1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዓለም ዜና፤ ታህሳስ 7 ቀን 2017 ዓ.ም ሰኞ

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 7 2017

--ባለፉት 8 ቀናት በጎጃም ቀጠና የነበረው የእንቅስቃሴ ገደብ መነሳቱን የአማራ ፋኖ በጎጃም አስታወቀ። የአማራ ፋኖ በጎጃም የህዝብ ግንኙነት መምሪያ ምክትል ኃላፊ እንደሆኑ የገለፁልን ዮሐንስ ዓለማየሁ ባለፉት 8 ቀናት በጎጃም ቀጠና አንዳንድ አካባቢዎች በተደርጉ ውጊያዎች ህብረተሰቡ በመንግድ ሊገጥመው የሚችለውን ሞትና እንግልት ለማስወገድ የመንገድና የንግድ እንቅስቃሴዎች ላይ ገደብ ተጥሎ መቆየቱን ተናግረዋል። -- የቱርኩ ፕሬዚዳንት ራቺብ ታይብ ኤርዶጋን በቅርቡ ኢትዮጵያን እና ሶማልያን እንደሚጎበኙ ተነገረ።--የሶርያዉ ባሽር አልአሳድ ከሶሪያ አቅጄ አልወጣሁም ለመዉጣትም እቅድ አልነበረኝም፤ የወጣሁት በሩስያ ነዉ አሉ።

https://p.dw.com/p/4oDMv

ጎጃም፤ እንቅስቃሴ ገደብ መነሳቱን የአማራ ፋኖ አስታወቀ

ባለፉት 8 ቀናት በጎጃም ቀጠና ተጥሎ የነበረው የእንቅስቃሴ ገደብ መነሳቱን የአማራ ፋኖ በጎጃም አስታወቀ። በነበረው የመንገድ መዘጋጋት በአርሶ አደሩና በህሙማን ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሶ እንደነበር አስተያየት ሰጪዎች ተናገረዋል። የአማራ ፋኖ በጎጃም የህዝብ ግንኙነት መምሪያ ምክትል ኃላፊ እንደሆኑ የገለፁልን ዮሐንስ ዓለማየሁ ባለፉት 8 ቀናት በጎጃም ቀጠና አንዳንድ አካባቢዎች በተደርጉ ውጊያዎች ህብረተሰቡ በመንግድ ሊገጥመው የሚችለውን ሞትና እንግልት ለማስወገድ የመንገድና የንግድ እንቅስቃሴዎች ላይ ገደብ ተጥሎ መቆየቱን ተናግረዋል። በዚህም የበርካታ ንፁሐን ዜጎችን ህይዎት ከሞት መታደግ መቻሉን ነዉ ያመለከቱት። “እገዳው ከዚህ በላይ መቀጠሉ በህዝብ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ላይ የሚያደርሰውን ጫና በማገናዝብ ከነገ ታሀሳሰ 8/2017 ዓ ም ጀምሮ የእንቅስቃሴ ገደቡ ተነስቷል” ብለዋል።
በእንቅስቃሴ ገደቡ ምክንያት አንዳንድ አርሶ አደሮች በቀላሉ የሚበላሹ ምርቶችን ወደ ገበያ ማድረስ ባለመቻላቸው በምርቶቻቸው ላይ ብልሽት ማጋጠሙን፣ እንዲሁም ወላጆችና ሌሎች ህሙማን ተገቢውን ህክምና ማግኘት እንዳልቻሉ የቢቸና፣ የደብረወርቅና የጎንጂ ቆለላ አስተያየት ሰጪዎች አመልክተዋል። አስተያየታቸውን ከሰጡን መካክል የሚከተሉት ይገኙበታል። የአማራ ፋኖ በጎጃም ከህዳር 30/2017 ዓ ም ጀምሮ በቀጠናው ከአምቡላንሶች በስተቀር  በሁሉም ዓይነት እንቅስቃሴዎች ላይ ላለተወሰነ ጊዜ ገደቦችን ጥሎ ነበር።

ቱርክ፤ ኤርዶጋን ኢትዮጵያና ሶማልያን ሊጎበኙ ነዉ

የቱርክ ፕሬዚዳንት ራቺብ ታይብ ኤርዶጋን ከ 15 ቀናት በኋላ በሚጠባዉ የጎርጎረሳዉያኑ 2025 ዓመት መጀመርያ ኢትዮጵያን እና ሶማልያን እንደሚጎበኙ ተነገረ። ኤርዶጋን በኢትዮጵያ እና ሶማልያ መካከል የነበረዉን ዉጥረት ለመቋጨት ባለፈዉ ሳምንት አንካራ ላይ ከሁለቱ ሃገራት መሪዎች ጋር ለስምምነት ከተቀመጡ በኋላ ይህን ያስታወቁት ትናንት  በ x ገጻቸዉ ላይ መሆኑን የፈረንሳዩ የዜና አገልግሎት አዣንስ ፍራንስ ፕሬዚስ ዛሬ ዘግቧል።  የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እና የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ ባለፈዉ ሳምንት ታህሳስ 2 ቀን 2024 ዓ.ም አንካራ ላይ ያደረጉትን ስምምነት ተከትሎ፤ ኤርዶጋን በአዲሱ 2025 ዓመት የመጀመርያዎቹ ሁለት ወራት፤ ኢትዮጵያን እና  ሶማልያን እጎበኛለሁ ማለታቸዉን መረጃዉ አመልክቷል። ባለፈዉ ሳምንት ኢትዮጵያ እና ሶማልያ አንድ ዓመት የዘለቀዉን ዉዝግባቸዉን አካራ ላይ በቱርኩ ፕሬዚዳንት ኤርዶጋን አሸማጋይነት ለሰዓታት ከዘለቀ ውይይት በኋላ ያመጡት ዉጤት “ታሪካዊ” መባሉም ተመልክቷል።  በኢትዮጵያ እና ሶማልያ መካከል በያዝነዉ 2024 ዓመት መጀመርያ ወር ጀምሮ ዉዝግብ የጀመሩት  ወደብ አልባዋ ኢትዮጵያ በራዝ ገዝዋ ሶማሊላንድ የባህር ወደብን ለመጠቀም እና ወታደራዊ ሰፈርን ለማቋቋም የመግባብያ ከስምምነት ከተፈራረሙ በኋላ ነበር። በምላሹ በጎርጎረሳዉያኑ 1991 ዓ.ም ከሶማልያ ተገንጥላ ነጻነትዋን ያወጀችዉ ራስ ገዝዋ ሶማሊላንድ፤ የሞቃዲሾ ዕውቅና በሌለበት፤ ከኢትዮጵያ የአገርነት ዕውቅናን እንደምታገኝ ገልፃ ነበር። ይሁን እና ይህ መረጃ ከአዲስ አበባ በኩል ማረጋገጫ እንዳልተሰጠዉ ይታወቃል። ሶማሊያ በኢትዮጵያ እና በራስ ገዝዋ ሶማሊላንድ በኩል የተፈፀመዉ የመግባብያ ስምምነት ሉዓላዊነቷን የሚጥስ እና በአፍሪቃዉ ቀንድ ቀጠና ዳግም ግጭትን የሚፈጥር ስትል በዓለም አቀፍ ደረጃ የማስጠንቀቂያ ደወሎችን ስታሰማ መቆየትዋ ይታወሳል። ከአፍሪቃ ህብረት እና ከአዉሮጳ ህብረት አድናቆትን የተቸረችዉ ቱርክ፤ ባለፈዉ ሳምንት በኢትዮጵያ እና ሶማልያ መካከል የመጀመርያ ስምምነት ከመድረሳቸዉ በፊት ሁለት ጊዜ በአንካራ አንድ ጊዜ ኒዮርክ ላይ ለዉይይት ተቀምጣ እንደነበር ተዘግቧል።  ከሰሞንኛዉ የቱርክ የዲፕሎማሲ ስኬት በተጨማሪ በሱዳን እና በተባበሩት አረብ ኢምሬትስ መካከል የሚታዩትን አለመግባባቶች ለመፍታት የቱርኩ ፕሬዚዳንት ኤርዶጋን፤ ጣልቃ እንደሚገቡ የፕሬዚዳንቱ ጽ/ቤት ማስታወቁ ተመልክቷል። 

ሱዳን፤ ሰፊ ፆታዊ ጥቃት በሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይላትና አጋር ሚሊሺያዎች

 ከሱዳን ጦር ሰራዊት ጋር የሚዋጉት የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይላትና አጋር ሚሊሺያዎች በሃገሪቱ ሰፊ የጾታዊ ጥቃት እየፈፀሙ ነዉ ሲል ዓለምአቀፉ የሰብዓዊ መብት ተከራካሪዉ ድርጅት ሂውማን ራይትስ ዎች (HRW) አስታወቀ።  ሂውማን ራይትስ ዎች (HRW) በአዲስ ይፋ ባደረገዉ ዘገባ፤ በደቡብ ኮርዶፋን ግዛት ጾታዊ ጥቃት የተፈፀመዉ ከሰባት እስከ 50 ዓመት እድሜ ክልል ባሉ ሴቶች እና ልጃገረዶች ላይ ነዉ። የሰብዓዊ መብት ተከራካሪዎች ድርጅት ይፋ እንዳደረገዉ፤ በደቡብ ኮርዶፋን ግዛት፤ በቡድን አስገድዶ መድፈር እና ጾታዊ ባርነትን ጨምሮ ጾታዊ ጥቃቶች ካለፈዉ የጎርጎረሳዉያን መስከረም 2023 ጀምሮ እስከ ጎርጎረሳዉያኑ 2024 ድረስ ተመዝግቧል። በሱዳን የ20 ወራት የቀጠለዉ የእርስ በእርስ ጦርነት ጾታዊ ጥቃትን በተመለከተ መቀመጫዉን ኒዮርክ ላይ ያደረገዉ ዓለምአቀፍ ተቆጣጣሪዎች ቡድን በቅርቡ ይፋ ያደረገዉ መግለጫን ተከትሎ ዩናይትድ ስቴትስ የዓለማችን እጅግ የከፋዉ ሰብዓዊ ቀውስ ማለትዋ የሚታወስ ነዉ።    
በሱዳን ከሱዳን ጦር ሰራዊት ጋር የሚዋጉት የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይላትና አጋር አረብ ሚሊሺያዎች በደቡብ ኮርዶፋን ግዛት፤ በተለይም  በኑባ ሲቪሎች ላይ ከታህሳስ 2023 እስከ ሚያዝያ 2024 ድረስ በርካታ ጥቃቶችን መፈፀማቸዉን ተቀማጭነቱን ኒውዮርክ ያደረገዉ ተቆጣጣሪ ድርጅት ባለፈው ሳምንት ይፋ ባደረገዉ ልዩ ዘገባ አመልክቷል። በዘገባዉ መሰረት በደቡብ ኮርዶፋን በሲቪሎች ላይ የደረሰዉ ሰፊ ጥቃት ትኩረት ያላገኘ እና እንብዛም ያልተዘገበ ነዉ። በርካታ የክርስትያን እምነት ተከታይ ነዋሪዎች የሚገኙበት ደቡብ ኮርዶፋን እና ከፊል ብሉ ናይል ግዛት የሱዳን ህዝቦች ነፃ አውጪ ንቅናቄ-ሰሜን (SPLM-N) የተሰኘዉ አማፂ ቡድን የሚቆጣጠረዉ ስፍራ መሆኑ ይታወቃል።  

ኤኮዋስ፤ ማሊ ቡርኪናፋሶ እና ኒጀር ከህብረቱ የመዉጣት ዉሳኔ

የምዕራብ አፍሪቃ መንግሥታት የኤኮኖሚ ማህበረሰብ፡ ኤኮዋስ፤ በወታደራዊ አስተዳደር የሚመሩትን እና ማህበሩን  ለመልቀቅ የወሰኑት ሦስት ሃገራት ማለትም ማሊ፤ ቡርኪናፋሶ፤ እና ኒጀርን ዉሳኔያቸዉን እንደገና እንዲያጤኑት በመጠየቅ የመልቀቅያ ቀን ዉሳኔዉን ለስድስት ወራት አራዘመ። ይህ የኤኮዋስ ዉሳኔ የተሰማዉ ሦስቱ የምዕራብ አፍሪቃ ሃገራት ከምዕራብ አፍሪቃ መንግሥታት የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ኤኮዋስ የመዉጣት ዉሳኔ የማይቀለበስ መሆኑን ካሳወቁ በኋላ መሆኑ ነዉ። ሦስቱ የቀድሞ የፈረንሳይ ቅኝ ግዛት ሃገሮች ማሊ፤ ቡርኪናፋሶ እና ኒጀር ኤኮዋስን ለመልቀቅ ዉሳኔ ካስተላለፉ በኋላ፤ የሳህል ግዛቶች በሚል የራሳቸዉ ማኅበር ማቋቋማቸዉ ይታወቃል።  ባለፈዉ በጥር ወር የሦስቱ የሳህል ሃገሮች አስተዳዳሪ ወታደራዊ ጁንታ 15ቱን ሀገራት ማህበር ለቀው እንደሚወጡ ሲያስታዉቁ ድርጅቱ “ኢሰብአዊ እና ኃላፊነት በጎደለው መልኩ ማዕቀብ በማድረግ እና ለቀድሞ ቅኝ ገዢ ፈረንሳይ ታዛዥ የሆነ ሲሉ መክሰሳቸዉ ይታወሳል። የሦስቱ ምዕራብ ሃገራት ከህብረቱ የመዉጣት ዉሳኔ ተፈፃሚነት እዉን የሚሆነዉ በሚቀጥለዉ ወር ሲሆን እንደ ህብረቱ ህግ፤  ሃገራት ማህበሩን እንደሚወጡ ባሳወቁ በአንድ ዓመት ተፈፃሚ ይሆናል። የሦስቱ የሳህል ግዛት ሃገሮች በቅርቡ ህብረቱን መልቀቅ በአካባቢዉ ላይ ለሚደረገዉ ነጻ ንግድ እና እንቅስቃሴ ላይ እንዲሁም ከአልቃይዳ እና ከእስላማዊ መንግስት ጋር የተሳሰሩ ጂሃዲስቶች እየተጠናከሩ ባሉበት በዚህ አካባቢ በፀጥታ ትብብር ላይ ትልቅ ተፅእኖ ሊኖረው እንደሚችል ተገልጿል። 

ሶርያ ፤ የተባበሩት መንግስታት የሶሪያ ልዩ መልዕክተኛ ከአማፂያኑ መሪ ጋር ተናገሩ

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሶሪያ “ታማኝ እና ሁሉን አቀፍ” ሽግግር ማድረግ ይኖርባታል ሲል ባሻር ኧል አሳድን ከስልጣን ላባረረዉ ለእስላማዊው ለሃያት ታህሪር አል ሻም ቡድን መሪ አስታወቀ። ትናንት እሁድ ደማስቆ የገቡት የተባበሩት መንግስታት የሶሪያ ልዩ መልዕክተኛ ገይር ፔደርሰን፤ ሶርያን የተቆጣጠረዉን ቡድን መሪ አቡ መሀመድ አል ጆላኒን ማግኘታቸውን የፔደርስን ጽ/ቤት ይፋ ባደረገዉ ቴሌግራም  አስታዉቋል።  በመረጃዉ መሰረት ሶርያን የተቆጣጠረዉ  ቡድን መሪ አቡ መሀመድ አል ጆላኒን አሁን በእዉነተኛ ስማቸዉ ፤ አህመድ አል ሻራ በሚል እንደሚታወቁም መግለጫዉ አክሎ አትቷል።  በተባበሩት መንግሥታት የሶርያ ልዩ መልዕክተኛ ፤ ደማስቆ ላይ በበሽር አልአሳድ መንግሥት ሥር የነበሩትን የቀድሞዉን የሶርያዉን ጠቅላይ ሚኒስትርንም ማግኘታቸዉ ተመልክቷል። 
ፔደርሰን ባለፈዉ ቅዳሜ በሶርያ ጉዳይ ዮርዳኖስ ውስጥ በተካሄደዉ ዓለም አቀፍ ስብሰባ ላይ እንደተናገሩት፤በተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት ውሳኔ 2254 (2015) መርሆዎች ላይ እንደተገለፀዉ፤  ታማኝ እና ሁሉን አቀፍ የፖለቲካ ሽግግር በሶርያ አስፈላጊ መሆኑን አፅንዖት ሰጥቷል። ከዚህ በተጨማሪ ልዑኩ ፤  የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ለሶሪያ ህዝብ ሁሉን አይነት ዕርዳታ ለመስጠት ያለውን ፍላጎት እና ለአስቸኳይ እና ቅድሚያ ለሚሰጧቸው ጉዳዮች ግን ቅድምያ እንደሚሰጥ አስታዉቀዋል። 

ሩስያ፤ ሩስያ ከአገሪ አሶጣችኝ ያሉት አልአሳድ 

ከስልጣን የተወገዱት የሶሪያ ፕሬዝዳንት በሽር አል አሳድ  በታጣቂዎች ወደ መዲና ደማስቆ እየገሰገሱ ባለበት ወቅት አገራቸዉን ጥለዉ ለመሄድ እንዳላሰቡ ገለፁ። አሳድ እንዳሉት ሩስያ ከነበሩበት ስፍራ ይዛቸዉ እንደወጣች ገልፀዋል። ሽምቅ ተዋጊዎቹ እየገሰገሱ ባለበት ክስተት፤ አልያም በፍልምያ ወቅት ስልጣን ለመልቀቅም ሆነ መጠግያ ለመፈለግ አላሳብኩም ያሉት ኧል አሳድ፤ ማንም ሰዉ መጠግያ እንስጥህ ያለኝም የለም ሲሉ በሶርያ የፕሬዝዳንቱ የቴሌግራም ቻናል ላይ በጽሑፍ መቀመጡን ዜና ምንጩ አትቶ ዘግቧል። "ከሶሪያ አቅጄ አልወጣሁም ለመዉጣትም እቅድ አልነበረኝም ፤ አንዳንዶች እንደሚሉት በጦርነቱ የመጨረሻዎቹ ሰዓታት የወጣሁትም በእቅድ አይደለም ሲሉ አሳድ ይፋ ባደረጉት መረጃ አክለዋል። በጎርጎረሳዉያኑ 2000 ዓም የአባታቸዉን ሞት ተከትሎ ወደ ስልጣን የመጡት ኧል አሳድ፤ እስከ ኅዳር  29 ማለዳ ድረስ ደማስቆ ቆይተዉ፤ ተፋላሚዎች ደማስቆን ሲጠጉ የባህር ዳርቻ በሆነችዉ እና የሩስያ የጦር ሰፈር ወደ ሚገኝባት ወደ ላቲኪያ ማቅናታቸዉ ተመልክቷል። በሩስያ ጦር ሰፈር አካባቢ ኧል አሳድን በአይሮፕላን ለማሳፈር እና አካባቢዉን ከአደጋ ለመጠበቅ ከፍተኛ የድሮን ጥቃቶች እንደነበሩም ተመልክቷል።  

የአዉሮጳ፣ ወደ ሶርያ ያቀናዉ የአዉሮጳ ህብረት ልዑክ 

የሶሪያ የአውሮጳ ህብረት ልዑክ ከአዲሱ የሀገሪቱ እስላማዊ ገዥዎች ጋር ለመነጋገር ዛሬ ወደ መዲና ደማስቆ አቀና። የአዉሮጳ ህብረት ልዑክ ወደ ሶርያ ዛሬ የተጓዘዉ ፕሬዝዳንት በሽር አል አሳድ ከስልጣን ከተወገዱ እና በሶርያ ለአስርት ዓመታት የዘለቀው  አስከፊ አገዛዝ እና የእርስ በርስ ጦርነት ካበቃ ከአንድ ሳምንት በኃላ መሆኑ ነው። የብራሰልስ ይህ እርምጃ የመጣዉ ዩናይትድ ስቴትስ እና ብሪታንያ በሶሪያ ዋና ከተማ ከሚገኙት አዲስ ባለስልጣናት ጋር ግንኙነት ማድረጋቸውን ከተናገሩ በኋላ ነው። የአዉሮጳ ህብረት ከፍተኛ ዲፕሎማት ወደ ደማስቆ እንዲሄድ እና ከአዲዱ መንግሥት ጋር እንዲነጋገር ኃላፊነት ሰጥቻለሁ ያሉት፤ የአዉሮጳ ኅብረት የዉጭ ፖሊሲ ኃላፊ ካጃ ካላስ  ከአዲሱ አመራር ጋር በምን አይነት ደረጃ እንገናኛለን እና በእርግጥ ሶሪያ ወደ ትክክለኛው አቅጣጫ እየተራመደች መሆንዋን ካየን ምን ተጨማሪ እርምጃዎችን ለመውሰድ ፈቃደኞች ነን በሚለዉ ላይ የህብረቱ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ዛሬ እየተነጋገሩ መሆኑን ገልፀዋል። « በመጀመሪያ ከሶሪያ አዲስ አመራር ጋር በምን አይነት ደረጃ እንደምንገናኝ እና ከእነሱ ጋር ግንኙነት ለመፍጠር ምን አይነት እርምጃዎችን ለመውሰድ ፍቃደኛ እንደሆንን መወያየት አለብን። እስካሁን ያሉት ነገሮች ቃላቶች ብቻ ናቸዉ። ይሁን እና ቃላቶች ብቻ ሳይሆኑ ተግባራዊነታቸዉን እና ወደ ትክክለኛ አቅጣጫ መሄዳቸዉን  ማየት እንፈልጋለን። እንደሚመስለኝ የሚቀጥሉት ሳምንታት እና ወራቶች ወደ ትክክለኛው አቅጣጫ መሄድ አለመሄዳቸዉን  ያሳዩናል ብዬ አስባለሁ።  ይህን ተከትሎ ለቀጣይ እርምጃዎች ለመወያየት ክፍት እንሆናለን።» 

ጀርመን፤ የመተማመኛ ድምፅን አጡ

የጀርመን ፓርላማ  ቡንደስ ታግ ዛሬ በመራሔ መንግሥት ኦላፍ  ሾልዝ ላይ የመተማመኛ ድምፅ ሲጠይቅ ነዉ የዋለዉ።  ሾልዝ የመተማመኛ ድምፅን አተዋል። በመራሄ መንግሥቱ ላይ የመተማመኛ ድምፅ ለመካሄድ የተወሰነዉ በቅርቡ ጥምረቱ የፈረሰበት የጀርመን መንግሥትን ለመተካት ዋነኞቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሦስት ወራት ጊዜ ውስጥ ሀገር አቀፍ ምርጫ ለማካሄድ ስምምነት ላይ ከደረሱ በኋላ ነዉ። ምርጫዉ ከመካሄዱ በፊት ግን በመራሔ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ ላይ የመተማመኛ ድምፅ እንዲካሄድ ተጠይቆ ነበር። መራሔ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ የመተማመኛ ድምፅ ማጣታቸዉ የተሰማዉ ዛሬ ምሽት ላይ ነዉ። የጀርመን ፓራላማ በቻንስለር ኦላፍ ሾልዝ ላይ ያለውን እምነት ባካሄደዉ ድምፅ አሰጣጥ ማንሳቱን ዛሬ ይፋ አድርጓል።  ለመራሔ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ በመተማመኛ ድምፅ የሰጡ 207 የፓርላማ አባላት ሲሆኑ 394 የፓርላማ አባላት ደግሞ ሾልዝን ተቃዉመዋል። 116 የፓራላማ አባላት ደግሞ ድምፀ ተአቅቦ አድርገዋል። እንደታሰበው ሁሉ የጀርመኑ መራሔ መንግሥት ቢያንስ የ367 ድምፅ ማጣታቸዉ ይፋ ሆንዋል። ዛሬ በጀርመን ፓርላማ ቡንደስታግ የተካሄደዉን የመተማመኛ ድምፅ አሰጣጥና ዉጤቱን ተከትሎ፤ የሶሻል ዲሞክራቶቹ መራሔ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ ለጀርመን ፌደራል መንግሥት ምርጫ ጥርግያ መንገዱን መክፈታቸዉ ይፋ ሆንዋል። 
የጀርመኑ ቻንስለር ኦላፍ ሾልዝ እስከያዝነዉ የጎርጎረሳዉያን 2024 ዓመት መጨረሻ አዲስ ምርጫ እንዲካሄድ ለማስቻል በጀርመን ፓርላማ ቡንደስታግ የመተማመኛ ድምፅ እንዲሰጥባቸዉ እንደሚሰሩ ቀደም ብለዉ አስታዉቀዉ እንደነበር የሚታወስ ነዉ። የሶሻል ዲሞክራት ፓርቲ አባሉ፤ የጀርመኑ ቻንስለር ኦላፍ ሾልዝ፤ ከጀርመን ከቴሌቪዥን ጣብያ ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ «የፓርላማ አባላቱ አዲስ ለሚካሂዱት ምርጫዎች የጊዜ ሰሌዳ ላይ መስማማት ይኖርባቸዋል፤ ቀኑ ሲወሰን፤ በቀጣይ የሚደረጉ እቅዶች ላይ ለመስራት እችላለሁ» ሲሉ ተናግረዉም ነበር።  በአፋጣኝ በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠ አዲስ ሕጋዊ መንግሥት እንደሚያስፈልግም ሾልዝ ገልፀዉ ነበር።

አዜብ ታደሰ

ሸዋዬ ለገሠ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ስለዚሕ ዝግጅት

ስለዚሕ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።