቅ ውሳኔ እንዲተላለፍ ሲጠይቁ ነበር ። ጀርመንና ኦስትሪያን የመሳሰሉ አባል አገሮች ደግሞ የተኩስ ማቆሙ ጥያቄ የእሥራኤልን እራስን የመከላከል ዘመቻ የሚያደናቅፍ እንዳይሆን በመጠየቅ ሲከራከሩ ቆይተዋል። መሪዎቹ ሁለት ቀን በዘለቀው ጉባኤያቸው ከረጅም ውይይትና ክርክር በኋላ ሀማስን በድጋሚ አውግዘውና እሥራኤልም እራሷን የመከላከል መብት ያላት መሆኑን ተቀብለዋል ። ሆኖም የእሥራኤል ርምጃ ሁሉ የዓለም አቀፍ ሕግን የተከተለ እንዲሆንና የሰብአዊ ርዳታ ለማድረስ የሚያስችል ፋታም እንዲኖር የሚጠይቅ ውሳኔ ያስተልለፉ መሆኑን የጉባኤው መሪና የካውንስሉ ፕሬዝድንት ሚስተር ቻርለስ ሚሸል ገልጸዋል ። «የሰብአዊ ርዳታ መተላለፊያ መንገድ እንዲከፈትና የስብአዊ ርዳታ ለማድረስ የሚያስችል ፋታ እንዲፈጠር የሚጠይቅ ውሳኔ አስተላልፈናል» በማለትም ውሳኔውን አረጋግጠዋል ።
የኮሚሽኑ ፕሬዝደንት ዑርዙላ ፎን ደር ላየንም ሃማስን ማውገዝና የእሥራኤልንም ድምፅ መስማት አስፈላጊ የነበር መሆኑን ጠቅሰዋል ። አብዛኛዎቹ መሪዎችም እሥራኤል ድረስ በመሄድ ይህንን ያደረጉ መሆኑን በመግለጽ በጉባዔው መሪዎቹ የጋዝ ከበባ መቆም እንዳለበት ያሳሰቡ መሆኑን አስታውቀዋል ። «መሪዎቹ የጋዛ ከበባ መቆም እንዳለበትና የፍልስጤም ሕዝብና ታጋቾቹ ባጠቅላይም በጋዛ ያሉ ሁሉ የሰብአዊ ርዳታ ሊደርስቸው እንደሚገብ አጽኖት ሰተው አሳስበዋል» ብለዋል።
በኒውዮርክ የፀጥታው ምክርቤት የሰብአዊ ተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ የቀረበው ጥያቄ ከአንዴም ሁለት ጊዜ ውድቅ መደረጉ የሚታወስ ሲሆን፤ የአውሮጳ ኅብረትመሪዎች ልዩነቶቻቸውን በማጥበብ የሰብአዊ ርዳታ ለማስገባት የሚያስችል ፋታ እንዲኖር መስማማታቸው በአውሮጳ ምክር ቤት ፕሬዚደንት ሚሸል በኩል ስኬት ተደርጎ ተጠቅሷል።
መሪዎቹ ከዚሁ ጋር ጦርነቱ ወደ አካባቢው እንዳይስፋፋ ይልቁንም ግለቱ እንዲበርድ አስፈላጊውን ጥረት ሁሉ ማደረግ እንደሚገባና ለዚህም በተለይ ከአካባቢው አገሮች ጋር መሥራት እንደሚያስፈልግ ባወጡት መገለጫ ትኩረት ስጥተውበታል።
የእሥራኤልና ፍልስጥኤም ጦርነትና ብጥብጥበኅብረቱ አገሮች የፀጥታ ስጋት እንዳይፈጥርም ግጭት ሊያነሳሱ የሚቺሉ የጥላቻ ንግግሮችንና ቅስቀሳዎችን መቆጣጠርና መከላከል እንደሚገባም በመግለጫቸው ተጠቅሷል። ከዚህ በተጨማሪም የእሥራኤል ፍልስጥኤምን ችግር ከመሰረቱ መፍታት የሚያስፈልግ መሆኑ በማመን በዚህ ላይ የሚመክር አለማቀፍ የሰላም ኮንፈርንስ እንዲጠራም ጥሪ አቅረበዋል።
ገበያው ንጉሴ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ነጋሽ መሐመድ