የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ለታጣቂዎች ያቀረበዉ ጥሪና ተግዳሮቱ
ሐሙስ፣ ሚያዝያ 17 2016
የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በትጥቅ ትግል ውስጥ ያሉ አካላት ወደ ምክክር መድረኩ እንዲገቡ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ቅዳሜ በሻሸመነ ከተማ ባካሄደው የኦሮሚያ ክልል ማህበረሰብ ተወካዮች የማጠቃለያ ልየታ መድረክ ላይ ጥሪ አቅርቦ ነበር።ኮሚሽኑ በምክክሩ መድረክ እንዲሳተፉ ጥሪ ለቀረበላቸው ለነዚህ ታጣቂዎች ተገቢውን የጥበቃ ዋስትና እንደሚያመቻችም አስታውቋል።
ይሁንና ይህ የኮሚሽኑ አስተያየት በአገሪቱ የሚስተዋለውን የፖለቲካ ውስብስብነት በአስቸጋሪነት ልኩ አለመረዳት ነው በሚል ትችትን አስተናግዷል፡፡ጥሪውን ተከትሎ ትችት ያሰሙ ወገኖች በትትቅ የሚንቀሳቀሱትን ወገኖች ወደ ሰላማዊ የፖለቲካ ሂደት በመመለስ ረገድ መንግስት ጉልህውን ድርሻ መወታት ይኖርበታልም ባይ ናቸው፡፡
በባለፈው የቅዳሜው የኮሚሽኑ ህዝባዊ የውይይት መድረኩ ላይ የተገኙት የኮሚሽኑ ከፍተኛ አመራሮች የኮሚሽኑን የሥራ ሂደት አስመልከተው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በትጥቅ የሚንቀሳቀሱ አካላት ወደ ምክክር መድረኩ ብመጡ ኮሚሽኑ ተገቢውን የጥበቃ ዋስትና እንደሚያመቻችላቸው አስታውቀው ነበር፡፡ በዚህ ጥሪውም በትጥቅ ትግል ያሉ ወገኖች ሳይመሽ ወደ ድርድሩ እንዲገቡ ሲል ጠይቋል፡፡ይህን የኮሚሽኑን ጥያቄና ጥሪ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የፖለቲካ ውስብስብነት አለመረዳት አሊያም የችግሮቹን ውስብስብነት ማቅለል ነው ብለው ሃሳባቸውን ያንጸባረቁ በርካቶች ናቸው፡፡
በኮሚሽኑ የቀረበው ጥሪ እና የችግሩ ጥልቀት
አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ፍልስፍና ረዳት ፕሮፈሰር ሲሳይ አሰምሬ የኮሚሽኑን ገለጻ ለመረዳት መቸገራቸውን ይናገራሉ፡፡ “ኮሚሽኑ የታጠቁ አካላት መንግስት ያስረናል ይጮቅነናል በሚል ነው ትጥቅ አንግበው በራሳቸው መንገድ የሚታገሉት፡፡ እነዚህን አካላት ከለላ እንድታገኙ ዋስትና እሰጣችኋለሁ ሲል ኮሚሽኑ ምን ማለቱ እንደሆነ ለመረዳት አስቸጋሪ ነው፡፡ ኮሚሽኑ እነዚህን ለመጠበቅ ወይም የጥበቃ ዋስትና ለመስጠት የኢኮኖሚና ወታደራዊ አቅሙስ አለው ወይ” በማለት ነው አስተያየታቸውን ያጋሩት፡፡
ሌላው አስተያየት ሰጪ የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ (ኦፌኮ) ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጥሩነህ ገምታ ሲሆን እሳቸውም በአስተያየታቸው ይህ ኃላፊነት የኮሚሽኑ መሆኑን ይጠራጠራሉ፡፡ “ከኃላፊነትህ ውጪ ሊሆኑ የሚችሉ ነገሮችን ኃላፊነትህ አድርገህ ስትወስድ ነገሮች አስቸጋሪ ሊሆኑብህ ስለሚችሉ ያንን ካላደረክህ እምነት ታጣለህ” በማለት ያንን ማድረግ ለኮሚሽኑ ቀላል ላይሆን እንደሚችል ገልጸዋል፡፡
ታጣቂዎችን በምክክር የማሳተፍ መንገድ
አስተያየት ሰጪዎቹ የታጠቁ አካላትን በምክክሩ ለማሳተፍ አስቀድሞ መሰራት ያለበት የፖለቲካ ስራ ነው ይላሉ፡፡ የፖለቲካል ፍልስፍና መምህሩ ረዳት ፕሮፈሰር ሲሳይ መሰል የኮሚሽኑ ጥሪ መቅረብ ያለበት በመንግስት ሊሰሩ የሚገባቸው ስራዎች ከተጠናቀቁ በኋላ ነው፡፡ “መንግስት አስቀድሞ መስራት መከወን ያለበት ስራ የኮሚሽኑንም ስራ ሊያቀለው የሚችል ነው፡፡ ሀገሪቱ ሰላምና መረጋጋት እንዲኖራት መንግስት የፐፖለቲካ ስራውን ከሰራ ኮሚሽኑ ችግሮቹ እንዳደገሙና ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ የምክክር መደላድል መፍጠር ይችላል” ብለዋል፡፡
አማጺያንን ጨምሮ የተካረረ የተቃውሞ ሁኔታ የመኖሩ ጉዳይ መነሻው መሬት ላይ ያሉ ችግሮች ሰፊ መሆናቸውን የሚሳይ ነው የሚሉት ፖለቲከኛ ጥሩነህ ገምታ በፊናቸው፤ የአገሪቱን የፖለቲካ ሁኔታ የሚመራው መንግስት ችግሮቹን ለመፍታት ጉልህውን ሚና አለው ባይ ናቸው፡፡ “ታጣቂዎችን በማስፈታት ወደ ሰላማዊ ፖለቲካ ለመመለስ መፍትሄው ሁለት ወይም ሶስት ነገሮች ናቸው፡፡ መንግስት በተናጥል ሊወስዳቸው ከሚችላቸው የሰላም ተግባራት አንዱ የሰላም መሻቱን ነገር ከቃላት ባለፈ በተግባር መደገፍ አለበት፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ከሁሉም ተቃዋሚዎች በተለይም መሳሪያን ይዘው ከሚዋጉት ጋር በቀጥታ ድርድር ማድረግ አለበት፡፡ ሶስተኛውና የመጨረሻው አማራጭ ከታጣቂዎች ጋር ለመደራደር ገለልተኛ ሶስተኛ አካል መጠቀም ነው” ሲሉ መፍትሄ ያመጣል ባሉት ጉዳይ ላይ የሰጡትን ሃሳብ ቋጭተዋል፡፡
ሽዩም ጌቱ
ነጋሽ መሐመድ
አዜብ ታደሰ