1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዓለም ዜና፤ ጥቅምት 26 ቀን 2017 ዓ.ም ማክሰኞ

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 26 2017

DW Amharic አርስተ ዜና በአማራ ክልል እየተባባሰ የሄደው ግጭት እንዳሳሰባት አሜሪካ አስታወቀች። በኢትዮጵያ ግጭቶች እልባት ያገኙ ዘንድ የፖለቲካ ውይይቶች መደረግ አለባቸው፤ የሚል አቋም እንዳላትም ገልፃለች።--አሜሪካ 47 ኛዉን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫን እያካሄደች ነዉ። ሁለቱ ፕሬዚዳንታዊ እጩዎች በየፊናቸዉ እንደሚያሸንፉ ተናግረዋል። በሌላ በኩል የአሜሪካ የደኅንነት ባለስልጣናት «የውጭ ኃይሎች» ያሏቸዉ የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እምነት እንዲያጣ ሙከራ እያደረጉ ነው ሲሉ እየከሰሱ ነዉ።--የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሜር ዜሌንስኪ 11,000 የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች ሩስያ ድንበር ኩርስክ ግዛት መግባታቸዉን በስጋት ገለፁ።

https://p.dw.com/p/4mep7

በአማራ ክልል እየተባባሰ የሄደው ግጭት እንዳሳሰባት አሜሪካ አስታወቀች

በአማራ ክልል እየተባባሰ የሄደው ግጭት እንዳሳሰባት አሜሪካ አስታወቀች ። የዩናይትድ ስቴትሱ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒዮ ብሊንከን እንዳሉት «በኢትዮጵያ የእርስ በርስ ግጭቶች እልባት ያገኙ ዘንድ የፖለቲካ ውይይቶች መደረግ አለባቸው ።» የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ  ጋር ባደረጉት  የስልክ ውይይት  «በአማራ ክልል የቀጠለው ግጭት ያሳስበኛል»  ሲሉ ብሊንከን መናገራቸዉን የፈረንሳዩ የዜና ወኪል አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ዛሬ ይፋ ባደረገዉ ዘገባዉ አመልክቷል።  በኢትዮጵያ ውስጥ እየተካሄዱ ያሉ ግጭቶችን ጨምሮ  በአማራ ክልል የሚታየዉን ግጭት መፍትሄ ለማግኘት የፖለቲካ ውይይት እንደሚያስፈልግ ብሊንከን አመልክተዋል። የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊንከን  ከጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ጋር በነበራቸው የስልክ ቆይታ «በፕሪቶሪያው ስምምነት እና አፈጻጸሙ ዙሪያ » መነጋገራቸውን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አክሎ አስታውቋል። ኢትዮጵያ ስምምነቱን ተግባራዊ ለማግረግ የምታደርገውን ጥረት የዩናይትድ ስቴትስ እገዛ እንደማይለያት የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ መናገራቸዉን አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ዛሬ ዘግቧል።  

 

የኢትዮጵያ አየር መንገድ አዲስ አዉሮፕላን ተረከበ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ በአይነቱ የመጀመሪያው ነው የተባለ ኤይርባስ A350-1000 የተሰኘውን አዲስ አውሮፕላን ተረከበ፡፡ አየር መንገዱ ከአውሮፕላን አምራቹ ኤርባስ ኩባንያ የተረከበውን የመጀመሪያውን አውሮፕላን ዛሬ በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለምአቀፍ አየር ፣ማረፊያ አስተዋውቋል፡፡ በአውሮፕላኑ አቀባበል ስነስርዓት ወቅት ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ዛሬ አየር መንገዱ የተቀበለው ኤይርባስ A350-1000 አውሮፕላን አየር መንገዱ ካዘዘው አራት አውሮፕላኖች አንዱ መሆኑን ተናግረዋል።

አዲስ አበባ ዛሬ የገባዉ አዲሱ አዉሮፕላን፤ አቪየሽን ሳንስ ፊሮንተርስ ከኤርባስ በመተባበር ለኢትዮጵያ አየርመንገዶች ፋውንዴሽን ያመጣዉን በ 100 ሺህ ዩሮ የሚገመት የህክምና ቁሳቁስ አስረክቧል። በአቀባበል ሥነስርዓቱ ላይ የመንግስት ባለስልጣናት እና ዲፕሎማቶች ተገኝተዋል። አዲሱ አዉሮፕላን የአየር ብክለትን በመቀነስ ረገድ አይነተኛ ሚና ያለው የአየር ትራንስፖርት ነው ተብሏል፡፡ በአውሮፕላኖች ጥራትና መጠን እራሱን እያሳደገ እንደሚገኝ የገለጸው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቅርቡ የቦሌ ዓለማቀፍ አየር ማረፊያን አቅም በአራት እጥፍ የሚያሳድግ አየር ማረፊያ ቢሾፍቱ አከባቢ መገንባት መጀመሩን ማሳወቁ ይታወሳል፡፡

 

አሜሪካ፤ ፕሬዚዳንትዋን እየመረጠች ነዉ 

ዩናይትድ ስቴትስ 47 ኛዉን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫን እያካሄደች ነዉ። ሁለቱ ፕሬዚዳንታዊ እጩዎች በትናንትናዉ ምሽት ለምርጫ ዉጤቱ ወሳኝ በተባሉባቸዉ ግዛቶች የመጨረሻ የምረጡኝ ዘመቻቸዉን አካሂደዋል። ሁለቱም  እጩዎች ምርጫዉን እንደሚያሸንፉም በየፊናቸዉ ተናግረዋል። የሪፐብሊካን እጩ የሆኑት የአሜሪካ የቀድሞ ፕሬዝዳነት ዶናልድ ትራምፕ በሚሺገን ግዛት የመጨረሻ የምርጫ ቅስቀሳ ባደረጉበት ንግግራቸዉ፤  የተቃጣቸውን የግድያ ሙከራ አውስተዋል። ትራምፕ «ከግድያ ሙከራዎች የተረፍኩት እግዚአብሄር በድጋሚ እኔን ፕሬዝዳንት ለማድረግ እቅድ ስለነበረው ነዉ፤  እግዚአብሔር አሜሪካንን ለመታደግ ፈልጎ እኔን ከሞት እንዳተረፈኝ ብዙ ሰዎች ያምናሉ» ሲሉ ትራምፕ ተናግረዋል። የመጨረሻ የምርጫ ቅስቀሳቸውን በፊላደልፊያ አድርገዉ የነበሩት ዲሞክራቷ ዕጩ ፕሬዝደንት ካማላ ሃሪስ በበኩላቸዉ «አሜሪካ ምን ማለት እንደሆነች፤ አንድ ላይ እንደሆንን ስላሳያችሁኝ አመሰግናለሁ» ሲሉ ደጋፊዎቻቸዉን አመስግነዋል።  ሃሪስ « መራጮች ለዓመታት በፍርሐት እና በክፍፍል የታመሰውን ፖለቲካ ለመቀየር ዕድሉ አሁንም አላቸው ሲሉም ተናግረዋል። 161 ሚሊዮን መራጮች የተመዘገቡ የዩናይትድ ስቴትስ 47ኛ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ፤ መራጮች ዛሬ ከማለዳዉ ጀምሮ ወደ ምርጫ ጣብያ በመሄድ በዴሞክራቲክ ምክትል ፕሬዝዳንት ካማላ ሃሪስ እና በሪፐብሊካኑ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ መካከል ይወስናሉ። ሁለቱም እጩዎች በጎርጎሮሳዉያኑ 2020 ዓ.ም ከፍተኛ መራጭ ቁጥር የታየበት ታሪካዊ የምርጫ ሂደት እንዲደገምም ጠይቀዋል። የዘንድሮ ምርጫ ከምንግዜዉም በላይ ቅድመ ድምፅ የተሰጠበትም እንደሆነ ተነግሯል። እስካሁን 75 ሚሊዮን አሜሪካዉያን መራጮች በደብዳቤ እና በኢሜል ድምፅ መስጠታቸዉ ታዉቋል።    

 

አሜሪካ፤ የዉጭ ኃይሎች የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እምነት እንዲያጣ ሙከራ እያደረጉ ነው 

ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ የአሜሪካ የደኅንነት ባለስልጣናት «የውጭ ኃይሎች» ያሏቸዉ የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እምነት እንዲያጣ ሙከራ እያደረጉ ነው የሚለዉን ክስ አጠናክረዉ ቀጥለዋል።  ባለስልጣናቱ በተለይ ሩስያ የአሜሪካንን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እምነት እንዲያጣ እየሰራች ነዉ ሲሉ ጣታቸዉን ወደ ሩስያ እያሳዩ ነዉ። ከሩስያ ሌላ ሌሎች የውጭ ኃይሎች ያልዋቸዉ “ሕዝቡ በአሜሪካ ምርጫ ላይ ያለው እምነት እንዲሸረሸር እና ክፍፍል እንዲሰፍን” ሙከራ እያደረጉ ነው ሲሉ ከሰዋል። የአሜሪካ ብሔራዊ ደህንነት ዳይሬክተር ቢሮ፣ ኤፍቢአይ እና የሳይበር ደህንነት ድርጅት በጋራ ባወጡት መግለጫ ከሩሲያ ጋር ግንኙነት አላቸዉ ያሏቸዉ ቡድኖች፤ የምርጫ አስተባባሪዎች ላይ አመፅ እንዲነሳ እያደረጉ ነው፤ ምርጫው ተጭበርብሯል የሚል ሐሰተኛ ዜናም እያሰራጩ ነው ብለዋል። «በሩሲያ ተፅዕኖ ሥር ያሉ ቡድኖች» በቅርቡ የምርጫ አስተባባሪዎች በተለይ በአሜሪካ የምርጫ ቁልፍ ግዛቶች፤ ማለትም አሪዞና፤ ኒቫዳ፤ ሚሺገን፤ ቪስኮንሲን፤ ፔንስልቬኒያ፤ ጆርጂያ፤ እንዲሁም ሰሜን ካሮላይና፣ ዉስጥ የምርጫ ሳጥኑን በመሙላት ምርጫውን ለማጭበርበር ሙከራ አድርገዋል የሚል ሐሰተኛ ዜና መለጠፋቸውን መግለጫው ጠቅሷል። በሚቀጥሉት ቀናት መሰል ዜናዎች የበለጠ ሊሰራጩ ይችላሉ የሚል ግምት እንዳለ የሦስቱ ተቋማት የጋራ መግለጫ አክሎ ያሳያል። ከዚህ በተጨማሪ ኢራን ለአሜሪካ «ከፍተኛ የውጭ ስጋት »  መሆንዋም ተጠቅሷል። ይሁንና ቴህራንም ሆነ ሞስኮ በአሜሪካ ምርጫ ጣልቃ ለመግባት እየሞከሩ ነው የሚለውን ዜና የሁለቱም ሃገራት መንግሥታት ማስተባበላቸዉ ተሰምቷል። ሞስኮ ታይምስ የተባለዉ ጋዜጣ የሩስያ መንግሥትን ጠቅሶ ዛሬ እንደዘገበዉ፤ ክሱን መሠረተ ቢስ ሲል አጣጥሎታል።   

 

ዩክሬይን፤ ኩርስክ ዉስጥ የሰሙን ኮርያ ወታደሮች ቁጥር ጨምሯል 

የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሜር ዜሌንስኪ 11,000 የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች ሩስያ ድንበር ኩርስክ ግዛት መግባታቸዉን በስጋት ገለፁ። ዜሌንስኪ ድንበር ላይ ደርሰዋል ያልዋቸዉ የሰሜን ኮርያ ወታደሮች ዩክሬን ዉስጥ ለጦርነት ይላካሉ የሚል ስጋት እንዳላቸዉም ተናግረዋል። ፕሬዚደንት ዜሌንስኪ ትናንት ምሽት በቪዲዮ ባሰራጩት መልክት የሰሜን ኮርያ ወታደሮች በዩክሪይን ድንበር ግዛት ዉስጥ ቁጥራቸዉ መጨመር ስጋት ጉዳይ ከአጋሮቻችን ምንም አይነት ምላሽ አለምስማታችን ግን ያሳዝናል ብለዋል።

«የሩሲያ  በኩርስክ ግዛት ዉስጥ ስለሚገኙ 11,000 የሰሜን ኮርያ ወታደሮች ጉዳይ ዛሬ የስለላ ድርጅታችን ያቀረበዉ አዲስ መረጃ አለ። የሰሜን ኮሪያውያን ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን እያየን ቢሆንም ከጋራዎቻችን ምላሽ እያገኘን ባለመሆኑ ያሳዝናል።» የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች በዩክሬይን ምድር ላይ ለመዋጋት ወይም የዩክሬይን ከፊል ክልል ኩርስክ ግዛት ውስጥ ይዋጉ እንደሆነ እስካሁን የታወቀ ነገር የለም። የዩናይትድ ስቴትስ በመከላከያ ሚኒስቴር ሰሞኑን እንደገለፁት በሩሲያ እስከ 12,000 የሚደርሱ የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች አሉ ማለታቸዉ ይታወቃል። ምዕራባውያን ሃገራት በበኩላቸዉ የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች ሩስያ ዉስጥ መግባታቸዉ ከዩክሬይን ጋር የሚታየዉን ግጭት በከፍተኛ መጠን ያባብሰዋል ሲሉ ስጋታቸዉን ይገልፃሉ።   

 

ሰሜን ኮሪያ በድጋሚ ዛሬ የባላስቲክ ሚሳይል ሙከራ ማድረጓን የደቡብ ኮሪያ ወታደራዊ ኃይል አስታወቀ። በርካታ አጫጭር ተወንጫፊ ባላስቲክ ሚሳይሎች ወደ ጃፓን ባህር አቅጣጫ ከሰሜን ህዋንግሃ ምዕራባዊ ግዛት እንደተተኮሱ የደቡብ ኮሪያ የዜና ወኪል ዮናሃፕ የደቡብ ኮርያ ወታደራዊ ኃይልን ጠቅሶ ዘግቧል። እንደ ደቡብ  ኮርያ ወታደራዊ ኃይል ፤መረጃዉን በዋሽንግተን እና ቶክዮ ከሚገኙት መንግሥታት ጋር መለዋወጡን አስታዉቋል። ፒዮንግያንግ የባላስቲክ ሚሳኤልን ሳይተኩስ አይቀርም ስትል ጃፓን መግለፅዋም ተሰምቷል።  ሰሜን ኮርያ የሚሳይል ተደጋጋሚ ሙከራ ማድረግን ተከትሎ ፤ ደቡብ ኮሪያ፣ ጃፓንና ዩናይትድ ስቴትስ በአንድ የዩናይትድ ስቴትስ ቦምብ ጣይ አውሮፕላን ጨምሮ የጦር ልምምድ ማድረጋቸዉን የጀርመኑ ዜና ወኪል DPA ዛሬ ዘግቧል።

አዜብ ታደሰ / ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ስለዚሕ ዝግጅት

ስለዚሕ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።