1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ስለ አፍሪቃ ሕብረት ምን አለ?

ዓርብ፣ ሚያዝያ 18 2016

የአፍሪቃ ሕብረት «የውጭ ምንዛሪ ሒሳቡን ወደ ሌላ ሀገር ሊያዘዋውር ነው» በሚል የተሰራጨው መረጃ «የተሳሳተ» ነው ሲል የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ አስታወቀ።

https://p.dw.com/p/4fEht
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ምስል Solomon Muchie/DW

የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ስለ አፍሪቃ ሕብረት ምን አለ?

 

 

የአፍሪቃ ሕብረት «የውጭ ምንዛሪ ሒሳቡን ወደ ሌላ ሀገር ሊያዘዋውር ነው» በሚል የተሰራጨው መረጃ «የተሳሳተ» ነው ሲል የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ አስታወቀ። የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አቶ ነቢዩ ተድላ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ የአፍሪቃ ሕብረት በግቢው ውስጥ በሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሒሳቡ ላይ በሀሰተኛ ሰነድ ገንዘብ ለማዘዋወር የተደረገበትን ሙከራ ተከትሎ መሰል መረጃዎች ቢወጡም «ከሕብረቱ ጋር ባደረግነው ቀጥተኛ ውይይት ይህ አይነት እሳቤ በተቋሙ ውስጥ እንደሌለ የተቋሙ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች አረጋግጠዋል» ሲሉ ተናግረዋል። የኢትዮጵያ መንግሥት ከሕብረቱ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ባደረገው ውይይት «በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያለው የድርጅቱ ሒሳብ በአስተማማኝ ሁኔታ እየተጠበቀ እንደሆነ» የሕብረቱ ኃላፊዎች መናገራቸውንም ቃል አቀባዩ ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስትያን ከፍተኛ የሥራ ኃላፊ የሆኑት ሊቀ ዐዕላፍ ቀሲስ በላይ መኮንን ከሳምንት በፊት አዲስ አበባ ውስጥ ተቀማጭ በሆነው አሕጉራዊው ድርጅት የአፍሪቃ ሕብረት ዋና ግቢ ውስጥ በሚገኝ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፍ በመቅረብ፣ «ከሕብረቱ የክፍያ ሰነድ ጋር ተመሳስለው የተዘጋጁ» በተባሉ ሀሰተኛ ሰነዶች በመጠቀም ከሕብረቱ የባንክ ሒሳብ ወደ ሌላ ሒሳብ ከስድስት ሚሊዮን ዶላር በላይ ለማዘዋወር ሲሞክሩ መያዛቸውን ተከትሎ፤ በሀገር ውስጥ ተነባቢ የሆነው The Report የእንግሊዝኛው ጋዜጣ፤ በስም ያልተጠቀሱ የአፍሪቃ ሕብረት የገንዘብ ባለሙያዎችን ዋቢ አድርጎ ሕብረቱ የውጭ ምንዛሪ ሒሳቡን ከኢትዮጵያ ሊያዘዋውር መሆኑን እንደገለፁለት ዘግቧልል።

ይህንን ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ከሕብረቱ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር በቀጥታ መወያየታቸውን የገለፁት የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ነቢዩ ተድላ መረጃው «ትክክለኛ አይደለም» ብለዋል። የተፈጠረው ክስተት በኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ነባራዊ ሁኔታ ላይ ያስከተለው ተጽዕኖ ስለመኖር አለመኖሩ የጠየቅናቸው ቃል ዐቀባዩ «ጉዳዩ በሕግ ያለ ነው። ዝርዝር ልንናገር አንችልም። የተሞከረው ጥቃት ግን ከሽፏል። ጉዳዩ ወደ ሌላ ደረጃ ሳያልፍ ወይም ጉዳት ሳያስከትል ለመቆጣጠር ተችሏል» በማለት መልሰዋል።

ቃል አቀባይ አቶ ነቢዩ ተድላ
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ነቢዩ ተድላምስል Solomon Muchie/DW

በጉዳዩ ላይ ከቀናት በፊት ዶቼ ቬለ ማብራሪያ የጠየቃት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን «ሊቀ ዐዕላፍ በላይ መኮንንበሕግ ጥላ ሥር የዋሉበት ጉዳይ ከቤተ ክርስቲያናችን ጋር የሚያገናኘው ምንም ጉዳይ እንደሌለ፤ በግል ሕይወታቸው ውስጥ የገጠማቸው ነገር እንደሆነ ነው የተረዳነው» የሚል ምላሽ መስጠቷ ይታወሳል።

የኢትዮጵያኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስትያን ከፍተኛ የሥራ ኃላፊ የሆኑት ቀሲስ በላይ መኮንን ባለፈው ሳምንት በአፍሪቃ ሕብረት ግቢ ውስጥ በሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፍ በአካል በመገኘት «ከአፍሪቃ ሕብረት የክፍያ ሰነድ ጋር ተመሳስለው የተዘጋጁ» በተባሉ ሐሰተኛ ሰነዶች፤ ከስድስት ሚሊዮን ዶላር በላይ ከሕብረቱ የባንክ ሒሳብ ወደ ሌላ የባንክ ሒሳብ ለማዘዋወር ሲሞክሩ በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ይታወሳል። 

ሰርቢያ ውስጥ የሚገኘው የሶማሊያ ኤምባሲ ያጋራው ካርታ

በዛሬው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ ሰርቢያ ውስጥ የሚገኘው የሶማሊያ ኤምባሲ ትናንት የኢትዮጵያን የኦጋዴን አካባቢ ያካተተ እና ታላቋ ሶማሊያ የሚል ካርታ በኤክስ የመገናኛ ዐውታር ማጋራቱን በተመለከተ የኢትዮጵያ መንግሥት ጉዳዩን እንዴት እየተከታተለው እንደሆነም ጥያቄ ቀርቦላቸው፤ «የሶማሊያ መንግሥት ኦፊሴል አቋም ነው ብለን አንወስድም» ብለዋል። 

«በኦፊሴል ምላሽ የምንሰጥበት አግባብ የለም» በማለትም የወጣው መረጃ መልሶ መነሳቱን የጠቆሙት ቃል ዐቀባዩ ሁኔታው የመገናኛ ዐውታሩን ከሚቆጣጠሩ ግለሰቦች የግል ሀሳብ መነሻ ሊሆን እንደሚችል ገልፀዋል። 

ሰሎሞን ሙጬ

ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ