1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማህበር ስጋት

ማክሰኞ፣ መጋቢት 3 2016

የህብረቱ ውሳኔ የኢትዮጵያ ቡና አመራረት ሂደቱ እስኪጣራም ቢሆን ተጽእኖው እየታዬ ነው ብሏል፡፡ በሌላ በኩል በቀይ ባህር አከባቢ እየተስተዋለ ያለው አለመረጋጋት የወደብና መርከብ እንቅስቃሴን በጉልህ ማቀዛቀዙም የቡና ማህበሩን በእጅጉ አሳስቧል፡፡

https://p.dw.com/p/4dRH5
በግሪጎሪያኑ 2025 ገቢራዊ ይሆናል በተባለዉ ሕግ መሰረት ወደ አዉሮጳ የሚገባዉ ቡና ደን ሳይጨፈጨፍ የተመረተ መሆን አለበት
ቡና፣ የአዉሮጳ ሕብረት የደን ጭፍጨፋን ለመከላከል ይረዳል ያለዉ አዲስ አደንብ የኢትዮጵያን የቡና ገበያ እየጎዳዉ ነዉ ምስል Seyoum Getu/DW

የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማህበር ስጋት

 

የአውሮፓ ህብረት በመጪዉ የግሪጎሪያን ዓመት ስራ ላይ ያውለዋልየተባለው ከደን ምንጣሮ ጋር ተያይዞ የምርቶችን የወጪ ንግድ የሚገድበው ደንብ በኢትዮጵያ ቡና ገበያ ላይ ከወዲሁ ተጽእኖ ማሳደሩ ተነገረ፡፡የኢትዮጵያ ቡና ማህበር (በቀድሞ ስሙ የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማህበር) አባላት ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ ባደረጉት ውይይት የህብረቱ ውሳኔ የኢትዮጵያ ቡና አመራረት ሂደቱ እስኪጣራም ቢሆን ተጽእኖው እየታዬ ነው ብሏል፡፡በሌላ በኩል በቀይ ባህር አከባቢ እየተስተዋለ ያለው አለመረጋጋት የወደብና መርከብ እንቅስቃሴን በጉልህ ማቀዛቀዙም የቡና ማህበሩን በእጅጉ አሳስቧል፡፡

እስራኤል ደገፋ የኢትዮጵያ ቡና ማህበር (በቀድሞ ስሙ የቡና ላኪዎች ማህበር) ቦርድ አባል ናቸው፡፡ ማህበሩ ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ አባላቱን ጠርቶ የተወያየበት ሁለት አበይት ጉዳዮች እኚህ ናቸው ይላሉ፡፡ “አንደኛው የአውሮፓ ህብረት ከደን ምንጣሮ ጋር ተያይዞ በደን ምንጣሮ የተመረቱ ምርቶችን አላስገባም ማለቱ በኢትዮጵያ ቡና ላይ ስላሳደረው ተጽእኖ እና እልባቱ ላይ መወያየት ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ከአሁናዊ የቀይ ባህር የጸጥታ ቀውስ ጋር ተያይዞ የገጠመን የወደብ ፈተና ላይ ተነጋግረን አቅጣጫ ማስቀመት ነው” ብለዋል፡፡

አቶ እስራኤል ደንቡ በዘላቂነት ለኢትዮጵያ ስጋት ይሆናል የሚል ፍራቻ የላቸውም፡፡ በብዛት በዛፎች ጥላ ስር የሚመረቱ ያሏቸው የኢትዮጵያ ቡና አመራረት ከደን ምንጣሮ ጋር እንደማይወዳጅም በማመልከት፡፡ “ያ ለኢትዮጵያ ስጋት አይደለም፡፡ ቶሎ ብለን ሂደቱን በማቀላጠፍ የኢትዮፕያ ቡና አመራረት ከደን ምንጣሮ ውጪ መሆኑን ማረጋገጥና ያለ ስጋት ተረካቢዎቻችን ቡና እንዲረከቡን ማሳመን አለብን” ነው ያሉት፡፡

የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ ደሳለኝ ጀና እንደሚሉትም ይህ ስጋት አገር ላይ ጭምር የተጋረጠ በመሆኑ ርብርብ ያሻዋል፡፡ “ችግሩ ካልተፈታ አገሪቷ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን የምትፈጽምበት የዶላር እጥረት ሊፈጥር ስለሚችል መንግስትም ሆነ ሁሉም ተዋናይ ተረባርበው ችግሩን መፍታ አለባቸው” ባይም ናቸው፡፡

አቶ ግዛቱ እንደሚሉት የኢትዮጵያ ቡና የወጪ ንግድን የሚፈትኑ ተግዳሮቶች አንድና ሁለት ጉዳዮች ብቻ አይደሉም
የኢትዮጵያ ቡና ማህበር ዋና ስራ አስከያጅ አቶ ግዛቱ ወርቁም ምስል Seyoum Getu/DW

የኢትዮጵያ ቡና ማህበር ዋና ስራ አስከያጅ አቶ ግዛቱ ወርቁም የኢትዮጵያ ቡና የወጪ ንግድን የሚፈትኑ ተግዳሮቶች አንድና ሁለት ጉዳዮች ብቻ አይደሉም ሲሉ የዘርፉን ፈተና ይዘረዝራሉ፡፡ “የቡና ላኪ ስትሆን ዓለማቀፍ ገቢያ ላይ ከባድ ውድድር ነው የሚጠብቅህ፡፡ ማጓጓዣ እና ግብይቱም በበፈተና የተሞላ ነው፡፡ አገሪቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ከመፈለግ አንጻር አንዳንዴ ለትርፍም ብቻ ሳሆን ሌላ እቃ አስገብተህበት የምታተርፍበትን ዶላር ለማግኘት ጭምር ይሸጣል” ብለዋል፡፡

አቶ ግዛቱ አስተያየታቸውን ቀጠሉ፤ በዚህ ላይ የአወሮፓ ህብረቱ የደን ምንታሮ ደንብ (EUDR) እና የቀይ ባህር የንግድ ቀጠና ስጋት ስታከል ዘርፉን ከባድ ፈተና ውስጥ የሚከት ብለውታልም፡፡ “የአውሮፓ ህብረቱ ደንብ እስካሁን ስራ ላይ ባውልም ተጽእኖው አሁንም ጀምሯል፡፡ ምክኒያቱም ዘንድሮ የሚሸጡ ምርቶች በሚቀትለው ዓመት በአውሮፓ ገቢያ መደርደሪያ ላይ ስለሚሆኑ ነገሩ እስኪጣራ የአውሮፓ ነጋዴዎች መረከብ ይሰጋሉ፡፡ ይህ ደግሞ ለኛ ፈተና ነው” ይላሉ፡፡ አክለውም የቀይ ባህር የንግድ ቃጠናው ስጋት የጂቡቲ ወደብንም የሚነካ በመሆኑ ስጋት ውስጥ ትሎናል ብለዋልም፡፡

አቶ እስራኤል የአዉሮጳ ሕብረት ደንብ በዘላቂነት ለኢትዮጵያ ስጋት ይሆናል የሚል ፍራቻ የላቸውም
እስራኤል ደገፋ የኢትዮጵያ ቡና ማህበር (በቀድሞ ስሙ የቡና ላኪዎች ማህበር) ቦርድ አባል ናቸውምስል Seyoum Getu/DW

አቶ ግዛቱ የ5 ሚሊየን ገበሬ ህይወትን በቀጥታ የሚደጉመውን ቡና ገቢያው ላይ የተጋረጠውን ፈተና በሙሉ አቅም የመፍታት አስፈላጊነትንም አንስተዋል፡፡  ዘንድሮ የተመረተ ቡና አሁን ገና ዋጋው ተቆርጦ ወደ ውጪ መላክ ባልተጀመረበት ነው ይህ ሰፋፊ ስጋቶች በገቢያው ላይ የተደቀኑትም፡፡ የቡና ላኪ ማህብር ስራ አስከያጁ አቶ ግዛቱ ወርቁ ለዚህ ደግሞ አማራጭ ወደብ እና መርከቦችን እስከመፈለግ የሚደርስ መፍትሄዎች ሊፈለጉ ይገባል ባይ ናቸው፡፡

ስዩም ጌቱ

ነጋሽ መሐመድ

ዮሐንስ ገብረ እግዚብአሔር