ኢትዮጵያ፤ የአማራ ክልል የደራን ግድያ አወገዘ
“ፅንፈኛና ሽብርተኛ” ያላቸው አካላት ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ደራ ወረዳ ፈጸሙት ያለውን ግድያ እንደሚያወግዝ የአማራ ከልል መንግሥት አስታወቀ፡፡ የክልሉ መንግሥት ትናንት ማመሻውን ባወጣው መግለጫ፣ በአማራ ክልል “ፅንፈኛ” ሲል የጠራውን ታጣቂ ቡድንና “ሸኔ” ሲል የጠራውንና በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሰውን ቡድን፤ ግድያ፤ እገታ፤ ዝርፊያና አፈና ይፈፅማሉ ሲል ከሷል። “ሁለቱም ኃይሎች ለአንድ ዓላማ ሁለት ቦታ የተሰለፉ ቡድኖች ናቸው” ያለው መግለጫው፤ሰሞኑን የተፈጸመው ደርጊትም የአማራ እና የኦሮሞ ሕዝቦችን ለመነጣጠል እና ወደ ግጭት ለማስገባት የተደረግ ሴራ ነዉ ሲል የክልሉ መንግስት አመልክቷል፡፡
የአማራ ሕዝብና የአማራ ክልል መንግሥት ከኦሮሞ ሕዝብና ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት እንዲሁም ከፌዴራል መንግሥት ጋር በመሆን የድርጊቱን ፈፃሚዎች ለሕግ ቀርበው አስፈላጊዉን ቅጣት እንዲያገኙ እየተሰራ እንደሆነም የአማራ ክልል መንግሥት ያወጣው መግለጫ ያሳያል፡፡ ያም ሆኖ፤ የሰሞኑን ግድያ በገለልተኛ ወገን እንዲጣራ በተለያዩ ወገኖች ጥሪ እየቀረበ ነው።
የአማራ ክልል መንግሥት ያወጣውን መግለጫ ይዘን ተጨማሪ አስተያየት ለማካትተ ለአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ ለዶ/ር መንገሻ ፋንታው ያደረግነዉ ተደጋጋሚ የስልክ ጥሪ፤ ስልካቸውን ባለማንሳታቸዉ ሊሳካልን አልቻለም።
አዲስ አበባ፤ ቀሲስ በላይ መኮንን ዛሬ የመከላከያ ምስክሮቻቸውን ማሰማት ጀመሩ
ባለፈው ዓመት ሚያዚያ ወር በአፍሪቃ ኅብረት ቅጥር ግቢ ውስጥ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፍ በአካል ቀርበው ሐሰተኛ የክፍያ ሰነዶችን በመያዝ፣ ለሦስት ግለሰቦችና ለአንድ የግል ድርጅት የባንክ ሒሳቦችን ከስድስት ሚሊዮን ዶላር በላይ ለማውጣት ሞክረዋል በሚል ክስ የተመሰረተባቸው ቀሲስ በላይ መኮንን ዛሬ የመከላከያ ምስክሮቻቸውን ማሰማት ጀመሩ፡፡ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሶስተኛ ሙስና ወንጀል ችሎት ዛሬ የተከሳሾቹን መከላከያ ምስክሮች ሲሰማ አንደኛ ተከሳሽ ቀሲስ በላይ መኮንን ከቆጠሯቸው አምስት ምስክሮች ዛሬ ሁለቱ ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡ ዛሬ በምስክርነት ቃላቸውን የሰጡም ሁለተኛ ተከሳሽ እና ሶስተኛ ተከሳሽ ናቸው፡፡ ከጠበቆቻቸው አንዱ ለዶቼ ቬለ እንደተናገሩትም ዛሬ ቃላቸውን የሰጡት ተከላካይ ምስክሮች ስለተዘጋጀው ሀሰተኛ ሰነድ የሚያውቁት ነገር እንደሌለና ከቀሲስ በላይ ጋርም ምንም አይነት ትውውቅ እንደሌላቸው አስረድተዋል፡፡ ቀሲስ በላይም በችሎቱ ላይ ዛሬ ቀርበው በሰጡት ቃል ወንጀል የተባለውን ድርጊት አለመፈጸማቸውንና ስለድርጊቱ ምንም በማያውቁበት መከሰሳቸውም አግባብ አለመሆኑን ለችሎቱ ማስረዳታቸዉን ጠበቃቸው ተናግረዋል። በከባድ የማታለል የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ከሁለት ተከሳሾች ጋር ዛሬ ፍርድ ቤት የቀረቡት ቀሲስ በላይ ዛሬ ካቀረቡት ሁለት ተከላካይ ምስክሮች በተጨማሪ ቀሪ ሦስት ምስክሮቻቸውን ለማሰማት ለታህሳስ 02 ቀን 2017 ዓ.ም. ተለዋች ቀጠሮ ተሰጥቷቸዋል ሲል የዶቼ ቬለዉ ስዩም ጌቱ ከአዲስ አበባ ዘግቧል።
ግብፅ፤ ቱሪስቶችን ያሳፈረች ጀልባ ሰመጠች 16 ሰዎችን ህይወት ማትረፍ ተችሏል
የአገር ጎብኝዎችን አሳፍራ ግብፅ ቀይ-ባህር ጠረፍ ላይ ትቀዝፍ የነበረች ጀልባ ሰምጣ፤ የ16 የቱሪስቶችን ህይወት ማትረፍ መቻሉን የግብፅ ባለሥልጣናት ዛሬ ገለፁ። 17 ሰዎች ግን የደረሱበት አይታወቅም። ባለሥልጣናቱ ለሮይተርስ ዜና አገልግሎት እንዳስታወቁት፤ በጀልባዉ ላይ የነበሩ ሌሎች ተሳፋሪዎችን እና የጀልባዉን ሰራተኞች ለማትረፍ የርብርብ ሥራዉ ቀጥሏል። ጀልባዋ በአጠቃላይ ከተለያዩ ሃገራት የመጡ 31 ቱሪስቶችን ጨምሮ 45 ሰዎችን፤ እና 14 የጀልባ ሰራተኞችን ጭና ማርሳ -አላም በተሰኘች ቀይ ባህር ዳርቻ ላይ በምትገኝ ከተማ አዋሳኝ ላይ በመቅዘፍ ላይ ነበረች። አደጋዉ የደረሰዉ ዛሬ ከንጋቱ 11 ሰዓት ላይ መሆኑም ተመልክቷል። የግብፅ የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች የአደጋ ጊዜ ቁሳቁሶችን ይዘዉ በሄሌኮብተር ጭምር ህይወትን ለማትረፍ እየተረባረቡ መሆኑን ዜና ምንጬ አክሎ ዘግቧል።
ሶማልያ፤ ሁለት ጀልባ ተገልብጦ የ24 ስደተኞች ህይወት ጠፋ
ህገ-ወጥ ስደተኞችን አሳፍረዉ ሕንድ ውቅያኖስ ማዳጋስካር የባሕር ዳርቻ ላይ ሲቀዝፉ የነበሩ ሁለት ጀልባዎች ተገልብጠዉ የ 24 ሰዎች ህይወት አለፈ። የሶማልያ መንግሥት የወጭ ጉዳይ ሚኒስትር አህመድ ሞአሊም ፊኪ እንደተናገሩት፤ በሁለቱ ጀልባ ላይ ተሳፍረዉ ከነበሩ ሰዎች መካከል የ 46 ሰዎችን ህይወት መታደግ ተችሏል። የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፤ በጀልባዎቹ ላይ የነበሩት አብዛኞቹ ተሳፋሪዎች ወጣት ሶማልያን መሆናቸዉን አክለዉ ተናግረዋል። የጀልባ ላይ ስደተኞቹ ወዴት መጓዝ እንደፈለጉ ግን እስካሁን ግልፅ የሆነ ነገር ባይኖርም በርካታ ወጣት ሶማልያን ኑሮዋቸዉን ለማሸነፍ አዲስ ተስፋን ሰንቀዉ አደገኛ ጉዞን እንደሚያደርጉ አሶሽየትድ ፕሬስ ዛሬ ዘግቧል። በህይወት የተረፉትን ወደ ሃገራቸዉ ለመመለስ እና የአደጋውን ጉዳይ ለማጣራትና በኢትዮጵያ የሶማሊያ አምባሳደር የሚመራ አንድ የልዑካን ቡድን ወደ ማዳጋስካር ለመጓዝ ዕቅድ መያዙም ታዉቋል። የሶማልያዉ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር አህመድ ሞአሊም ፊኪ፤ በሞሮኮ የባህር ጠረፍ ላይ የደረሱ የሌሎች ሶማልያ ስደተኞችን ጉዳይ፤ በሞሮኮ የሚገኙት የሶማሊያ አምባሳደር እየተከታተሉ እንደሆነም አክለዉ ተናግረዋል። ስጉዳዩ ግን የሰጡት ዝርዝር መረጃ የለም። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፍልሰተኞ ጉዳይ ድርጅት፤ ከአፍሪቃ ቀንድ ሀገራት፤ ግጭትድርቅና ረሃብን ሸሽተዉ የሚፈልሱ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን አሳሳቢ ብሎታል። ባለፈዉ ሚያዝያ ወር ወደ የመን በሚወስደው ከታዋቂዉ የጅቡቲ ባህር ጠረፍ ላይ አንዲት ጀልባ ተገልብጣ፣ የ38 ሰዎች ህይወት ሲጠፋ 22 ሰዎች ደግሞ መትረፋቸዉ ይታወሳል።
ኒጀር፤ የአዉሮጳ ኅብረት አምባሳደር ይቀየሩልኝ ስትል ክስ አአረበች
ኒጀር መንግሥት በሃገሪቱ ከሚገኙት ከአዉሮጳ ኅብረት አምባሳደር ሳልቫዶር ፒንቶ ዳ ፍራንሳ ጋር መስራት እንደማይችል እና በአስቸኳይ ሌላ አንባሳደር እንዲተካ ኅብረቱን ጠየቀች። ባለፈዉ የጎርጎረሳዉያን 2023 ዓመት በመፈንቅለ መንግሥት ስልጣኑን የተቆጣጠረዉ የኒጀር ወታደራዊ መሪዎች በሃገሪቱ ከተከሰተዉ ጎርፍ መጥለቅለቅ አደጋ ጋር በተያያዘ አምባሳደሩ 1.3 ሚሊዮን ዩሮ ለድንገተኛ እርዳታ መንግሥታዊ ላልሆኑ ድርጅቶች ሲሰጡ የሃገሪቱን ባለሥልጣናት አላስታወቁም ሲሉ ከሰዋቸዋል። የአዉሮጳ ኅብረት በበኩሉን ክሱን "ከፍተኛ አለመግባባት" ሲል ገልጾታል። በኒጀር መንግሥት ክስ የቀረበባቸዉን የኅብረቱን አምባሳደር ለምክክር ወደ ብራስልስም ጠርቷል። ካለፈዉ ከሰኔ ወር ጀምሮ ኒጀር ዉስጥ በጣለ ከባድ ዝናብ ምክንያት በተከሰተዉ ከፍተኛ ጎርፍ ከ330 በላይ ሰዎች ሞተዋል፤ ከ1.1 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ከመኖሪያ ቀያቸዉ ተፈናቅለዋል። በጎርፍ መጥለቅለቁ አብዛኞቹ የሳህል ሀገሮች ወሳኝ የተባሉ ሀብቶች፣ ትምህርት ቤቶች እና ባህላዊ ቅርሶች ጉዳት ደረሶባቸዋል። የኒጀር የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እርዳታ ለማግኘት ወደ አዉሮጳ ኅብረት ምንም የርዳታ ጥያቄን አቅርቦ እንደማያዉቅ እና አገሪቱ "በራሷ ገንዘብ የጎርፍ መጥለቅለቅ ያስከተለውን ጉዳት እንደምትሸፍን" አክሎ አስታዉቋል።
የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ፤ የራባዩ ገዳዮች በቁጥጥር ስር ዋሉ
የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ባለስልጣናት አንድ ትዉልደ ሞልዶቭያ የእስራኤል ራባይን/የሀይማኖት መሪ/ በመግደል የተጠረጠሩ ሦስት የኡዝቤኪስታን ዜጎችን በቁጥጥር ስር መዋላቸዉን ገለፁ። ከባለፈዉ ሐሙስ ጀምሮ ዱባይ ውስጥ የደረሱበት ጠፍቶ የነበረዉ እና በፀጥታ አስከባሪዎች አስክሬናቸዉ የተገኘዉ የ28 ዓመቱ ራባይ /የሀይማኖት መሪ/ ጺቪ ኮጋንን፤ ግድያ እስራኤል “አሳፋሪ ፀረ ሴማዊ ጥቃት” ስትል አስታዉቃለች። በደህንነቷ፣ በመረጋጋትዋ እና በሃይማኖታዊ መቻቻልዋ በምትኮራዉ እና አብዛኛዉ የሙስሊም ነዋሪዎች ባልዋት የተባበሩት አረብ ኤሜሪትስ፤ የራባዩ ግድያና ሞት፤ ጥቂት ቁጥር ነዋሪዎች ለሆኑት የአይሁድ እና የእስራኤል ማኅበረሰቦች ከፍተኛ ድንጋጤን ነዉ የፈጠረዉ።በግድያ የተጠረጠሩት ሦስቱ የኡዝቤክስታን ዜጎች ትናንት እሁድ በቁጥጥር ስር ከዋሉ እና "የመጀመሪያ ምርመራ" ከተደረገባቸዉ በኃላ መታሰራቸዉን የተባበሩት አረብ ኤሜሪትስ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣዉ መግለጫ አስታዉቋል። ራባይ ኮጋን በየተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ውስጥ የኦርቶዶክስ አይሁድ ድርጅት የሆነው የቻባድ ሃሲዲክ ንቅናቄ ተወካይ ነበሩ። ይህ ንቅናቄ በዓለም ዙሪያ በሚያደርገው የስብከት ጥረት የታወቀ መሆኑን የፈረንሳዩ የዜና አገልግሎት አዣንስ ፍራንስ ፕሬዚስ ዘግቧል።
ጣልያን፤ በመካከለኛዉ ምስራቅ እና ዩክሬይን ላይ የሚመክረዉ የቡድን ሰባት ጉባኤል
«G7» በመባል የሚጠሩት ሰባቱ በኢንዱስትሪ የበለፀጉት አገራት የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በመካከለኛዉ ምስራቅ እና በሩስያ ዩክሬይን ቀዉስ ጉዳይ ላይ ለመምከር ዛሬ ጣልያን መዲና ሮም አቅራቢያ የሁለት ቀን ስብሰባቸዉን ጀመሩ። ከዚህ በተጨማሪ ሰባቱ የበለፀጉት ሃገራት የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ፤ ዓለምአቀፉ የጦር ወንጀለኞች መዳኛ ፍርድ ቤት ICC በእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እና በሃማስ ወታደራዊ አዛዥ ላይ የሰጠውን የእስር ማዘዣ እና "በአሁኑ ጊዜ በሊባኖስና በጋዛ ቀውሶች ላይ ሊያስከትል ስለሚችለዉ ተጽእኖ ላይ" እንደሚወያዩ የጣሊያን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
በጉባዔዉ ላይ የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከንን፤ ጨምሮ የብሪታኒያ፣ የካናዳ፣ የጀርመን፣ የፈረንሳይ እና የጃፓን የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በጣሊያን የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒዮ ታጃኒ አስተናጋጅነት ስብሰባዉን በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።