1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአውሮጳ ኅብረት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጉባኤ

ረቡዕ፣ ግንቦት 16 2015

ብራስልስ ውስጥ የ27ቱ ያአውሮጳ ኅብረት አባል አገሮች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ሰኞ ግንቦት 14 ቀን፤ 2015 ዓ.ም ባደረጉት ስብሰባ በአፍሪቃ ቀንድ የኢትዮጵያ፤ ሱዳን እና ሶማሊያ ጉዳይ ትኩረት ሰጥተዋል ። ዩክሬን እና ሩስያ ጉዳይ ላይም ተወያይተዋል ።

https://p.dw.com/p/4RlY1
Belgien Treffen der EU-Außenminister in Brüssel
ምስል Virginia Mayo/AP Photo/picture alliance

የአፍሪቃ ቀንድ ሁኔታም ትኩረት ተሰጥቶታል

ባለፈው ሰኞ በብራስልስ ቤልጄይም የተካሄደው የ27ቱ ያአውሮጳ ኅብረት አባል አገሮች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ፤ የዩክሬንን ጦርነትና የአፍርቃ ቀንድን  ሁኔታ ትኩረት ሰቶ ተወያይቷል። በአፍሪቃ ቀንድ የኢትዮጵያ፤ ሱዳን እና ሶማሊያ ጉዳይ ትኩረት ሰጥተዋል ።  ሚኒስትሮቹ በሩሲያና ዩክሬን ጦርነት ላይ ባካሄዱት ውይይት፤ ለዩክሬን የሚሰጠው የጦር መሣሪያ ርዳታ ተጠናክሮ በሚቀጥልበት ሁኒታና ባንጻሩም ሩሲያን የበለጠ ሊያገሉና ሊነጥሉ በሚችሉ ርምጃዎች ላይ ትኩረት እንዳደረጉ ተገልጿል ። 

የኅብረቱ የውጭ ጉዳይ ኃላፊና የስብሰባው መሪ ጆሴፍ ቦሬል፤ ዩክሬን እራሷን ለመከላከል እያደረገችው ባለው ጦርነት የምታገኘው የመሳሪያ ርዳታ ወሳኝነት ያለው መሆኑን በማንሳት፤ በስብሰባው በዚህ ጉዳይ በጥልቀት ውይይት እንደተደረገበት አስታውሰዋል። ሚስተር ቦርየል በጋዜጣዊ መገለጫቸው እንደገለጹትም የዩክሬን ወታደራዊ ስኬት የሚወሰነው በሚደርሳቸው የጦር መሣሪያ ርዳታና ድጋፍ  ነው። «የዩክሬን ጦርነት ድል የሚወሰነው በዩክሬኖች ጀግንነትና ተጋድሎ ብቻ ሳይሆን ይልቁንም በመጠንና  በአይነት በሚያገኙት ወታደራዊና የመሳሪያ ርዳታ ልክ ነው» በማለት ወታደራዊ እርዳታው እንዲጨምርና እንዲፈጥንም የተመከረበት መሆኑን ገልጸዋል። ከዚሁ ጋር የህብረቱ ወታደራዊ ድጋፍ ሰጭ ክፍል 15ሺ የዩክሬን ወታደሮችን ማሰልጠን መቻሉንና በቀጣይም ከዚህ ቁጥር እጥፍ ለማስልጠን የታቀደ ስለመሆኑ ለሚኒስትሮቹ ተገልጿል ተብሏል።

የአውሮጳ ኅብረት የውጭ ጉዳይ ኃላፊና የስብሰባው መሪ ጆሴፍ ቦሬል ከውጭ ጉዳይ ሚንሥትሮች ጋር
የአውሮጳ ኅብረት የውጭ ጉዳይ ኃላፊና የስብሰባው መሪ ጆሴፍ ቦሬል ከውጭ ጉዳይ ሚንሥትሮች ጋር ምስል Virginia Mayo/AP Photo/picture alliance

በሩሲያ አንጻር 11ኛው ዙር ማዕቀብ እየተሠራ መሆኑንም ሚስተር ቦርየል ጠቅሰው፤ ማዕቀቦቹ በሶስተኛ ወገን እንዳይጣሱም ተገቢው እርምጃ እንዲወሰድ ሚኒስትሮቹ መክረዋል ማሳሰቢያም ሰተዋል ብለዋል። በተጨማሪም ሚኒስትሮቹ  በዚህ  ስብሰባቸው፤ ባአፍሪቃ ቀንድ ላይም ሰፋ ያለ ውይይት ማድረጋቸው ታውቋል። በአፍሪቃ ቀንድ የፖለቲካና የጸጥታ ሁኔታ ዘገባ ቀርቦ ውይይት መደረጉን ያነሱት ሚስተር ቦርየል፤ በሱዳን የተደረሰውን የተኩስ አቁም ስምምነት በበጎ እንደተቀበሉትና ለተግባራዊነቱና ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ለሚደረገው ጥረት፤ ኅብረቱ ድጋፉን እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።ከአካባቢው አገሮች ኪንያ ለአካባቢው ሰላምና መረጋጋት ለመታደርገው ጥረትና አስተዋጾ ኅብረቱ እውቅና እንደሚሰጥና ዋና የኅብረቱ አጋርም እንደሆነች ሚስተር ቦሩየል አመላክተዋል ።

ኢትዮጵያን በሚመለከትበቀረበው ሪፖርት ሚኒስትሮቹ የተወያዩ መሆኑን ያውሱት ሚስተር ቦርየል፤ በአሁኑ ወቅት የኅብረቱና የኢትዮጵያን ግንኙነት ስላለበት  ደረጃ « በመጨረሻም ከሁለት አመት ጦርነት በኋላ ግንኑታችን እየተሻሽለ ነው» በማለት የሰላም ሰምምነቱ ለብሄራዊ እርቅና መግባባት ሂደት መሳክት አንድ ርምጃ መሆኑንም አንስተዋል። በተለይ ከእርስ በርስ ጦርነት ማብቃት በሁዋላ የብሔራዊ እርቅ ሀሳብ ቁልፍ መሆኑን በማውሳትም፤ ኅብረቱ ለኢኮኖሚው ማንሰራራት፤ ለዳግም ግንባታውና ለእርቀ ሰላም ሂደቱ መሳክት የበኩሉን ድጋፍ እንደሚያደርግ አስገንዝበዋል። 

የአውሮጳ ውጭ ጉዳይ ኃላፊው ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ ለኢትዮጵያ ይሰጥ የነበረውን የበጀት ድጋፍ ማቆየቱን አስታውሰው፤ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የሚሰጠውን ድጋፍ ግን አቁርጦ አያውቅም ብለዋል። በአሁኑ ወቅትም አሉ የውጭ ግንኑነት ኃላፊው «180 ሚሊዮን የሚያወጣና በተለይ በጦርነቱ ለተጎዱ አካባቢዎች የጤና እና የትምህርት ፕሮግራሞች የሚውል የርዳታ መርሀ ግብር» ያዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል። ጆሴፍ ቦሬል ታግዶ የቆየው የበጀት ድጋፍ ከዚህ አዲስ የእርዳታ ማዕቀፍ ጋር የሚለቀቅ ስለመሆኑም ሆነ ወይም መቼ እንደሚለቀቅ ግን ያሉት ነገር የለም።

ገበያው ንጉሤ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ