የጀርመን ሽልማት ለአፓርታይድ ሰለቦች ታጋይዋ
ረቡዕ፣ የካቲት 29 2009ለሴቶች ዴሞክራስያዊ መብት ባደረጉት ትግልና በአፓርታይድ ሥርዓት ሰለባ ለሆኑ እርቅ እንዲደረግና ካሣ እንዲከፈል በመታገላቸዉም ነዉ።
«አነ ክላይን» ሃይንሪሽ ቦል ግብረሰናይ ድርጅት ዓመታዊ ሽልማት ያሸነፉት ደቡብ አፍሪቃዊትዋ ኖማሩስያ ቦንሴ ከጆሃንስበርግ ወጣ ብላ ወደ ምትገኘዉ ቶካዛ አነስተኛ ከተማ ወደሚገኘዉ መኖርያ ቤታቸዉ ሲመለሱ ወጣት ሕጻናት፤አዋቂዎችና አዛዉንቶች በዘፈን በዳንስና በጭብጨባ ነበር የተቀበላቸዉ ።
ቦንሴ «ኩሉማኒ » በተሰኘዉና ከ 104 ሺህ በላይ የአፓርታይድ ሰለቦችን በሚረዳዉ ድርጅት ዉስጥ ብሔራዊ አስተባባሪ ሆነዉ ያገለግላሉ። የ2017 «አነ ክላይን» ሽልማት አሸናፊ መሆናቸዉን የሚያበስረዉን ዜና ከሰሙ ጀምሮ ደስታ እና ጥሩ ስሜት ዉስጥ መሆናቸዉን ይገልጻሉ።
«እንደዉ የምሰማዉ እዉን ነዉን ስል ጠየኩ፤ እዉነት መሆኑን ደግመዉ ነገሩኝ ። ከዚም ኖማሩስያ ናት ይህን ሽልማት የምታገኘዉ ስል ደግሜ ጠየኩ፤ እራሴንም አየሁ። ይህን የምስራች ዜና ለቤተሰቦቼና ለቡድኖቼ ስነግር አለቀስኩ። »
ኖማሩስያ ቦንሴ ቶኮዛ በተሰኘት ከተማ ዉስጥ ኩማሎ ጉዳና አጠገብ የሚገኘዉ መኖርያ ቤታቸዉ ለመብታቸዉ እንዲታገሉላቸዉ በሚፈልጉ ሴቶች ተጨናንቆል። አብዛኞቹ ሴቶች ራሳቸዉ አልያም ቤተሰቦቻቸዉ በአፓርታይድ ስርዓት ፍትህ የተጓደለባቸዉ ወሲባዊ ጥቃት የተፈፀመባቸዉና መንግሥት አሁን ካሳ እንዲከፍላቸዉ የሚጠይቁ ናቸዉ። ከነዚህ መካከል ልጁ በአፓርታይድ ዘመን በወታደር የተገደለበት ዳኒሴሌ ማሃንጋ ይገኝበታል። ማሃንጋ ፤ ኖማሩስያ ቦንሴ የ«አነ ክላይን»ን ሽልማት ማግኘትዋ ተገቢ ነዉ ሲሉ ይገልፃሉ።
« በጣም ያስደስታል። ኖማሩስያ ደፋርና ብሩህ አዕምሮ ያላት የድርጅታችን ምሶሶ ናት። እና ያለስዋ ምንም መራመድ አንችልም። የድርጅታችን ዋና ስራ ቀያሽ፤ የሁሉን በር ማንኳኳት የምትችል ልክ እንደ ፕሬዚዳንት ማለት ናት ለኛ። በርግጥም በጣም ጠንካራ ሴት ናት።» የ 70 ዓመቱ ማታምባ ማቴምቡ በበኩላቸዉ ቦንሳ ማኅበረሰቡ ዉስጥ ያለዉን ያለፈ ቁስል ለማሻር ከፍተኛ ስራ እየሰሩ መሆናቸዉን ያምናሉ። በአፓርታይድ ስርዓት ልጃቸዉ የተገደለባቸዉ ማቴምቡ ልጃቸዉ ለምን እንደተገደለ ማወቅ ይፈልጋሉ፤ ካሳም ይጠብቃሉ።
ልጄ በጎርጎረሳዉያኑ 1993 ዓ.ም በጠራራ ፀኃይ ቀትር 8 ሰዓት ላይ ዓይኔ እያየ ነዉ የተገደለብኝ። ከቤት አዉጥተዉ ነዉ የገደሉት። ልጄ አሁን 22 ዓመት የሆነዉን ጨቅላ ሕጻን ልጁን ትቶልኝ ነዉ ያለፈዉ። ያለ ቤተሰብ ከቀረዉ ከዚህ ልጅ ጋር ከፍተኛ ስቃይ አይቻለሁ። አሁንም ስቃይ ላይ ነን ተርብናል፤ ህሊናችን ቆስሎአል። ምንም የተረጋጋ ሕይወት የለንም።»
ቦናሴ ለእነዚህ ሴቶች ካሳ እንዲያገኙ ከመታገል ባሻገር ሴቶች በስፊት ፤ በጓሮ እርሻና የመዝናኛ ፓርክ ሥራ ዉስጥ እንዲሰሩና ገንዘብ እንዲያገኙ ድጋፍ ያደርጋሉ። «መንግሥት ፤ እንዲሰማን እዉቅናና መልስ እንዲሰጠን፤ ለሕዝቡም ካሳን እንዲከፍል እንፈልጋለን። ከለዉጥ ይልቅ በቅድምያ ማሻሻያን እንፈልጋለን።»
ኖማሩስያ ቦንሴ ወጣቶች ታይፕ ማድረግና የኢሜል መልክት እንዲለዋወጡ ኮምፒዉተሮችን አቅርበዋል። ቦንሴ በአፓርታይድ ዘመን የደረሰባቸዉ ከፍተኛ መድሎና እንግልት ዛሬ ድምፅ ለሌላቸዉ እንዲታገሉ እንዳደረጋቸዉ ይናገራሉ።
«አንዳንዴ ይሄን ነገር ሳስብ እንቅልፍ አይወስደኝም።እጅግ ጉስቁልና የደረሰባቸዉ ሰዎች ኖማሩስያ ቦንሴ ለችግራችን መፍትሄ ለማግኘት ሄዳ በር ታንኳኳለች ፤ አንድ ነገርም ይከሰታል ብለዉ ተስፋን በኔ ሲጥሉ ሳይ ህመም ይሰማኛል። አንዳንድ ጊዜ ጤና ሁሉ ነዉ የማጣዉ» በቦንሴ ድጋፍ የሚደረግላቸዉ ሰዎች ከመንግሥት ካሳ እንዲከፈላቸዉ የጠየቁት ጥያቄ መልስ እስኪያገኝ ገና ብዙ ትግል ይጠብቃቸዋል። ለአሁኑ ግን የትግሉን ጓንቲ ለአፍታ ወለቅ አድርገዉ ኖማሩስያ ቦንሴ ለፈፀሙት በጎ ተግባር ሃይንሪሽ ቦል ግብረሰናይ ድርጅት ያበረከተላቸዉን ሽልማት ምክንያት በማድረግ ዳንሱን ድግሱን ማቅለጥ ነዉ።
ቱሶ ኩማሎ/አዜብ ታደሰ
ነጋሽ መሃመድ