የደሴ አላማጣ መንገድ በፋኖ ትእዛዝ ተዘጋ፦ ኗሪዎች በኑሯችን ላይ ጫና ፈጥሮብናል አሉ
ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 2 2017በአማራ ክልል በኢትዮጵያ መንግስትና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል እየተካሄደ በሚገኘዉ ጦርነት ምክንያት ነዋሪዎች ለከፍተኛ ችግር እየተዳረጉ መሆኑን ተናገሩ ። ከደሴ በሀይቅ መስመር ወልድያ፣ ቆቦ፣ ጋሸና፣ ላሊበላ፣ ሰቆጣና ሌሎች ቦታዎች የሚንቀሳቀሱ አሽከርካሪዎች በፋኖ የተጣለዉ የተሽከርካሪ እንቅስቃሴ ገደብ መነሳቱን እስክናረጋግጥ ሥራ ማቆሙ አማራጭ ነዉ ብለዋል ።
ከትናንት በስትያ ጀምሮ በፋኖ ትእዛዝ ተግባራዊ በተደረገዉ የተሽከርካሪዎች ገደብ ምክንያት ለቀናት ከቤታቸዉ እንደወጡ ደሴ ከተማ በሆቴል ዉስጥ ቆይታ ማድረጋቸዉን የነገሩን አስተያየት ሰጪ ለዘመድ ጥየቃ ከአዲስ አበባ ቢመጡም ዘመዶቻቸዉን ለማግኘት መቸገራቸዉን ይናገራሉ ።
ለህክምና መንቀሳቀስ አስቸጋሪ መሆኑ
ሌላዉ ከሰቆጣ ለህክምና እንደመጡ የገለፁልን አስተያየት ሰጭ ባለቤታቸዉ ከሰቆጣ ሆስፒታል ወደ ደሴ ሪፈራል ሆስፒታል ሪፈር ተብለዉ ቢመጡም ከህክምና በኃላ ዳግም ወደ ቤታቸዉ ለመመለስ በተሽከርካሪ እንቅስቃሴ ገደቡ ምክኒያት አለመቻላቸዉን ይናገራሉ ።
በተሽከርካሪ እንቅስቃሴ ገደቡ ምክንያት ከደሴ ወደተለያዩ ቦታዎች ለመጓዝ ቢያስቡም እንዳልቻሉ የገለፁት አስተያየት ሰጭዎቹ ህፃናት አረጋዉያንና እናቶች መቸገራቸዉን ይገልፃሉ ።
አሽከርካሪዎች የእንቅስቃሴ ገደቡ ለሕይወታችን ያሰጋና አሉ
ከደሴ በሀይቅ መስመር ወልድያ፣ ቆቦ፣ ጋሸና፣ ላሊበላ፣ ሰቆጣና ሌሎች ቦታዎች የሚንቀሳቀሱ አሽከርካሪዎች አሁን የተጣለዉ የተሽከርካሪ እንቅስቃሴ ገደብ ለሕይወታችን ጭምር ያሰጋናል ይላሉ፥ እንደ አሽከርካሪዎቹ ገለፃም ገደቡ መነሳቱን እስክናረጋግጥ ሥራ ማቆሙ አማራጭ ነዉ ይላሉ ።
በአማራ ክልል በተለያየ ቦታ በተደጋጋሚ እየተጣለ በሚገኘዉ የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ ገደብ ምክንያት አሽከርካሪዎቹ ከፍተኛ የኑሮ ጫና እየፈጠረብን ነዉ ሲሉ ይናገራሉ ።
ከትናንት በስቲያ ጀምሮ በአማራ ክልል በተለያዩ ቦታዎች በተጣለዉ የእንቅስቃሴ ገደብ ምክንያት አሽከርካሪዎች ባሉበት ለመቆም የተገደዱ ቢሆንም ዛሬ ከአዲስ አበባ ደሴ ዋናዉ መንገድ ለተሽከርካሪዎች ክፍት ሆኖ ዉሏል ። በተሽከርካሪ እንቅስቃሴ ገደቡ ዙሪያ የአማራ ክልል የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጽ/ቤት ኃላፊን ሀሳብ ለማካተት ቢሞከርም ስብሰባ ነኝ በማለታቸው ሳይሳካ ቀርቷል።
ኢሳያስ ገላው
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር