የአፍሪቃ ቀንድ አካባቢ ውጥረት በርግጥ ይረግብ ይኾን?
ሰኞ፣ ታኅሣሥ 7 2017የአንካራው ስምምነት አንድምታ
ለአንድ ዓመት ገደማ ነግሶ የነበረው የአፍሪቃ ቀንድ ውጥረት በትንሹም ቢሆን አንካራ ላይ ተንፈስ ብሏል። ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ወደ ግጭት ጦርነት ከሚያመራው መንገድ አንድ ርምጃ መለስ ብለው ጉዳያቸውን በንግግር ሊፈቱ እሺታቸውን ሰጥተዋል። በየራሳቸው የውስጥ ጉዳይ በእጅጉ ተይዘው ያሉት ሁለቱ ሃገራት በሰላማዊ መንገድ አንዱ የሌላኛውን ጥቅም ለማስጠበቅ የደረሱት ስምምነት ምን ያህል ገቢራዊ እንደሚሆን ከወዲሁ መገመት አስቸጋሪ ነው። እንዲያም ሆኖ ግን አሜሪካን ጨምሮ ምዕራባዉያኑ እና የአፍሪቃ ሕብረት ጉዳያችሁን በአስቸኳይ ቋጩ የሚለውን መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። ጤና ይስጥልን አድማጮቻችን ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በቱርክ አደራዳሪነት የደረሱት አጠቃላይ ስምምነት የአፍሪቃ ቀንድ አካባቢ ውጥረትን በርግጥ ያረግበዋል ወይስ አዳፍኖ ሌላ ተጨማሪ ጊዜ ይወስዳል ?
የሶማሊያ እና ኢትዮጵያ የአንካራ ስምምነት፥ የሶማሊላንድ በዓለ ሲመት
ኢትዮጵያ ወደብ እና የባሕር በር ያስገኝልኛል ያለችውን ስምምነት ከራስ ገዟ ሶማሌ ላንድ ጋር ከደረሰች እነሆ አንድ ዓመት ሊደፍን በተቃረበበት ወቅት ነበር የአንካራው ሽምግልና ውጤት የማስገኘቱ ድንገተኛው ዜና የተሰማው።
ለሁለቱ የአፍሪቃ ቀንድ ሃገራት ጠንካራ ወታደራዊ እና ኤኮኖሚያዊ ተጓዳኝ የሆነችው ቱርክ የሁለቱን ሃገራት መሪዎች ፊት ለፊት ለማገናኘት ወራት ቢቆጠሩም ብዙም የከበዳት አልመሰለም።
የሶማሊያዉ ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ መሐመድ ኢትዮጵያ የሉዓላዊ ግዛቴ አካል ናት ከሚሏት ሶማሌ ላንድ ጋር የደረሰችውን ስምምነት እስካላጠፈች ድረስ የመሪ ለመሪም ሆነ ማንኛውንም የፊትለፊት ንግግር ለማድረግ ዝግጁ እንዳልሆኑ በውጭ ጉዳይ ሚንስትራቸው በኩል ደጋግመው ግልጽ አድርገው ነበር።
ኢትዮጵያ በበኩሏ ከሶማሌ ላንድ ጋር የደረሰችውን ስምምነት ገቢራዊ ለማድረግ ምንም እንኳ በተቀመጠለት የጊዜ ሰሌዳ መሠረት መፈጸም ባትችልም ለስምምነቱ አጋዥ የሆኑ ሌሎች አስተዳደራዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ሥራዎችን ከማከናወን አልተቆጠበችም።
ባለፈው ረቡዕ ቱርክ አንካራ ባስተናገደችው የኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ሽምግልና የተደረሰው አጠቃላይ ስምምነት፤ ሃገራቱ ሌሎች ባለድርሻዎችን አስከትለው ከገቡበት ዲፕሎማሲያዊ ቀውስ አንጻር በርግጥ በብዙዎች ዘንድ ያልተጠበቀ እና ድንገተኛም ነበር።
ስምምነቱ የጦርነት ስጋት ለጊዜውም ቢሆን አስቀርቷል
የተገኘው ውጤት ግን በርግጥ ለጊዜዉም ቢሆን በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የጦርነት ነጋሪት ከመጎሰም ገታ የሚያደርግ እንደሆነ ነው ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ተንታኞች የሚናገሩት።
በኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ተቋም የአውሮጳ እና አሜሪካ ጉዳዮች ጥናት ዳይሬክተር ዶ/ር ዳርእስከዳር ታዬ እንደሚሉት የአንካራው ስምምነት አደራዳሪዋ ቱርክን ጨምሮ ሁለቱንም ሃገራት አሸናፊ ያደረገ ነው።
«ለሁለቱ ሃገራት ብቻ ሳይሆን ለሦስቱም ለአደራዳሪዋም፤ ለኢትዮጵያም ለሶማሊያም በጎ ነገር ይዞ የመጣ ስምምነት ነው ብዬ እወስዳለሁ። ከቱርክ አንጻር የሰላም ሚናን የምትጫወት በሚል አንድ ነጥብ ያስመዘገበች ሀገር ሆናለች። በአፍሪቃ ቀንድም ምናልባት ወደ ፊት ለሚኖራት መስተጋብርም ጥሩ ዕድል ይዞ የመጣ ነው ብለን ማየት እንችላለን።»
የአፍሪቃ ቀንድ አካባቢ ጉዳዮችን በመተንተን የሚታወቁት ኤርትራዊው አቶ አብዱራህማን ሰዒድ ግን ሌላ ምልከታ ነው ያላቸው። ምንም እንኳ ሶማሊያ ካሁን ቀደም በቅድመ ሁኔታ አስቀምጣው የነበረው የኢትዮ ሶማሌ ላንድ ስምምነት ካልተቀደደ አልነጋገርም አቋሟን ትታ ለድርድር ብትቀመጥም በድርድሩ ፍላጎቷን አሳክታ ወጥታለች፤ ኢትዮጵያም ከሶማሌ ላንድ ጋር የደረሰችውን የወደብ ስምምነት በተዘዋዋሪ መንገድ አጥታለች፤ ባይ ናቸው ።
የአንካራው ስምምነት የኢትዮ-ሶማሊላንድ ስምምነትን ይሽራልን?
«ስምምነቱ በኢትዮጵያ በኩል የሶማሊያን ሉዓላዊ ግዛት ማክበር እንዳለባት ተቀብለዋል ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ፤ እና ይኼ ዋናው መግቢያ ነበር። ምክንያቱም ለሶማሊያ ፕሬዚዳንት ይኼ እንደ ቅድመ ኹኔታ ነበር ሲያስቀምጡት የቆዩት። ምክንያቱም ከሶማሌ ላንድ የተደረገው ስምምነት የሶማሊያን ሉዓላዊ ግዛት የማያከብር ነው ብለው ነው ሲናገሩ የቆዩት ባለፈው ዓመት ማለት ነው፤ እና ይኼ በኢትዮጵያ በኩል ተቀብለዋል። ሁለተኛው መግለጫው ላይም ያለፈውን አንመለስበትም እንተወው ብለው ማለፋቸውም ይኼም በሌላ ዲፕሎማሲያዊ ቋንቋ ታሪክ ሆኗል ማለት ነው።»
እርግጥ ነው የአንካራው ድርድር አንድምታ የአፈጻጸም ቴክኒካዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ገና ተጨማሪ ጊዜ ቢጠይቅም አንድ መሠረታዊ ነገር ግን ግልጽ ሳይሆን አልቀረም። ኢትዮጵያ ለሶማሊያ ሉዓላዊ የግዛት አንድነት ዕውቅና መስጠት እና የባሕር በር ፍላጎቷን በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ ብቻ ማስፈጸም እንዳለባት መመላከቱ። ታዲያ እንዲህ ከሆነ አቶ አብዱራህማን ሰኢድ እንዳሉት በርግጥ የኢትዮጵያ እና የሶማሌ ላንድ ስምምነት ቀሪ ይሆናል ማለት ነውን? እንጠይቅ።
የኢትዮጵያ እና ሶማሌ ላንድ ስምምነት ዕጣ ፈንታ
የአውሮጳ እና አሜሪካ ጉዳዮች ጥናት ዳይሬክተር ዶ/ር ዳርእስከዳር ታዬ እንደሚሉት በሁለቱ ሃገራት መካከል የተደረሰው ስምምነት አስቀድሞ በኢትዮጵያ እና ሶማሌ ላንድ መካከል የተፈጸመው አጠቃላይ የስምምነት አንድምታ ላይ የጎላ ተጽዕኖ አያሳድረም። እንደ ተንታኙ አገላለጽ ኢትዮጵያ ከሶማሌ ላንድ ጋር እያከናወነች ያለችው ዘርፈ ብዙ የትብብር ሥራ ስምምነቱን ለማሳለጥ መሠረት የሚጥሉ ናቸው ።
«በተግባር ምን እየተደረገ ነው ስንል ኢትዮጵያ ስምምነቱ እንኳ እየተደረገ ልዑኳን ልካ ሶማሌ ላንድ ላይ ፕሬዚዳንቱ ሥልጣን ሲረከቡ ተገኝታለች። ይሄ ሶማሌ ላንድን እንደ ሀገር የመቀበል ሂደቱ አንድ አካል ነው። ከስምምነቱ አንድ ቀን ቀድሞ ደግሞ የትራንዚት ቢሮ ሁሉ የተከፈተበት ሁኔታ አለ። ስለዚህ የሚያሳየን ከሶማሌ ላንድ ጋር ያለን ግንኙነትም ሆነ የመግባባቢያ ስምምነቱ እንዳለ ነው።»
አቶ አብዱራህማን ሰዒድ ግን በዚህ ሃሳብ አይስማሙም ። ኢትዮጵያ የአንካራዉን የአጠቃላይ ስምምነት አስኳል የሆነውን ለሉዓላዊ እና የግዛት አንድነት መከበር ለሚያመለክተው ነጥብ ተገዢ ከሆነች ከበርበራ ጋር የደረሰችውን ስምምነት ቀሪ የማድረግ ግዴታ ይኖርባታል ማለት ነው።
የቱርኩ የኢትዮጵያና የሶማሊያ ስምምነት ምንነት
«በተደረገው ስምምነት መሠረት እንግዲህ በግልጽ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ የሶማሊያ ፌዴራላዊ ሉዓላዊ ግዛት እንደሚያከብሩ አስታውቀዋል። የሶማሊያ ፌዴራላዊ ግዛት ማለት ደግሞ ሶማሌ ላንድን ያካተተ ነው ። ስለዚህ በዚህ መሠረት ራሱ ውድቅ ነው ሊሉ ባይደፍሩም ነገሮች ግን ውድቅ ሆነዋል። እና አዲስ ነገር አሁን ስምምነቶች ላይ ለመድረስ ሊሞክሩ ነው ሁለቱም በቱርክ አጋዥነት ማለት ነው። ይሄ እንግዲህ ስለ ወደብ በርባራ ሊሆን ይችላል፤ ስለ ኪስማዮ ሊሆን ይችላል፤ ስለ የሆነ የሶማሊያ ወደብ ሊሆን ይችላል።»
አሁን ዋናው ጥያቄ ስምምነቱ ኢትዮጵያ፣ ሶማሊያ እና ራስ ገዟ ሶማሌ ላንድን በጋራ ተጠቃሚ ማድረግ የሚችልበት ዕድል አለ ወይ? የሚለው ይሆናል። ይህ ካልሆነ ግን በጊዜ ሂደትም ቢሆን፤ አንደኛው ወገን ከመጫወቻው ሜዳ ገለል ማለቱ አይቀርም።
ባለፈው ዓመት ታኅሣሥ ወር በኢትዮጵያ እና ራስ ገዝ ሶማሌ ላንድ መካከል የተፈረመው እና በኢትዮጵያ መንግሥት ይፋ የተደረገው የመግባቢያው ስምምነት ሰነድ ዋናው እና አንኳሩ ጉዳይ «ለኢትዮጵያ በኤደን ባሕረ-ሰላጤ ላይ ዘላቂና አስተማማኝ የባሕር ኃይል ሰፈር እና የንግድ የባሕር በር አገልግሎት በሊዝ የምታገኝበትን ዕድል ለማስገኘት ያለመ ሲሆን መንግሥት አስቀድሞ በገለፀው አቋሙ መሠረት ሶማሌ ላንድ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ከሊዙ የሚታሰብ ድርሻ እንዲኖራት ያስችላል።» ይላል። በተጨማሪም « በሂደት ሶማሌ ላንድ ዕውቅና ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት በተመለከተ የኢትዮጵያ መንግሥት በጥልቀት አጢኖ አቋም የሚወስድበትን አግባብ» እንደሚያካትት ያትታል።
የአንካራው ስምምነት አንኳር ነጥቦች
በአንካራው የመሪዎች አጠቃላይ ስምምነት ከተዘረዘሩት ስድስት አንኳር ነጥቦች መካከል ኢትዮጵያ የሶማሊያን የሉዓላዊ የግዛት አንድነት ለማክበር መስማማቷ ከሶማሌ ላንድ ከምትፈልገው ብሔራዊ ጥቅሟ ጋር እንዴት እንደምታጣጥመው የታወቀ ነገር የለም። ምክንያቱም ሶማሌ ላንድ ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ ሀገር ሳትሆን ነገር ግን እንደ ሀገር የኖረች እንደመሆኗ መጠን የሶማሊያ መንግሥት ለሚያደርገው የሁለትዮሽ ስምምነት ተገዢ የመሆን ዕድሏ የመነመነ በመሆኑ ነው።
የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ወቅታዊ ሁኔታ
ለዚህም ማሳያ የሚሆነው በቅርቡ በተደረገው የሶማሌ ላንድ ምርጫ የቀድሞውን ፕሬዚዳንት ሙሴ ቤሂን በሰፊ ልዩነት አሸንፈው ባለፈው ሳምንት ፕሬዝዳንታዊ ቃለመሃላ የፈጸሙት አብዲራሕማን ሞሐመድ አብዱላሒ በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ መካከል የተደረሰው ስምምነት የሁለት ሃገራት ጉዳይ እንጂ ሶማሌ ላንድን እንደማይመለከት ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያ ከሶማሌ ላንድ ጋር የደረሰችውን ስምምነት ቀሪ አድርጋ ከሶማሊያ ጋር በምታደርጋቸው ቀጣይ ድርድሮች ከተቀሩት የሶማሊያ ግዛቶች የወደብ አገልግሎት የምትሻ ከሆነ አስቀድሞ ትጠቀምባቸው ከነበሩ የጂቡቲ እና የበርበራ ወደቦች ጋር ሲወዳደር ኤኮኖሚያዊ አዋጭነቱ ጥያቄ ማስነሳቱም አይቀርም።
በዚህ ሁሉ ውስጥ ግን ልብ ሊባል የሚገባው የውዝግቡ ሁሉ መነሻ የሆነችው ራስ ገዟ ሶማሌ ላንድ በአዲሱ ፕሬዚዳንቷ የሥልጣን ዘመን መባቻ የተሸናፊውን ፕሬዝዳንት ስምምነቶች ስለማስቀጠላቸው አልያም ስለመሻራቸው በግልጽ የታወቀ ነገር አለመኖሩ ነው። በዲፕሎማትነታቸው የሚታወቁት የ69 ዓመቱ የቀድሞ አፈ ጉባኤ አብዲራሕማን ሞሐመድ አብዱላሒ ወይም ኢሮ ስምምነቱን ዳግም ሊያጤኑ እንደሚችሉ ፍንጭ ሰጥተዋል። ለአፍሪቃ ቀንድ ውጥረት መባባስ መነሻ የሆነውን የባሕር በር ስምምነት ፓርቲያቸው ገምግሞ አዋጩን መንገድ እንደሚከተልም ግልጽ አድርገዋል።
ኢትዮጵያ «ያለመረጋጋት ምንጮችን ማድረቅ በሚቻልበት ሂደት ቁልፍ ሚና ትጫወታለች » ፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
የቀጣናው ተዋናዮች ሚና
በቀጣናዊ ዓለም አቀፋዊ፣ ኤኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ተደማጭነቷን ከፍ እያደረገች የመጣችው ቱርክ ሁለቱን ለግጭት የሚፈላለጉ የአፍሪቃ ቀንድ ተጎራባቾችን ያለአንዳች ቅድመ ሁኔታ አገናኝታ እና አስማምታ መመለሷ ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ምስጋና አስገኝቶላታል።
ቱርክ በኢትዮ ሶማሊያ ሽምግልና ያገኘችውን የዲፕሎማሲ ተጽዕኖ ፈጣሪነት ተጠቅማ በሱዳን የእርስ በእርስ ጦርነት እና በተከተለው ቀውስ የሚካሰሱትን የሱዳን መንግሥት ብሔራዊ ጦር እና የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶችን ፊት ለፊት የማገናኘት ውጥን እንድትይዝ አድርጓታል። በዚህም ለሁለቱም ወገኖች የላሸማግላችሁ ጥሪ በይፋ እንድታቀርብ ዕድል ፈጥሮላታል።
የሆነ ሆኖ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በሁሉም ተጠቃሚነት መርህ ላይ የደረሱት ስምምነት ከመርህ ባለፈ ምን ያህል ሊያሠራ እንደሚችል ከሚነሳው ሃሳብ ባሻገር በተጨባጭ ተግባራዊ ሊያደርጉ እና ሃገራቱን ተጠቃሚ ሊያደርጉ የሚችሉ ዕድሎችን መፍጠሩ ግን አልቀረም ።
የቀጣናዊ ጉዳዮች አጥኚው ዶ/ር ዳር እስከዳር ታዬ እንደሚሉት በስምምነቱ ኢትዮጵያ ካሳካቻቸው ጉዳዮች አንዱ ወታደራዊ ኃይሏ ከሶማሊያ እንዳይወጣ እና ለሶማሊያ ደህንነት የተከፈለው መሰዋዕትነት ዕውቅና ማግኘቱ ነው።
«ሌሎች ተጨማሪ ጥቅሞች ለኢትዮጵያ የተገኘበት ሁኔታ አለ። ለምሳሌ ታኅሣሥ 31 ላይ ሶማሊያ ውስጥ ያለን ቆይታ ያበቃል፤ ኢትዮጵዮያ ተጠራርጋ ትወጣለች፤ እያሉ ሶማሊያዉያን ደጋግመው እያወሩ ነበር። ነገር ግን በዚህ ስምምነት መሠረት ከዚያ በኋላ ባለውም ሶማሊያ ውስጥ የኛን የደህንነት ፍላጎት በሚያሟላ መንገድ እዚያ እንደምንቆይ ስምምነት ላይ የተደረሰበት ሁኔታ እንዳለ ማየት ይቻላል።»
የኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ውዝግብ
የአፍሪቃ ቀንድ ቀውስ በርካታ ሃገራትን በተለያዩ ፍላጎቶች ጎትቶ ያስገባ እንደመሆኑ መጠን ሃገራቱ ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ የተጓዙት መንገድ እንዲሁ አጭር አለመሆኑ ስምምነቱ በሁለት ሃገራት መካከል በሚደረግ ስምምነት ብቻ በቀላሉ ይቋጭ እንደሁ በቀጣይ የሚታይ ቢሆንም የቀውሱ ባለድርሻ ሃገራትን ሚና መርሳት ግን ተገቢ አይሆንም።
ኢትዮጵያ ከሶማሌ ላንድ ጋር የደረሰችው ስምምነት ያስቆጣት ሶማሊያ በመጀመሪያ ያደረገችው ከኢትዮዮጵያ ጋር ሆድ እና ጀርባ የሆኑትን ግብጽ እና ኤርትራን ጎትታ ማስገባት ነበር። ፕሬዝዳንት መሐመድ ሼክ ወደ አስመራ እና ካይሮ በተደጋጋሚ በተመላለሱባቸው ያለፉት 12 ወራት ቀላል የማይባል ወታደራዊ ድጋፍ ተችሯቸዋል።
ግብጽ ለሶማሊያ በታሪኳ ከፍተኛ ነው የተባለለትን የጦር መሳሪያ ድጋፍ ከማድረግ ባሻገር፤ ወታደሮቿን በአፍሪቃ ሕብረት ሰላም አስከባሪ ኃይል ስር ለማሰለፍ ጉዞ ጀምራለች። ኤርትራ ከውጥረቱ አስቀድሞም ቢሆን የሶማሊያ ወታደሮችን በማሰልጠን ላይ የነበረች እንደመሆኗ ዝቅተኛ ግምት የማይሰጠው ወታደራዊ ድጋፍ ሰጭ ናት።
ለኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ጠንካራ ወዳጅነቷን በማሸማገል ጭምር ያሳየችው ቱርክ ሚናም እንዲሁ በቀላሉ የማይታይ ነው። በዚህም ቀጣናው የባለ ብዙ ባለድርሻ ኃይሎች ፍላጎት ሰለባ የሆነ አካባቢ መሆኑ ግልጽ ሆኗል።
የኢትዮጵያ መሻት እና ተስፋው
በዚህ ሁሉ ሂደት ለኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዋ በተመጣጠነ ዋጋ የወደብ አገልግሎት መሻትን ጨምሮ አሁን ከፍ ብሎ እየታየ የመጣዉ የባሕር ኃይል የጦር ሰፈር ፍላጎቷ እየጨመረ የመጣው ኢትዮጵያ እንደምን መሻቷን ታሳካለች የሚለው ከየካቲቱ ቴክኒካዊ ውይይት እና ድርድር የሚታይ ቢሆንም ነገር ግን እንዲሁ በቀላሉ መልስ የሚያገኝ ስለመሆኑ በርግጥ ያጠያይቃል።
ሦስት አስርት ዓመታትን በራስ ገዝነት እንደ ሀገር የዘለቀችው ሶማሌ ላንድ አሁን ዓለም አቀፋዊ የሀገርነት ዕውቅናን በእጅጉ ትሻለች። ከቅርቡ ከጎረቤት ኢትዮጵያ እንዲጀምር ይጠበቅ የነበረው የሀገርነት እውቅና ለጊዜውም ቢሆን እንቅፋት ገጥሞታል።
ኢትዮጵያ የባሕር ኃይል የምታሰፍርበትን የባሕር በር ጨምሮ ወደብ የሚያስገኝላት የተሻለውን መንገድ ታማትራለች። ዓለም አቀፋዊው ዲፕሎማሲያዊ ጫና ግን የሚያላውሳት አይመስልም። ለጊዜው በጦርነት ከሚቆርጡት ቁርጥ በሰላም የሚቆረጥሙት ቆሎ ጤና ነው እና ውሎ አድሮ በሰላማዊ መንገድ ሊሆን የሚችለውን በተስፋ ማማተር አማራጭ አይኖረውም።
ታምራት ዲንሳ
ሸዋዬ ለገሠ