1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ የሚፈቅደው አዋጅ ይዘትና የተነሱበት ሥጋቶች

ሰለሞን ሙጬ
ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 8 2017

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሁለት መሰረታዊ የተባሉ ባንክ ነክ አዋጆችን አጽድቋል። ብሔራዊ ባንክን ከሌሎች ሀገራት አቻ ማዕከላዊ ባንኮች እኩል የሚያደርገው አንዱ ነው። ሌላኛዉ ደግሞ ማንኛውም የውጭ ባንክ በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ በባለቤትነት የሚይዘው የውጭ ባንክ ተቀጥላ እንዲያቋቁም የሚፈቅደው የባንክ ሥራ አዋጅ ነው።

https://p.dw.com/p/4oFlN
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክምስል Solomon Muchie/DW

የውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ የሚፈቅደው አዋጅ ይዘትና የተነሱበት ሥጋቶች

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቱ ዛሬ ማክሰኞ ሁለት መሰረታዊ የተባሉ ባንክ ነክ አዋጆችን አጽድቋል። ብሔራዊ ባንክን ከሌሎች ሀገራት አቻ ማዕከላዊ ባንኮች እኩል የሚያደርገው ነው የተበለለት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ረቂቅ አዋጅ አንዲ ነው። ሌላኛው ደግሞ ማንኛውም የውጭ ባንክ በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ በባለቤትነት የሚይዘው የውጭ ባንክ ተቀጥላ እንዲያቋቁም የሚፈቅደው የባንክ ሥራ አዋጅ ነው። የባንክ ሥራ አዋጅ መፈቀድ የሀገር ውስጥ የንግድ ባንኮችን ከውድድር ውጭ እንዳያደርግ ሥጋት መፍጠሩ በምክር ቤት አባላት የተነሳ ቢሆንም የብሔራዊ ባንክ ገዢ አቶ ማሞ ምህረቱ ሁኔታው የሀገር ውስጥ ባንኮችን የሚያፈርስ አለመሆኑን፤ በዚህ ወቅት ባንኮች ጤናማ መሆናቸውን እና የተረጋጋ ያሉት የፋይናንስ ሥርዓት መኖሩንም ገልፀዋል። 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አዋጅ የያዛቸው ድንጋጌዎች

የብሔራዊ ባንክ ገዢ አቶ ማሞ ምህረቱ ይህ አዋጅ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክን "ከሌሎች አቻ ማዕከላዊ ባንኮች እኩል የሚያደርግ ነው" ብለዋል። በተጨማሪም የባንክን አሠራር ዘመናዊ የሚያደርግ፣ በብዙ መልኩ የሚያራምድ እና ባንኩ ከመንግሥት ጋር ያለውን ግንኙነት በግልጽ ያስቀመጠ መሆኑን ጠቅሰዋል። የፀደቀው አዋጅ "ክሪፕቶ ከረንሲ ወይም ሌላ ማንኛውም ዲጂታል ወይም የኤሌክትሮኒክ ገንዘብ እንደ መገበያያ ገንዘብ አድርጎ በኢትዮጵያ ውስጥ መጠቀም የተከለከለ ተግባር ነው" ይላል። 

የባንክ ሥራ አዋጅ ምን ይዟል? 

የባንክ ሥራ ረቂቅ አዋጅ ብዙ አዳዲስ እና መሠረታዊ የባንክ ሥራ ድንጋጌዎችን አካትቷል። በረቂቁ አዋጁ ከተካተቱት ድንጋጌዎች መካከል "ማንኛውም የውጭ ባንክ በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ በባለቤትነት የሚይዘው የውጭ ባንክ ተቀጥላ እንዲያቋቁም ወይም የውጭ ባንክ ቅርንጫፍ እንዲከፍት ወይም የባንክ አክሲዮኖችን እንዲይዝ ሊፈቀድለት ይችላል" በሚል ደንግጓል። በተመሳሳይ "የውጭ ሀገር ዜጎች ወይም በውጭ ሀገር ዜጋ ባለቤትነት የተያዙ የኢትዮጵያ ድርጅቶች የባንክ አክሲዮን እንዲይዙ ሊፈቅድ ይችላል" በሚል ተደንግጓል። "የውጭ ሀገር ዜጎች በባንክ ውስጥ ልዩ እውቀት ወይም ሙያ በሚጠይቁ የሥራ መደቦች ላይ በብሔራዊ ባንክ ፈቃድ ከአምስት ዓመት ላልበለጠ ጊዜ" ሊቀጠሩ እንደሚችሉ፣ "የውጭ ባንኮች ነባር የሀገር ውስጥ ባንኮችን በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ በግዢ አማካኝነት እንዲይዙ" ፣ " የውጭ ዜጎች እና ሙሉ በሙሉ በውጭ ሀገር ዜጎች በባለቤትነት የተያዙ የኢትዮጵያ ድርጅቶች በአንድ ባንክ ኢንቨስት ማድረግ የሚችሉት በውጭ ሀገር ገንዘብ ብቻ" ስለመሆኑ፣ "ማንኛውም ሰው ከባንክ በተገኘ ብድር የአንድ ባንክ አክሲዮን መግዛት" እንደማይችልም ተደንግጓል።

በባንክ ሥራ አዋጅ የተነሱ ጥያቄዎች 

በዛሬው የምክር ቤት ውሎ የውጭ ባንኮች ወደ ሀገር ውስጥ ገበያ ሲቀላቀሉ የሀገር ውስጥ በንኮችን እንዳይጎዱ፣ ከገበያ እና ከውድድር እንዳያስወጡ፣ አልፎም የሀገር ውስጦች ተሽመድምደው "የሀገር ሉዓላዊነት እንዳይጎዳ" ምን ታስቧል የሚል ጥያቄ ቀርቧል። በተመሳሳይ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ በንኮች ሀብት የማሸሽ አዳጋ እንዳይፈጥሩ ምን ታስቧል? ይህ እርምጃ የግል "ባንኮች ይጥፉ ብሎ የመወሰን ያህል" አደጋ አያስከትልም ወይ? የሚሉ ሥጋቶች ቀርበዋል። የብሔራዊ ባንክ የቁጥጥር አቅም እና የግል በንኮች ተዋህደው እና ቁጥራቸው ውሱን እስኪሆንና ተወዳዳሪ መሆን የሚችሉበትን አቅም እስኪፈጥሩ ለምን መጠበቅ አላስፈለገም የሚሉትም ከተነሱ ጥያቄዎች መካከል ናቸው።

አዲስ አበባ ከተማ
አዲስ አበባ ከተማ ምስል Solomon Muchie/DW

የብሔራዊ ባንክ ገዢ የሰጡት ምላሽ

የብሔራዊ ባንክ ግዢው አቶ ማሞ ምህረቱየባንክ ሥራ አዋጅከፍተኛ ለውጥ በዘርፉ ላይ የሚያስከትል፣ መሠረታዊ የሕግ ማሻሻያ ነው ብለዋል። የማሻሻያው ውሳኔ ከሦስት ዓመታት በፊት የተደረገ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ማሞ በችኮላ የተገባበት ሥራ እንዳልሆነም ተናግረዋል። "የውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ ገበያ ስለገቡ የሀገር ውስጥ ባንኮች ይፈርሳሉ የሚል እምነት የለንም" ያሉት የባንኩ ገዢ በማሳያነትም ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡት የውጭ ባንኮች ቁጥር የተወሰነ እንደሚሆን፣ በሽርክና እና ከሀገር ውስጦቹ ጋር በጋራ እንደሚሠሩ ተናግረዋል። የባንኩን የቁጥጥር አቅም በሚመለከትም "ሥራውን ለማስቀጠል የምንችልበት አቅም ላይ ነን" ሲሉ ተደምጠዋል። ይልቁንም ማዕከላዊ ባንኩ የንግድ ባንኮች የቀውስ ጊዜ ሲገጥማቸው ለዚያ ቀውስ መፍትሔ ለመስጠት አቅም ያገኙበት አዋጅ ስለመሆኑ አብራርተዋል።

የገንዘብ ባለሙያ አስተያየት

በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸው የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው አቶ ዳዊት ታደሰ የውጭ ባንኮች ወደ ሀገር ውስጥ መግባታቸውን የሚፈቅደው ሕግ መጽደቅ ባንኮቹ የተሻለ የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲያደርጉ ከማስቻሉ በላይ የብድር አማራጮችን በማስፋት ለትልልቅ ፕሮጀክቶች እና ብድር ፈላጊ አልሚዎች የተሻለ ዕድል ይዘው ይቀርባሉ ብለዋል። አክለውም በሀገሪቱ ኢንቨስትመንት ፍሰት ላይ አወንታዊ ሚና እንደሚኖራቸው ጠቁመዋል። ሆኖም ግን የሀገር ውስጥ ንግድ ባንኮች መወዳደር ካልቻሉ የህልውና አደጋ ውስጥ ሊገቡ እንደሚችሉ፣ የሀገርን ሀብት የማሸሽ ችግር ውስጥም ሊገቡ እንደሚችሉ ሥጋታቸውን ጠቅሰዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ በአሁኑ ወቅት ሁለት የመንግሥት እና 30 የግል ባንኮች መኖራቸው፣ ጠቅላላ ሀብታቸውም 3.3 ትሪሊዮን ብር መሆኑ እና ሰባት ባንኮች ደግሞ በምስረታ ሒደት ላይ መሆናቸው ከዚህ በፊት ተገልጿል።

ሰለሞን ሙጬ 

አዜብ ታደሰ 

ሸዋዬ ለገሠ