1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስኢትዮጵያ

የኢንተርኔት አጠቃቀም ፍትሃዊነት ችግር በኢትዮጵያ

ፀሀይ ጫኔ
ረቡዕ፣ ሰኔ 26 2016

ኢትዮጵያም ከጠቅላላው ህዝብ ከሩብ በታች ወይም ወደ 30 ሚሊዮን ለሚጠጋው ህዝብ ብቻ በይነመረብ ተደራሽ በማድረግ፤ አነስተኛ የበይነመረብ ተጠቃሚ ከሆኑ ሀገራት ውስጥ አንዷ ነች።የመብቶች እና ዲሞክራሲ እድገት ማዕከል በቅርቡ ይፋ ባደረገው አንድ ጥናት ደግሞ በኢትዮጵያ ከኢንተርኔት ተደራሽነት በተጨማሪ የፍትሃዊነት ችግር መኖሩን አመልክቷል።

https://p.dw.com/p/4hnGn
Symbolbild Soziale Medien Social Media Smartphone ZOOM
ምስል Fotolia/bloomua

የኢንተርኔት አጠቃቀም ፍትሃዊነት ችግር በኢትዮጵያ

ባለንበት የዲጅታል ዘመን በይነመረብ/ኢንተርኔት/ ለሰው ልጆች እጅግ አስፈላጊ ከሚባሉ ነገሮች አንዱ እየሆነ መጥቷል።ያም ሆኖ አዳጊ ሀገራት የበይነመረብ ተደራሽነት እጅግ አነስተኛ ነው።ኢትዮጵያም ከጠቅላላው ህዝብ ከሩብ በታች ወይም ወደ 30 ሚሊዮን ለሚጠጋው ህዝብ ብቻ በይነመረብ ተደራሽ በማድረግ፤ አነስተኛ የበይነመረብ ተጠቃሚ ከሆኑ ሀገራት ውስጥ አንዷ ነች።ይህ የተደራሽነት አሃዝ በአንዳንድ የሀገሪቱ ክፍሎች በተከሰቱ  ግጭቶች ሳቢያ በይነመረብ  ከመቋረጡ በፊት የወጣ በመሆኑ ደግሞ አሁን ሊቀንስ ይችላል። የመብቶች እና ዲሞክራሲ እድገት ማዕከል በእንግሊዝኛው ምህፃሩ / CARD/ በቅርቡ ይፋ ባደረገው አዲስ ጥናት ደግሞ ከበይነመረብ ተደራሽነት ችግር ባሻገር በተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች መካከል እጅግ ጥልቅ የሆነ የአጠቃቀም ልዩነት መኖሩን አመልክቷል። የማዕከሉ የፕሮግራም ማኔጄር አቶ መንግስቱ አሰፋ እንደሚሉት ጥናቱ እንደማሳያ በሁለት ከተሞች የተሰራ ነው። በአማራ ክልል የኢንተርኔ እገዳ እንዲነሳ ዓለም አቀፍ ጥሪ

 አቶ ሙንግስቱ አሰፋ፤ የመብቶች እና የዲሞክራሲ እድገት ማዕከል ፕሮግራም ማኔጄር
አቶ መንግስቱ አሰፋ፤ የመብቶች እና የዲሞክራሲ እድገት ማዕከል ፕሮግራም ማኔጄርምስል privat

«የኢንተርኔት ተደራሽነት ፍትሃዊነት በኢትዮጵያ» በሚል ርዕስ  አክሰስ ናው በተባለው በዲጂታል መብቶች ላይ ባተኮረ ድርጅት ድጋፍ የተሰራው ይህ ጥናት  የኔትወርክ ጥራትን፣፣ የበይነመረብ ተመጣጣኝ ዋጋ፣ ዲጂታል ክህሎት እና የዲጅታል መሳሪያዎች ተደራሽነትንም ዳሷል።
ጥናቱ በኢትዮጵያ የኢንተርኔት አገልግሎትን እና የአጠቃቀም ሁኔታን ለመረዳት በአዲስ አበባ እና በአርባምንጭ ከተማ ከሚገኙ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ውስጥ በ810 ሰዎች ላይ ጥናት አድርጓል። ቃለመጠይቆችን፣ የሰነድ ትንታኔዎችን እና የመስክ ምልከታዎችንም አካቷል። 
ጥናቱ በአጠቃላይ መጠነኛ የኢንተርኔት አጠቃቀምን አረጋግጧል፣ ሩብ የሚሆኑ የጥናቱ ተሳታፊዎች በየቀኑ ከሁለት እስከ አራት ሰአታት ውስጥ በይነመረብ ላይ ያሳልፋሉ። ይህ አሃዝ በዓለም አቀፍ ደረጃ ካላው ከሰባት ሰአት አማካይ አጠቃቀም በእጅጉ ያነሰ ነው።     

ኢትዮጵያ ውስጥ በተደጋጋሚ የሚዘጋው፣ የሚገደበው ኢንተርኔት እና ያስከተለው ኪሳራ
ከዚህ በተጨማሪ እንደ ኦንላይን ባንክ፣ ትምህርት እና ኢ-ኮሜርስ ላሉ ተግባራት የተገደበ የበይነመረብ አጠቃቀም መኖሩንም ጥናቱ አመልክቷል።ጥናቱ እንደሚያሳየው ለአብዛኞቹ በተንቀሳቃሽ ስልክ የሚቀርብ በይነመረብ /ሞባይል ኔትወርክ/ ተመራጭ ነው። ዋይ ፋይ /Wifi / እና ቋሚ ብሮድባንድ በቅደም ተከተል ሁለተኛ እና ሶስተኛ ናቸው።«በኢትዮጵያ የኢንተርኔት አገልግሎት ከሰብአዊ መብት አንጻር እንዴት ይታያል?»
ነገር ግን፣ እንደ የትምህርት ደረጃ፣ ጾታ፣ ዲጂታል ክህሎት እና መሠረተ ልማትን የመሳሰሉ  ነገሮች  በበይነመረብ አጠቃቀምላይ ተፅዕኖ ያደርጋሉ። በበይነመረብ አጠቃቀም ረገድ ከቦታ ቦታ ጉልህ ልዩነቶች መኖራቸውን ያመለከተው ጥናቱ፤ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ከአርባ ምንጭ ከተማ  ጋር ሲነጻጸሩ የላቀ የበይነመረብ አገልግሎት ተጠቃሚ ሆነዋል። በተጨማሪም፣ ወንዶች፣ ከፍተኛ ገቢ እና የትምህርት ደረጃ ያላቸው ግለሰቦች ረዘም ያለ የበይነመረብ አጠቃቀም ጊዜ እና ሰፋ ያለ  እንቅስቃሴ እንዳላቸው ጥናቱ ጠቁሟል።ከዚህ አንጻር የሴቶች የበይነመረብ አጠቃቀም ዝቅተኛ ነው።

ሩብ የሚሆኑ የጥናቱ ተሳታፊዎች በየቀኑ ከሁለት እስከ አራት ሰአታት ውስጥ በይነመረብ ላይ ያሳልፋሉ። ይህ አሃዝ በዓለም አቀፍ ደረጃ ካላው ከሰባት ሰአት አማካይ አጠቃቀም በእጅጉ ያነሰ ነው። 
ሩብ የሚሆኑ የጥናቱ ተሳታፊዎች በየቀኑ ከሁለት እስከ አራት ሰአታት ውስጥ በይነመረብ ላይ ያሳልፋሉ። ይህ አሃዝ በዓለም አቀፍ ደረጃ ካላው ከሰባት ሰአት አማካይ አጠቃቀም በእጅጉ ያነሰ ነው።  ምስል Fotolia/dell

በኢትዮጵያ ያለውን የኢንተርኔት ተደራሽነት ፍትሃዊነት የመረመረው ጥናቱ ስርዓተ-ፆታ፣ የትምህርት ደረጃ ፣ ገቢ እና የመኖሪያ አካባቢ ከቋሚ የበይነመረብ ተደራሽነት ጋር  ግልጽ ግንኙነት እንዳለው አመልክቷል። ስለሆነም በጥናቱ የተገለፁትን ችግሮች በመፍታት በኢትዮጵያ ፍትሃዊ እና ተመጣጣኝ ዋጋ ያለው ዘላቂ የበይነመረብ ተጠቃሚነት እንዲኖር ለማድረግ እና የተደራሽነት አለመመጣጠን ለማጥበብ የፖሊስ እና የአሰራር ስርዓቶችን ማሻሻል ያስፈልጋል ይላሉ።

«ለሚመለከታቸው በጥናቱ የጠቆምናቸው ሪኮሜንዴሽን አሉ። ለሚመለከታቸው ሁሉም ባለ ድርሻ አካላት፤,ነገር ግን ፍትሃዊ እና «አፎርደብል»የሆነ የኢንተርኔት አገልግሎት ዘላቂ እንዲሆን ከተፈለገ በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በተለይ ሴቶች በእድሜ እንዲሁም በገቢ ደረጃ፣ በትምህርት ደረጃ ከመሀል ሀገር ርቀት አንፃር ያለውን ተደራሽነት አለመመጣጠን ማጥበብ ከተፈለገ የፖሊሲ እና የአሰራር ስርዓቶችን ማሻሻል ይጠበቅብናል።አንደኛው ከአዲስ አበባ ራቅ ወዳሉ ቦታዎችም እንዲዳረስ ማድረግ።የመሰረተ ልማት መዘርጋት ይኖርብናል።እንዲሁም ደግሞ ኢንተርኔት ስለደረሰው ብቻ ሁሉም ሰው ኢንተር ኔት ተጠቃሚ ይሆናል ማለት አይለም።ስለዚህ ኢንተርኔት መጠቀም ራሱን የቻለ ክህሎት፣እውቀት እና ግንዛቤ ይጠይቃል። ስለዚህ ዲጅታል ክህሎትን ማስረፅ ይኖርብናል ማለት ነው።ይሄ መንግስት የሚሰራው ነገር ነው።»ካሉ በኋላ እንደእርሳቸው ድርጅት ያሉ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችም ሊሰሩ እንደሚገባ አመልክተዋል።

የመብቶች እና ዲሞክራሲ እድገት ማዕከል ዓርማ
የመብቶች እና ዲሞክራሲ እድገት ማዕከል ዓርማምስል Seyoum Getu/DW

ከዚህ በተጨማሪ በዋጋ ደረጃ ተመጣጣኝ ማድረግ ፤ዲጅታል ክህሎትን እና  መሰረተልማቶችን ማሳደግም አስፈላጊ መሆኑን አቶ መንግስቱ አብራርተዋል። «አንዳንድ ጊዜ ደግሞ መሰረተልማቱ ስላለ ብቻ ወይም ክህሎቱ ስላለ ብቻ ለሁሉም ሰው ይዳረሳል ማለት አይደለም።አንዳንድ ጊዜ ከዋጋ አንፃርም ሲታይ ኢትዮጵያ ውስጥ ሁሉም ሰው «አፎርድ» አያደርግም ኢንተርኔት ወይም ፈጣን ኢንተርኔት ማለት ነው።የህዝብ «ዋይፋይ ስፖቶች»በበቂ ሁኔታ አይገኙም። እንዲሁም በግለሰብ ደረጃ ኢንተርኔትን በበቂ ሁኔታ »መጠቀም ሲያስፈልግ ሁሉም ሰው ዋጋውን ላይችል ይችላል።ስለዚህ በዚያ ጉዳይም ላይ ኢኮኖሚ እድገቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ከዚሁ የሚገኘው ሀገራዊ ገቢ እንደተጠበቀ ሆኖ ተደራሽነቱን በማስፋትም የሚገኘውን ገቢ በዚህ ደረጃ ማሳደግ ይቻላል።የሚል ከዚህ በፊትም የሰራነው ጥናት ነበር።እንደዚህ አይነት ነገሮች መደረግ አለባቸው።»በማለት ከገለፁ በኋላ፤«ዲጅታል ግንዛቤን ማሳደግ፣ ዲጅታል ክህሎትን ማሳደግ፣ መሰረተልማቶችን ማስፋፋት እንዲሁም በማኅበረሰብ ዘንድ በኢኮኖሚም ሆነ በሌሎችም በትምህርትም፣ በእድሜም ፣በፆ ታም የተፈጠሩ ኢ እኩልነቶችን እንዳይሰፉ መጠንቀቅ አለብን።ይሄን ይመስላል።የብዙ ባለድርሻዎችን ርብርብ የሚጠይቅ ነው።»በማለት ገልፀዋል።እየጨመረ የመጣው የኢንተርኔት አፈና በኢትዮጵያ

ያካልሆነ ግን የበይነመረብ አጠቃቀም ከዚህ ቀደም በማህበረሰቡ የነበሩ የእኩልነት እና የኢፍትሃዊነት ችግሮችን እያሰፋ ሊሄድ ይችላል የሚል ስጋት አላቸው። «ይህ ግኝት ሙሉበሙሉ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ገፅታ ያሳያል ማለት አይደለም። ነገር ግን እንደ አንድ መስኮት ኢትዮጵያ ውስጥ ኢንተርኔት ተጠቃሚነት ከአንድ አራተኛ በታች ህዝብ ነው ኢንተርኔት የሚያገኘው። በዚህ ደረጃ ትንሽ ሆኖ ሳለ በህዝቦች መካከል ያለው የተጠቃሚነት አለመመጣጠን በዚህ ደረጃ ከሆነ በዚህ ደረጃ ቢስፋፋ ሌሎች አገልግሎት ሰጪ የቴሌ ድርጅቶችም ሲመጡ ይህንኑ ኢ እኩልነት የሚያባዙ ከሆነ በዜጎች ዘንድ ያለው የኢኮኖሚ የማህበራዊ ምክንያቱም ከዚህ በኋላ ሁሉም ነገር ዲጅታል እየሆነ ነው የሚሄደው፤እድሎች ዲጅታል ናቸው። ስለዚህ የነበሩ  ኢ እኩልነቶችን ነው እያባዙ የሚሄዱት።ስለዚህ በዚህ ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲደረግ ሁሉም ባለድርሻ አካላት አይናቸውን እና ልባቸውን እንዲጥሉ ለማሳሰብ እወዳለሁ።» በማለት አቶ መንግስቱ አሰፋ አብራርተዋል።

 

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።

ፀሀይ ጫኔ
ዮሀንስ ገብረእግዚአብሄር