1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ በረራ አቆመ

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 28 2016

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አስመራ ኤርትራ በየቀኑ የሚያደርገውን በረራ ከዛሬ ጀምሮ ያቋረጠው ካለፈው ቅዳሜ ጀምሮ አስመራ ውስጥ ገንዘቡን ማንቀሳቀስ እንዳይችል "ሙሉ በሙሉ በመታገዱ" መሆኑን አስታወቀ።

https://p.dw.com/p/4kELb
አቶ መስፍን እንዳሉት አየር መንገዱ ወደ ኤርትራ በረራ ያቆመዉ አስመራ የሚገኝ ገንዘቡ በመታገዱ ነዉ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ መስፍን ጣሰዉ ምስል Solomon Muchie/DW

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ በረራ አቆመ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ በረራ ያቆመው አስመራ ውስጥ ገንዘብ መንቀሳቀስ በመታገዱ መሆኑን ገለፀ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አስመራ ኤርትራ በየቀኑ የሚያደርገውን በረራ ከዛሬ ጀምሮ ያቋረጠው ካለፈው ቅዳሜ ጀምሮ አስመራ ውስጥ ገንዘቡን ማንቀሳቀስ እንዳይችል "ሙሉ በሙሉ በመታገዱ" መሆኑን አስታወቀ።

አየር መንገዱ ከኤርትራ ተገዶ መውጣቱን የገለፁት የአየር መንገዱ ግሩፑ ዋና ሥራ አሥፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው ሁኔታዎች ከተስተካከሉ ወደፊት ተመልሰን ወደ ኤርትራ ለመብረር ዝግጁ ነን ብለዋል።

ዋና ሥራ አስፈፃሚው አየር መንገዱ በኤርትራ አየር ክልል መብረራቸው እንደሚቀጥሉ ሆኖም ግን ያንን የሚያስቆም እርምጃ ቢመጣ ሌሎች አማራጮች መኖራቸውን ተናግረዋል። 

የአየር ክልል እግድን የተመለከተ ውሳኔ ከሶማሊያ ቢመጣ በሚል የአየር መንገዱን ዝግጅት የተጠየቁት ዋና ሥራ አስፈፃሚው ሶማሊያ አንስታው የነበረው ጥያቄ በአግባቡ ስለተመለሰ "እነሱም ደስተኞች ናቸው፣ ከሶማሌላንድም ምንም ተቃውሞ የለም፣ ችግሩ ተፈትቷል" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አሥፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው ዛሬ ከቀትር በኋላ "ወቅታዊ እና ቁልፍ" ባሉት ጉዳይ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ወደ አስመራ በቀን ሁለት ጊዜ ይደረግ የነበረው በረራ የተቋረጠው ከኤርትራ ሲቪል አቪየሽ ከዚህ በፊት አየር መንገዱ ላይ የተጣለበት የበረራ እግድ ምክንያቱን በውል ባላወቁበት፣ የመነጋገር እድል ማግኘት ባልቻሉበት እና ቀጥሎም በአስመራ ያለው የአየር መንገዱ የባንክ ሒሳቡ እንዳይንቀሳቀስ "ሙሉ በሙሉ" እግድ ስለተጣለበት መሆኑን ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አስመራ ለመጓዝ ቀድመው ትኬት ለቆረጡ መንገደኞቹ "ያለምንም ተጨማሪ ክፍያ በሌሎች አየር መንገዶች የሚጓጓዙበትን ሁኔታ ያመቻቻል" አልያም እንደ አማራጭ በደንበኞች ፍላጎት ለትኬት የከፈሉትን ገንዘብ ሙሉውን ተመላሽ ያደርጋል" ተብሏል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በረራውን ለመቀጠል "አዳጋች ሁኔታዎች ተፈጥረዋል" ያሉት ዋና ሥራ አስፈፃሚው፣ አየር መንገዱ ለቀረቡበት ቅሬታዎች ምላሽ መስጠቱን ተናግረዋል።

"በኤርትራ አየር ክልል መብረራችን እንቀጥላለን። ያንን ለማቆም የሚያስገድደን ነገር የለም።" የአየር መንገዱ  ዋና ሥራ አሥፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው
"በኤርትራ አየር ክልል መብረራችን እንቀጥላለን። ያንን ለማቆም የሚያስገድደን ነገር የለም።" የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አሥፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰውምስል AP

ከኤርትራም ይሁን ከሶማሊያ የበረራ አየር ክልልን የመከልከል ወይም የማገድ ውሳኔ ቢመጣ የአየር መንገዱ ዝግጅት ምን እንደሆን ተጠይቀው ምላሽ ሰጥተዋል።

"በኤርትራ አየር ክልል መብረራችን እንቀጥላለን። ያንን ለማቆም የሚያስገድደን ነገር የለም። ሶማሊያ አንስታው የነበረው ጥያቄ በአግባቡ ስለተመለሰ "እነሱም ደስተኞች ናቸው፣ ከሶማሌላንድም ምንም ተቃውሞ የለም፣ ችግሩ ተፈትቷል" ብለዌል።

የኤርትራ ሲቪል አቪዬሽን ከአዲስ አበባ ወደ አስመራ የሚደረጉ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎች ከመስከረም 20 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ እንዲቋረጡ ወይም በረራ እንዳይደረግ አስቀድሞ እግድ መጣሉ ይታወሳል። አየር መንገዱ የዚህን ውሳኔ ምክንያት ለማወቅ ያደረገው ያልተቋረጠ ጥረት ግን ምላሽ አለማግኘቱን ዛሬ አስታውቋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራውን ለማስቀጠል ጥረት ቢያደርግም "በጎ ምላሽ ባለማግኘቱ" ሥራውን ማቋረጡን ነው የገለፀው።

ለብዙ ዓመታት ተቃርጦ የነበረው የኢትዮጵያ አየር መንገድየኤርትራ በረራ ሁለቱ ሀገራት ሰላም ማውረዳቸውን ተከትሎ ከግሪጎሪያን ሐምሌ 2018 ጀምሮ ላለፉት 6 ዓመት አገልግሎት ሲሰጥ የቆየ ቢሆንም ከዛሬ ጀምሮ ዳግም ተቋርጧል። 

የኤርትራ ሲቪል አቭዬሽን ባለስልጣን እርምጃ የአለም አቀፍ የበረራ ተቋማትን ሕግ ያከበረ እንዳልሆነም በዛሬው መግለጫ ተጠቅሷል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሁኔታዎች ከተስተካከሉ ወደፊት ተመልሶ ወደ ኤርትራ ለመብረር ዝግጁ መሆኑን አቶ መስፍን ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

አዲስ አበባ የሚገኘዉ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቡድን ዋና ፅሕፈት ቤት
አዲስ አበባ የሚገኘዉ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቡድን ዋና ፅሕፈት ቤት ምስል Solomon Muchie/DW

የኤርትራ ሲቪል አቭዬሽን ይህንን ውሳኔ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በተጓዦች ላይ ምክንያታዊ ያልሆነ የበረራ ቲኬት ዋጋ ጨምሯል፣ ስልታዊ እና የተደራጀ ያለው የሻንጣ ስርቆት ተፈጽሟል፣ ተገቢነት የሌላቸው ያላቸውን የንግድ ተግባራትን ተከትሏል፣ ተደጋጋሚ የበረራ እና የሻንጣዎች መዘግየት ታይቶበታል፣ ለእነዚህም ካሳ እየከፈለ አይደለም ሲል በመጥቀስ ከዚህ ቀድሞ አስታውቋል።
ሰሎሞን ሙጬ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
እሸቴ በቀለ